Jump to content

ኒነጨር

ከውክፔዲያ
ኒነጨር

ኒነጨር የግብጽ የቀድሞ ዘመነ መንግሥት ፈርዖን ነበረ። በ2ኛው ሥርወ መንግሥት ውስጥ ምናልባት 3029-3014 ዓክልበ. አካባቢ ነበር። ከፈርዖኑ ነብሬ ቀጥሎ እንደ ተከተለ ይታወቃል።

የኒነጨር መቃብርና በርካታ ቅርሶች ተገኝተዋል። በዚሁም ዘመን የሐውልት አሠራር ስራ ገና አዲስ ነበረ፤ ስለዚህ የኒነጨርም መልክ መጀመርያው ከሐውልት የምናውቀው ነው።

የጥንታዊ ዘመን ፈርዖኖች መዝገቦች ወይም 'ንጉሣዊ ዜና መዋዕል' በተለይ ከፍርስራሽ ክፍሎች ይታወቃል፤ «የፓሌርሞ ድንጋይ» የተባለው ትልቅ ክፍል ከኒነጨር ዘመን 15 ሳትኖች ያሳያል። እነዚህ ሳትኖች ከኒነጨር 3ኛ ከብት ቁጠራ እስከ 10ኛው ከብት ቁጠራ ያሳያሉ። እንደ ሌሎች ፈርዖኖች ብዙ የአረመኔ ሥነ ስርዓቶች እንዳካሄደ ያሳያል።

ብዙ ሊቃውንት እንደሚገመቱ የከብት ቁጠራ በየ፪ አመት ተደረገና በድንጋዩ እያንዳንዱ ሳትን ፩ አመት ነው መስሎዋቸው ብለዋል። እንዲህ ከሆነ፣ ይህ ፍርስራሽ ክፍል ከኒነጨር 7ኛ እስከ 20ኛው ዘመነ መንግሥት ያሳያል ይላሉ። ሆኖም የሔሩ ተከታዮች (የፈርዖን ወገን) የአባይ ሸለቆ ከብት ለመቆጠር የወጡ በየአመቱ ከሆነ፣ በድንጋዩ አንዳንድ ሳትን ስድስት ወር ነውና ከኒነጨር 3ኛ እስከ 10ኛ አመት ያሳያል።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ሊቃውንት የኒነጨር ዘመን በሌላው ፍርስራሽ ክፍል «የካይሮ ድንጋይ» በተባለው ክፍል እንደሚቀጠል ያምናሉ። በጠቅላላ ኒነጨር 44 ያህል አመት እንደ ገዙ ይገምታሉ። ሆኖም በውነት በዚህ «ካይሮ ድንጋይ» ክፍል አንዳችም ሊነበብ አይቻልም። በሌላ ግመት የኒነጨር ዘመን በፓሌርሞ ድንጋይ ዓመታት 3-10 ያሳያልና እስከ ካይሮ ድንጋይ ክፍል አልዘረጋም፣ በጠቅላላ 15 ዓመት ያህል ገዛ የሚል ነው።

ከ1500 ያህል አመት በኋላ በግብጽ አዲስ ዘመነ መንግሥት በተቀነባበሩት ፈርዖኖ ዝርዝሮች፣ የአቢዶስ ፈርዖኖች ዝርዝርየቶሪኖ ፈርዖኖች ዝርዝር ሲሆኑ፣ ስሙን «ባ-ነጨር» ይሉታል። የቶሪኖ ዝርዝር ለ96 ዓመታት እንደ ገዛ ሲል ይህ አይታመነም። ከዚህም እንደገና 1000 ዓመታት ያህል በኋላ የማኔቶን ፈርዖኖች ዝርዝር «ቢኖጥሪስ» ይለዋል። ማኔቶን እንዳለን፣ ቢኖጥሪስ ለ47 ዓመት ገዝቶ በእርሱ ዘመን «ሴቶች የፈርዖን ማዕረግ ለማግኘት መብቱን ተቀበሉ።» ከኒነጨር በፊት ግን በ1ኛው ሥርወ መንግሥት ንግሥቶች መርኒትኒትሆተፕ ታውቀዋል።

ከኒነጨር ቀጥሎ ማን እንደ ተከተለው ግልጽ አይደለም። በአንዳንድ አስተሳሰብ የዋጀነስወነግ ወይም ሰነጅ መታወቂያ አንድላይ ነበርና ቢያንስ በደቡቡ ኒነጨርን ተከተለው። በስሜኑ ግን ነፈርካሬ እና ነፈርካሶካር በዚያን ጊዜ እንደ ገዙ ይመስላል። ለነዚህም ስሞች ሁሉ፣ ሰረኽ የተባለው ምልክት አልተገኘም፣ ነገር ግን አዲሱ ካርቱሽ የተባለው ንጉሣዊ ምልክት ከኒነጨር በኋላ ሊታይ ጀመረ። ከጦርነት ጊዜ በኋላ የደቂቀ ሴት ወገን በፈርዖን ፐሪብሰን እንደ ተነሣ ይታመናል።