ከነዓን (ጥንታዊ አገር)

ከውክፔዲያ
የከነዓን ምርከኞች በግብጽ፤ 1160 ዓክልበ. ገደማ

ከነዓን ጥንታዊ አገር ሲሆን ዛሬ በእስራኤልና በሊባኖስ አካባቢ ያሉትን አካባቢዎች ያጠቃልል ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘንድ እግዚአብሔር ይህን አገር ለአብርሃም ልጆች በቃል ኪዳን ሰጠ።

ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቅድመ-ታሪክ ከማናቸውም መዝገቦች በፊት የሆነ ጊዜ ነውና እዚህ በተለይ ብዙ አስተያየቶች ስላሉ የከነዓን ቅድመ ታሪክ ተከራካሪ ሆኗል። በብዙ ምዕራብ ሥነ ቅርስ ሊቃውንት ዘንድ ኢያሪኮ ከሁሉ አስቀድሞ የተሠፈረው ቦታ ሲሆን በ9000 ዓክልበ. እንደ ተሠራ ይላሉ። ይህን ዕድሜ ለማረጋገጥ ግልጽ አይሆንም። የግብጽ ጥንታዊ መንግሥት ፈርዖኖች (1-6ኛ ሥርወ መንግሥታት) አቅራቢያውን ሰትጨት እንዳሉት ይመስላል፤ አንዳንድ ሰረኾች (የፈርዖን አርማዎች) በተለይም የናርመር ሰረኽ (ከ3100 ዓክልበ. ግድም) እዚያ ተገኝተዋል።

አገሩ በኋላ «ከነዓን» እና «ማር-ቱ» ተብሎ ታሪኩ ከተለያዩ ምንጮች ሊሰበሰብ ይችላል።

መሠረቶች 2425-2225 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኦሪት ዘፍጥረት አገሩ ስለ መሥራቹ ከነዓን (የካም ልጅ) ተሰየመ። በመጽሐፈ ኩፋሌ ዘንድ፣ ካምና ሌሎች ልጆቹ ኩሽምጽራይምፉጥሰናዖር ወደ አፍሪካ በተጓዙበት ጊዜ ከነዓን ግን ሥምምነታቸውን ጥሶ በአርፋክስድ ርስት በዚያው አገር ተቀመጠ። በሱመር አፈ ታሪክ ደግሞ የአሞራውያን ምድር ወይም «ማርቱ» ከኤፍራጥስ ወንዝ ምዕራብ ያለው አገር ሲሆን በዚህ ሰዓት ያሕል (2425 ዓክልበ. ግድም) የሱመር መጀመርያው ንጉሥ ኤንመርካር በማርቱ ላይ ግድግዳ እንዳሠራ ይጠቅሳል።

ከ2390 ዓክልበ. በፊት ከተሞች በጌባልሲዶን (በፊንቄ) ተሠሩ፣ መርከበኞቻቸውም በባሕርና በውቅያኖስ ላይ በመጓዝ አንጋፋዎች ሆኑ። ሌሎችም ከተሞች በሐማትአርቃ ተሠሩ። በ2345 ዓክልበ. ግ. በኤፍራጥስ ላይ የማሪ መጀመርያ ንጉሥ ጋንሱድ ይጠቀሳል፤ ይህም ከተማ ለማር-ቱ (ሶርያ) እና ለመስጴጦምያ የንግድ ማዕከል ሆነ። በስተ ደቡብ የሲዲም ሸለቆ (ሰዶም ወዘተ.) ምናልባት 2235 ዓክልበ. ተሰፈረ።

የእርሻ ተግባር መስፋፋት 2225-2150 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከ2210 ዓክልበ. በኋላ ከግብጽመኮትኮቻ ጥቅም በከነዓን ይስፋፋ ጀመር። በዚህ ዘመን ደግሞ የላጋሽ ንጉሥ ሉማ ከ2200 እስከ 2195 ዓክልበ. ድረስ ማሪን ይዞ ነበር፣ በማረፉ ግን ማሪ ወዲያው እንደገና ነጻ ሆነ። እንዲሁም ከ2175 ዓክልበ. ጀምሮ ከመስጴጦምያ የማረሻ ጥቅም በከነዓን ይስፋፋ ጀመር።

ችግሮችና ፍልሰቶች 2150-2075 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሶርያ በ2116 ዓክልበ.

በ2150 ዓክልበ. ግ. በኋላ ለትንሽ ጊዘ አስጊ ሁኔታ (ጦርነት ወይም ረሃብ) በከነዓን ስለ ደረሰ፣ አንዳንድ ብሔር ወደ ውጭ እንደ ፈለሰ ይመስላል። ከነዚህም መካከል የሲኒ እና የሰማሪዎን ነገዶች በኋላ በኩሽ መንግሥት እንደ ደረሱ በኢትዮጵያ መዝገቦች ይጻፋል።

በ2125 ዓክልበ. ግ. በስሜኑ በሶርያ ተዋዳዳሪ የኤብላና የማሪ ግዛቶች ይበረቱ ጀመር። ከዚህ ትንሽ በኋላ (2122 ዓክልበ.) የሱመር (አዳብ) ንጉሥ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ በደቡብ ያለውን ምድር እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ያዘ። በመጽሐፈ ኩፋሌ አቆጣጠር አብርሃምሣራ ወደ ከነዓን የፈለሱ በ2118 ዓክልበ. ሲሆን የሰናዖር ንጉሥ አምራፌልን ዘመን ያሳስባል። ያንጊዜ ኬብሮንደማስቆ ከተሞች፣ በኋላም ሐቲ አገር ወደ ስሜኑ በኬጥያውያን ተሠፈሩ። በ2115 ዓክልበ. ረሃብ በከነዓን ስለ ሆነ አብርሃምና ሣራ ወደ ግብጽ ወረዱ፤ እንዲሁም በ2110 ዓክልበ. የቅማንት አባት ከነዓናዊው አይነር ወደ ኩሽ እንደ ፈለሰ ይዘገባል። በ2108 ዓክልበ. ሰዶምና ሌሎቹ የሲዲም ከተሞች ከአምራፌል አገዛዝ አመጹ፣ በሚከተለውም አመት የአምራፌል ሃያላት መጥተው የአብርሃም ሥራዊት ግን አጠፋቸው። በዚህ ጊዜ በሱመር ታሪክ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ ወድቆ የሱመር ላዕላይነት ለጊዜው ወደ ማሪ እንዳለፈ ይመስላል። የሰዶም ጥፋት በኩፋሌ አቆጣጠር በኋላ በ2092 ዓክልበ. ከእሳት ደረሰ። በ2080 ዓክልበ. ግድም ሳሌም (ኢየሩሳሌም) ተመሠረተ።

የአካድ መንግሥት ዘመቻዎች በሶርያ 2075-2015 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ2074 ዓክልበ. (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን ኤብላን አጠፋና በስሜኑ ሶርያን ያዘ። ከ፲ አመት በኋላ ሳርጎን ባረፈ ጊዜ ግን ሶርያ እንደገና ነጻ ሆነ፣ ያንጊዜ ወደ ግብጽ ተጽእኖ ተዛወረ። የሶርያና በተለይም የሊባኖስ ግንኙነት ከግብጽ ጋራ ምንጊዜም በመርከብ ይካሄድ ነበር።

በ2036 ዓክልበ. ደግሞ የሳርጎን ተከታይ ናራም-ሲን በሶርያና ሊባኖስ አካባቢ ዘመተ፤ እርሱም ከ፮ አመት በኋላ አርፎ አገሩ እንደገና ነጻ ሆነ። በአንድንድ ዜና መዋዕል ዘንድ ኢያሪኮ በዚህ ወቅት ያህል ተሰፈረ።

በ2021 ዓክልበ. የአካድ ንጉሥ ሻርካሊሻሪ እንደገና በአሞራውያን ላይ በሶርያ ዘመተ። በዚህም ወቅት ያህል ነባታያውያንእስማይል ልጆች በደቡባዊ በረሃ ማዶ ተመሠረቱ።

የግብጽ ተጽእኖ 2015-1860 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከአካድ መንግሥት በኋላ የግብጽ ተጽእኖ እንደገና ወደ ሶርያና ሊባኖስ ተመለሠ።

ከኩፋሌ አቆጣጠር ያዕቆብዔሳው ስለ ረሃብ ምስር ወጡን የሼጠበት አመት 1991 ዓክልበ.፣ ይስሐቅም ወደ ጌራራ ፍልስጥኤማውያን ንጉሥ አቢሜሌክ የሄደበት አመት 1990 ዓክልበ. ሆነ።

በአንድ ግብጻዊ ጽሑፍ «የሲኑሄ ታሪክ» ዘንድ፣ የ1 ሰኑስረት አለቃ ሲኑሄ በ1972 ዓክልበ. አካባቢ በረጨኑ (ስሜን ከነዓን ወይም ሶርያ) ይዘመት ነበር። በኋላ በተከታዩ 2 አመነምሃት ዘመን በ1932-1930 ሥራዊቱ በሶርያና ሊባኖስ እንደ ዘመተ ይዘገባል። የብርጭቆ መሥራት ኢንዱስትሪ የተጀመረው በፊንቄ በዚህ ወቅት ያህል እንደ ነበረ ይመስላል።

በደቡቡ ግን በዚሁ ወቅት የያዕቆብ (እስራኤል) ሥራዊት ይበረታ ነበር። በ1928 ዓክልበ. የሴኬም ንጉሥ ኤሞርን አጠፉ፣ በ1923 ዓክልበ. አሞራውያን አሸነፉ፣ በ1909 ዓክልበ. የዔሳው ስራዊት (ኤዶምያስን) አሸነፉ።

አሞራውያንም በዚህ ሰዓት በመስጴጦምያ ውስጥ ይበዙ ጀመር። በ1899 ዓክልበ. ታላቁ ረሃብ በደረሰ ጊዜ፣ አሞራውያን የኢሲን መንግስት በሱመር መሠረቱ፣ የያዕቆብም ቤተሠብ ከከነዓን ወደ ጌሤም ወረዱ።

ዕብራውያን በጌሤም እየኖሩ የግብጽ ፈርዖን 3 ሰኑስረት በ1884 ዓክልበ. ምድያም፣ ሴኬምና ረጨኑ ወርሮ ያዘና የከነዓን ምድር ለጊዜው ወደ ግብጽ መንግሥት ተጨመረ። ይህም ሰኑስረት እስካረፈበት ጊዜ እስከ 1859 ዓክልበ. ድረስ ቆየ፣ ያንጊዜ ከነዓን እንደገና ከግብጽ ነጻ ሆነ።

አሁን ከዕብራውያን በላይ በርካታ ሌሎች ከነዓናዊ ያልሆኑት ህዝቦች በአካባቢያቸው ተገኙ፦ ፍልስጥኤማውያን እንደ ከነአናዊ አልተቆጠሩም፣ እንዲሁም ኤዶምያስ፣ ምድያም፣ ነባታያውያን፣ ሞአብአሞንአማሌቅ የተባሉት አገሮች ሁላቸው ከሴማውያንና ከዕብራውያን ዘመዶች ተነሡ።

ነጻ ከተማ-አገሮች 1860-1620 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የያምኻድ መንግሥት ጫፍ፣ 1673 ዓክልበ.

ከሰኑስረት በኋላ፣ ከነዓን እንደገና ነጻ ከተማ አገሮች ሆነ። አሞራውያን አለቆች በመስጴጦምያ ጉዳይ ጥልቅ እያሉ፣ ዕብራውያን በጌሤም፣ የአሦርካሩም በሐቲ ነጋዴዎች የሆኑበት ወቅት ነበር።

በዚህ ዘመን ያሕል (ምናልባት ከ1800-1400 ዓክልበ. ግድም) በጌባል (ቢብሎስ) ከተማ እስካሁን ሊነበብ የማይቻለው የጌባል ጽሕፈት ከግብጽ ሃይሮግሊፎች እንደ ተለማ ይታስባል።

በጌሤም ዕብራውያን ከ1821 እስከ 1742 ዓክልበ. ድረስ የየራሳቸውን 14ኛው ሥርወ መንግሥት የነበራቸው ይመስላል። በ1808 ዓክልበ. ግን የግብጽ ፈርዖን ከከነዓን ንጉሥ መምካሮን ጋር ጦርነት ስላደረገ የግብጽ በሮች እንደ ተዘጉ በኩፋሌ ይዘገባል። ከከነአን ስለደረሱ ዕብራውያንም ከዚህ በኋላ በጥርጣሬ ይታዩ ጀመር። ከ1742 ዓክልበ. በኋላ በጌሤም የነበሩት ወደ ባርነት ተገደዱ።

ከዚያ በኋላ በሶርያ ከተማ ሐለብ ዙሪያ የያምኻድ መንግሥት ተነሣ። የያሚና ልጆች ወይም «ብኔ-ያሚና» (የቀኝ ልጆች) የተባለ ብሔር ከያምሓድ ቢደገፍም፣ የማሪ ነገሥታት ከ1720-1690 ዓክልበ. ይዘመቱባቸው ነበር።

ዕብራውያን ከግብጽ በጸአት አምልጠው በ1661 ዓክልበ. ግ. የግብጽ ሃይል እጅግ ደክሞ ወዲያው ሌሎች አሞራውያን «ሂክሶስ» ግብጽን ወርረው እንደ ገቡ ይመስላል። በኦሪት መሠረት፣ ከ፵ ዓመት በኋላ ዕብራውያን በሙሴ መሪነት ከዮርዳኖስ ምዕራብ የተገኙት አሞራውያን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን አሸነፉዋቸው፤ በኋላም በኢያሱ ወልደ ነዌ መሪነት ከዮርዳኖስ ምሥራቅ የነበሩትን ከነዓናውያን አሸነፉዋቸው። በያህዌ ትዕዛዝ ሀገሩ ለአብርሃምና ለአርፋክስድ ሰጥቶ ስለሆነና ስለከነዓናውያን አስቀያሚ መረንነት እንደ ነበር በኦሪትም ይገልጻል። ከነዓናውያን ግን በጥቂት ሥፍራዎች ቀሩ፣ እስራኤልም በበረታ ጊዜ ለዕብራውያን አገልጋዮች ሆኑ።

የሃቢሩ ዘመንና ዘመነ መሳፍንት 1620-1050 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከእስራኤላውያን ወረራ በኋላ 1587 ዓክልበ. በመጽሐፈ ኢያሱ ዘንድ

የዕብራውያን ወረራ በከነዓን በተለይ በመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ ይገለጻል። መጀመርያ ኢያሪኮንና ጋይን ያዙ፣ ከዚያም ገባዖን ተገዛላቸው። አምስት የአሞራውያን ነገሥታት፦ የኢየሩሳሌም ንጉስ አዶኒጼዴቅ፣ የኬብሮን ንጉሥ ሆሃም፣ የየርሙት ንጉሥ ጲርአም፣ የለኪሶ ንጉሥ ያፊዓ፣ የኦዶላም ንጉሥ ዳቤር ለመቃወም ተሰብስበው ኢያሱ አጠፋቸውና ደቡቡን ከነዓን ሁሉ ያዘ። ትልቅ ተዓምራት እንደ ተደረጉ ይጻፋል። ካሌብ ኬብሮን የተሰጠው ከጸአት 45 ዓመት በኋላ (ኢያሱ 14:10) ወይም በ1616 ዓክልበ. ነበር። ከዚያ የአሶር (ሐጾር) ንጉስ ኢያቢስና የማዶን ንጉሥ ዮባብ በስሜን ተቃወሙት፣ ኢያሱም አሸነፋቸውና ሐጾርን አቃጠለ። ከኢያሱ ዘመቻዎች በኋላ የከነዓን ሰዎች በአንዳንድ ቦታዎች በተለይ በፍልስጥኤምና በፊንቄ አካባቢ ቀሩ።

ወደ ስሜኑ በሶርያ የያምኻድ ንጉሥ እርካብቱም (1587-1575) ከ«ሃቢሩ ወገን አለቃ «ሰሙማ» ስምምነት እንዳደረገ ይዘገባል። ከዚህ ጀምሮ «ሃቢሩ / አፒሩ» የተባለው ወገን በከነዓን ምድር ሃይለኛ ወገን እንደ ነበሩ በብዙ መዝገቦችና ሰነዶች በእርግጥ ይታወቃል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝነት ለምዕራባውያንና ለአይሁዳውያን ሊቃውንት እጅግ ተከራካሪ በመሆኑ ምክንያት፣ ስለዚህ የ«ሃቢሩ» መታወቂያ ከዕብራውያን ጋር አንድ አይሆንም፣ ይህም እንግዲህ ከግድ አጋጣሚ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው። በ1550 ዓክልበ. ግድም የሶርያ ሑራውያን ቲኩናኒ ከተማ ንጉሥ ቱኒፕ-ተሹፕ በሥራዊቱ የተገኙት ሃቢሩ ስሞች በቲኩናኒ ፕሪዝም ላይ ሲዘረዝር፣ ብዙዎቹ ሑርኛ፣ የተረፉትም ሴማዊ ስሞች ነበሩዋቸው።

በ62 ዓም ገደማ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊነት የተባለው መጽሐፍ ብቻ ከኢያሱ ዘመን ቀጥሎ ስለ ፈረዱት ቄኔዝዜቡል 82 ዓመታት ይዘርዝራሉ። በ1548 ዓክልበ. አዲሱ ግብጻዊ ፈርዖን 1 አሕሞስ ሂክሶስን አባርረው ሂክሶስ በደቡብ ሻሩሔንን ከስሜዖን ርስት ያዙ። አሕሞስ ከብቦት ከ6 ዓመት በኋላ ሻሩሔንን አጠፋ። በ1537 ዓክልበ. ደግሞ የአሕሞስ ባሕር ሃይል በጌባል፣ ፊንቄ አካባቢ እንደዘመቱ ይመስላል። በዚህም ዘመን የኬጥያውያን መንግሥት ከስሜን ወደ ሶርያ ገብተው በ1531 ዓክልበ. ሐለብን ይዘው የያምኻድን መንግሥት አስጨረሱ። በኋላ ፈርዖኑ 1 ቱትሞስ በ1513 ዓክልበ. ግድም በሶርያ ሑራውያን (ናሐሪን) ላይ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ እንደ ዘመተ ይመስላል። ተከታዩም 2 ቱትሞስ ደግሞ (1500 ዓክልበ. ግድም) «ሻሱ» በተባለ ወገን ላይ በከነዓን ይዘምት ነበር። እነዚህም «ሻሱ» (ማለት «ዘላኖች») በግብጽ መዝገቦች ከ1500-1200 ዓክልበ. ያሕል ሲገኙ፣ «ሃቢሩ» ያልሆነ ሌላ የተለየ ወገን ናቸው፤ መታወቂያቸውም ተከራካሪ ሆኗል። ከኤዶምያስና ከዙሪያው እንደ ወጡ ቢመስልም፣ እኚህ «ሻሱ» በውነት የአይሁድ አባቶች እንደ ሆኑ የሚሉ አስተሳስቦች ይኖራሉ።

በ1506 ዓክልበ. ግድም የመስጴጦምያ (ዕብራይስት፦ አራም-ናሐራይም) ንጉሥ ኲሰርሰቴም ወርሮ እስራኤልን ገዛ። በዚሁ ዘመን ደቡብ መስጴጦምያ ወይም ባቢሎንካሣውያን ወገን እየወደቀ፣ በስሜኑ መስጴጦምያና ሶርያ ደግሞ ሑራውያን የተባሉት ነገዶች በሚታኒ ገዥነት ወደቁ፣ አገራቸውም በተጫማሪ «ናሓሪን» («ሁለቱ ወንዞች») ይባል ነበር። የሚታኒ መጀመርያ ንጉሥ ኪርታ ሲባል እርሱ ከሶርያ በላይ ምናልባት መላውን ከነዓን ያስተዳደር ነበር። ያም ሆነ ይህ ከ8 ዓመታት በኋላ (1497 ዓክልበ.) ጎቶንያል የናሓራይም ሥራዊት እንዳሸነፈና የእስራኤል ፈራጅ እንደ ሆነ በመጽሐፈ መሳፍንት እናንባለን። በ1473 ዓክልበ. ግድም በሶርያ «ሃቢሩ» ከሐለብ መስፍን ኢድሪሚ ጋር ተባብረው አላላኽን ለመያዝ እንደ ረዱት ይታወቃል።

ከነዓናውያን በባሕር ዳርና በመጊዶ አካባቢ ቀርተው ነበር (መሳፍንት 1:27)። በ1465 ዓክልበ፣ ፈርዖኑ 3 ቱትሞስ በባሕር ዳር ላይ ገስግሦ የመጊዶ እና የቃዴስ አሞራውያን ነገሥታትን በታላቁ መጊዶ ውግያ ድል አደረጋቸው። ሃቢሩ ፍላጻ ወርዋሪዎች በፈርዖኑ ሥራዊት እንደ ተገኙ ይዘገባል። በሚከተሉት አመታት እስከ 1437 ዓክልበ ያህል ድረስ የግብጽ ሥራዊት ሶርያን ከሚታኒ መንግሥት ያዙ። በደቡብም፣ በመሳፍንት መሠረት ሞአባውያን (ከአሞንና አማሌቅ ብሔሮች ተባብረው) በእስራኤላውያን ላይ ከ1457 እስከ 1439 ዓክልበ ድረስ ወይም ፈራጁ ናዖድ የሞአብን ንጉሥ ዔግሎምን እስካሸነፈው ድረስ ገዝተው ነበር። የ3 ቱትሞስ ተከታይ 2 አመንሆተፕ እንዲሁም እስከ 1426 ዓክልበ ድረስ በሚታኒ ላይ በሶርያ ዘምቶ፣ በዚያው ዓመት ስምምነት ተደረገና በታላቅ አገራት ግብጽ፣ ሚታኒ፣ ባቢሎንና ኬጥያውያን መካከል ዲፕሎማስያዊ ግንኙነቶች ተመሠረቱ።

ናዖድ ሞዓባውያንን ካሸነፈ በኋላ እስራኤላውያን ለ80 ዓመት ወይም 1439-1359 አክልበ. ድረስ ነጻ ነበሩ። በዚያ ዘመን ወደ መጨረሻ ሴመጋር 600 ፍልስጥኤማውያን በበሬ መውጊያ እንደ ገደላቸው በመሳፍንት 3:31 ይዘገባል፤ ስለዚያ ወቅት ከዚህ በላይ አይነግረንም። ከ1400 ዓክልበ. ገደማ ጀምሮ በሶርያ ባሕር ዳር ላይ የነበረው ትልቅ ከተማ ኡጋሪት ሰዎች ለሴማዊ ቋንቋቸው የራሳቸውን አልፋቤት ፈጠሩ፣ እስከ 1200 ዓክልበ. ድረስ ይጻፍ ነበር። ይህ የኡጋሪት አልፋቤት እንደ ኩኔይፎርም መሰለ፣ የፊደሎቹም በሁለት ቅደም ተከተሎች እንደ ግዕዝ (አ፣ በ፣ ገ፣ ደ) ወይም (ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ) መሰሉ። (ሌላው ኩኔይፎርም ያልሆነ «ቅድመ-ከነዓናዊ» የተባለው ፊደል ከቅድመ-ሴማዊ ጽሕፈት የተደረጀ ሲሆን ከ1200 ዓክልበ. በፊት ብዙ አልታየም፤ ይህ ግን ከ1050 ዓክልበ. ጀምሮ የፊንቄ አልፋቤት ስለ ወለደ በዚያ ለአውሮፓ ዘመናዊ አልፋቤቶች ሁሉ ወላጅ ሆነ።)

1350 ዓክልበ. ግድም - የሃቢሩ ጥቅሶች በአማርና ደብዳቤዎች ያሳያል።

ከ1369 እስከ 1339 ዓክልበ. ድረስ ደግሞ በግብጽ የተገኙት የአማርና ደብዳቤዎች ዘመን ነው። ብዙዎቹ ደብዳቤዎቹ በአካድኛ (ኩኔይፎርም) ከከነዓን ገዦች ወደ ፈርዖኖች 3 አመንሆተፕአኸናተን ተጽፈው፣ የሃቢሩ ወገን በከተሞቻቸው ላይ እንደ ታገሉ ይመስክራሉ። በስሜኑ፣ አንዳንድ ሃቢሩ ከአሞራውያን አለቆች አብዲ-አሺርታና ልጁ አዙሩ ጋር ተባብረው የሊባኖስን ጠረፍ ከኡጋሪት ወደ ደቡብ እስከ ሲዶና ድረስ እየቃሙ ነበር። ወደ ደቡብም፣ ሃቢሩ ወገኖች ከሴኬም ንጉስ ላባያ ጋር ተባብረው ለጊዜው ሐጾርን ይዘው ብዙ ከነዓናዊ ከተሞች ከነመጊዶና ኢየሩሳሌም ለፈርዖን እርዳታ ይለምኑ ነበር። ከዚህም ወቅት ጀምሮ «አሕላሙ» (የአራም ሕዝብ) በሶርያ ገብተው ብዙ ጊዜ ይጠቀሱ ጀመር። በ1359 ዓክልበ. መጽሐፈ መሳፍንት እንዳለን፣ የሐጾር ንጉሥ ያቢስ (ያቢን ወይም እብኒ) እና አለቃው ሲሰራ 900 ሠረገላዎችን ይዘው እስራኤልን አሸነፉ፣ ለሃያ ዓመት ገዙአቸው። በ1339 ዓክልበ. ነቢይቱ ዲቦራባራክም እንደገና ያቢስን ድል አደረጉት።

በዚህም «አማርና ደብዳቤዎች ዘመን» ኬጥያውያን እንደገና ወደ ደቡብ ገፍተው ከ1357 ዓም ጀምሮ ሚታኒ ይገዛላቸው ነበር። አሦራውያንም ያንጊዜ እንደገና ነጻ ሆነው ይበረቱ ጀመር፤ ከ1327 ዓክልበ. በኋላ ሚታኒ ለነርሱ ይወድቅ ጀመር። ተወዳዳሪ የግብጽና የኬጥያውያን ነገሥታት ብዙ ጊዜ በሶርያ ይዘመቱ ነበር፤ በመጨረሻ በትልቁ የቃዴስ ውግያ በ1282 ዓክልበ. ኬጥያውያን የፈርዖኑን 2 ራምሴስ ስራዊት ድል አደረጉ። በ1266 ዓክልበ. ራምሴስ ከኬጥያውያን መንግሥት ጋር ዘላቂ ስምምነት ተዋዋለ። ከ1299 እስከ 1292 ዓክልበ. ድረስ ግን ዕብራውያን ለምድያምና አማሌቅ ሰዎች ተገዝተው ሰብላቸውን እንደቀሙ በመሳፍንት እናብባለን። ከዚያ ጊዴዎን የተባለው ፈራጅ ምድያምን አሸንፎ ነገስታቸውን ዛብሄልንና ስልማናን ገደላቸው፤ እስከ 1252 ዓክልበ. ድረስ ፈራጅ ሆነ። የግብጽም ሰነዶች በዚሁ ዘመን ያህል አሸር የተባለውን ዕብራውያን ነገድ በዙሪያው ጠቅሰዋል።

ከጊዴዎን በኋላ በመሳፍንት ዘንድ አቢሜሌክ ለሦስት አመት (1252-1249 ዓክልበ.) በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነ። የራሱ ከተማ ሴኬም ስለ አመጸበት አጠፋው። ከእርሱ ቀጥሎ ቶላ 1249-1226 ዓክልበ. ፈራጅ ሆነ ይለናል፤ ከዚያም ኢያዕር 1226-1204 ዓክልበ. ፈራጅ ሆነ። የኢያዕር ልጆቹ 30 ከተሞች በገለዓድ አካባቢ አስተዳደሩ ይለናል። በ1215 ዓክልበ. ግድም ግን የራምሴስ ተከታይ መርነፕታህ እንደ ዘገበ የእስራኤልን ስም በንቀት ሥፍራ ጠቅሶ «የእስራኤል ዘር ጠፍቷል» በማለት የመርነፕታህ ጽላት አስቀረጸ።

የመርነፕታህ ተከታይ 2 ሴቲ 1205 ዓክልበ. ግድም የመዳብ ማዕድንና የአረመኔ ጣኦት መቅደስ በኤዶምያስ አበጀ። ከ1204-1186 ዓክልበ. እስራኤላውያን በገለዓድ ሆነው ለአሞንና ለፍልስጥኤም ሰዎች ተገዙ። የአሞን ንጉሥ ስም አይሰጠም፤ በዚህ ዘመን በግብጽ ላይ ንግሥት ትዎስረት እያለች በአንዱ ፓፒሩስ ሰነድ ዘንድ «የርሱ» ወይም «ሱ» የተባለ አለቃ መላውን ከነዓን ይገዛ ነበር። በዚህም ጊዜ «የባሕር ሕዝቦች» የተባሉት ወገኖች አናቶሊያን እስከ ስሜን ሶርያ ድረስ ወርረው የኬጥያውያን መንግሥት እንዳጠፉ ይታስባል፣ በሦስት ራምሴስ ዘመን በግብጽ ላይ ጥቃት አደረጉ፣ በከነዓንና በፍልስጥኤም ደግሞ እንደ ሰፈሩ ይታስባል።

በ1186 ዓክልበ. ዮፍታሔ የአሞንን ንጉሥ አሸነፈ፣ ነገደ ኤፍሬምንም አሸነፈ፣ በገለዓድ (እስራኤል) እስከ 1180 ዓክልበ. ፈረደ፣ ከዚያም ኢብጻን 1180-1173 ዓክልበ.፣ ኤሎም 1173-1163 ዓክልበ.፣ ዓብዶን 1163-1155 ዓክልበ በዕብራውያን ላይ ፈረዱ። ግብጽም እስከ 1155 ዓክልበ ድረስ ያሕል ኢዮጴን በፍልስጥኤም ያስተዳድር ነበር። በ1155 ዓክልበ. ግን ፍልስጥኤም በርቶ እስራኤልንም ይገዛ ጀመር።

በ1135 ዓክልበ. በፍልስጥኤማውያን ሥር እየቆዩ ሶምሶን የእስራኤላውያን አለቃ ሆነ። ከ1122 ዓክልበ. ጀምሮ የአሦር መንግሥት በአራም ላይ በሶርያም እስከ ሊባኖስ ድረስ ይዘምቱ ጀመር። በ1115 ዓክልበ. ኤሊ የእስራኤል ፈራጅ ሆነ። በ1076 ዓክልበ. ፍልስጥኤማውያን ታቦትን ማረኩ፤ በሚከተለው አመት ግን ሳሙኤል አስመለሰው። በ1055 ዓክልበ. ሳሙኤል ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን አደረገ።

የከነዓን ቅሬታ፣ ፊንቄና ቀርጣግና 1050-150 ዓክልበ.[ለማስተካከል | ኮድ አርም]