ፐሪብሰን

ከውክፔዲያ
የፐሪብሰን ሰረኽ በሴት እና ሬ ምልክቶች

ሴት ፐሪብሰን ከ3007-2996 ዓክልበ. ግድም የግብጽ የቀድሞ ዘመነ መንግሥት ፈርዖን ነበረ። ይህ ማኔቶን እንደሚቆጥረው በ፪ኛው ሥርወ መንግሥት ውስጥ ነው።

ከፔሪብሰን አስቀድሞ፣ ከናርመር ጀምሮ እስከ ኒነጨር ድረስ (3101-3014 ዓክልበ ግድም ድረስ) እያንዳንዱ የፈርዖኖች ሰረኽ ስም በጣኦቱ ሔሩ ስም ጀመረ፣ መሉ አርእስታቸውም «ኸንቲ-አመንቲው-ሔሩ- (እገሌ)» ሆኖ ነበር። ከኒነጨር ቀጥሎ ሁኔታው ግልጽ አይደለም፣ በአዲስ መንግሥት የተወረሱት የነገሥታት ዝርዝሮች ይለያያሉ። ምናልባት ነፈርካሬነፈርካሶካር በስሜን ብቻ እየነገሡ ሰነጅ የደቡብ ፈርዖን ሆነ። ከነዚህ ሦስት፣ አንዳችም የሔሩ ስም ወይም ሰረኽ እንደ ነበረው አይመስልም፤ ሁላቸው በአዲስ ምልክት በካርቱሽ ይወከላሉ። ሴት ፐሪብሰን ከነዚህ ቀጥሎ እንደ ነገሠ ይመስላል።

ከሁሉ ጥንታዊ የሆነው ግብጽኛ ሙሉ አረፍተ ነገር

ሴት ፐሪብሰን በተለይ ከቀድሞ ፈርዖኖች የሚለይበት ነገር አርእስቱ በኸንቲ-አመንቲው እና በሔሩ ስሞች የጀመረው ሳይሆን፣ በሔሩ ጠላት በሌላው ጣኦት ሴት ስም ጀመረ። አንዳንዴም የ (የፀሐይ ጣኦት) ምልክት ከዚህ ጋር ይታያል። ፈርዖኖች በፊት ከሔሩ ወገን እየሆኑ፣ በሴት ወገን ላይ ጦር ዘመቻዎች ያድርጉ ነበር። አሁን ግን የሴት ወገን የወከለው ፈርዖን፣ ሴት ፔሪብሰን፣ ግብጽን እንደ ገዛ ይመስላል።

የፐሪብሰን ኅልውና ከመቃብሩና ከበርካታ ቅርሶች ይታወቃል፤ አንዳንድ ጽሑፍ «ኢኒ-ሰትጨት» «የሰትጨት ሰዎች ግብር» ሲል ሰትጨት በኋላ ዘመን ከነዓን የተባለው ምድር እንደ ነበር ይታስባል። ፐሪብሰን በግብጽ ከሠሩት ከተሞች መሃል አንዱ «የሰትጨት (ሰዎች) ከተማ» ተባለ፤ ይህ ለሴት (ሰት) ወገን አንድ መጠሪያ እንደ ነበር ይቻላል።

በተጨማሪ ሌላ የንጉሥ ስም ሔሩ ስኸሚብ ወይም ሔሩ ሰኸሚብ-ፐረንመዓት በሥነ ቅርስ ተገኝቷል፤ በተለይ ይህ ስም በፐሪብሰን መቃብር ውስጥ ተገኝቷል። ለፈርዖን ሰኸሚብ እራሱ ግን መቃብር አይታወቅም፤ ብዙ ሊቃውንት ሁለቱ አንድ እንደ ነበሩ የሚል መላምት አላቸው። በዚህ አስተሳሰብ ፈርዖን ሔሩ-ሰኸሚብ-ፐረንመዓት ስያሜውን ቀይሮ ለዘመኑ መጨረሻ ፈርዖን ሴት-ፐሪብሰን ሆነ። እንዲህ ከሆነ ምናልባት ፈርዖኑ ታማኝነቱን ደግሞ ከሔሩ ወደ ሴት ወገን ቀየረው። ሌሎች ሊቃውንት ግን ሁለቱ የተለያዩ ነገሥታት እንደ ነበሩ ያምናሉ።

ብዙ ጊዜ በሴት ፐሪብሰን ቅርሶች ላይ የ«ሴት-እንስሳ» ወይም አዋልደጌሣ ምልክት በሌላ እጅ ተደምስሷል። ጣኦቶቹ ሴትና ሔሩ በአፈ ታሪክ ጠላቶች እንደ ሆኑ፣ የሴትና የሔሩ ወገኖች ጠላቶች ነበሩ። በዚህ ዘመን ያህል የእርስ በርስ ትግሎች ወይም ጦርነት በግብጽ እንደ ተከሰተ በብዙ ሊቃውንት ይታስባል። በኋላ በአንዳንድ አዲስ ዘመን ነገሥታት ዝርዝሮች ዘንድ፣ በዚህ ፈንታ በግብጽኛ «ኹጀፋ» (ተደመሰሰ) ብቻ ይላል፤ ስለዚህ በጥንታዊው ቅጂ ስሙ በውነት ተደምሰሰ ማለት እንችላለን። አንዳንድ ዘምናዊ ጸሐፊ ግን «ኹጀፋ» የሌላ ፈርዖን ስም እንደሚሆን ይቆጥረዋል። እንዲሁም በመረጃ ጉድለት ምክንያት አያሌ ተቀራኒ አስተሳስቦች ይኖራሉ።

ያም ሆነ ይህ በግብጽኛ መጀመርያው የምናውቀው ሙሉ አረፍተ-ነገር በፐሪብሰን መቃብር ተገኝቷል። «ወርቃማው (ጣኦቱ ሴት) ለልጁ ፐሪብሰን፣ ለላይኛና ታችኛ ግብጽ ንጉስ፣ ሁለቱን ግዛቶች አስረክቧል» ይላል።

ባብዛኛው እንደሚታሠብ፣ የፐሪብሰን ተከታይ ሔሩ-ኻሰኸም ሲሆን እሱ ደግሞ ስሙን ወደ «ሴት-ሔሩ-ኻሰኸምዊ» (2996-2987 ዓክልበ. ግድም) ቀየረው። የሴትና ሔሩ ስያሜዎች አንድላይ የታዩበት ፈርዖን ስም ይህ ብቻ ነበር። «-ዊ» የሚለውም ክፍለ-ቃል «ሁለቱ (አገራት)» ይወክላል፤ ከብሔራዊ ጦርነቱ ቀጥሎ ሁለቱን ወገኖች እንዳዋሐደ ይታስባል። ከርሱም በኋላ የሴት ወገን ስም በፈርዖን አርዕስት ላይ በጥንታዊው መንሥት እንደገና አልታየም ነበር፤ ሰረኾቻቸውም ወደ ሔሩ ስያሜዎች ብቻ ተመለሱ።