Jump to content

አምራፌል

ከውክፔዲያ

አምራፌልኦሪት ዘፍጥረት 14 መሠረት በአብራም (አብርሃም) ዘመን የገዛ የሰናዖር ንጉሥ ይባላል።

ሲዲም ሸለቆ (በጨው ባሕር አጠገብ) የተገኙት 5 ከተሞች የኤላም ንጉሥ የኮሎዶጎምር ተገዦች ሆነው ከዐመጹበት በኋላ፥ አምራፌል ከኮሎዶጎምር 3 ጦር ጓደኞች መካከል ሆኖ አብረው በዘመቻ ላይ ሔዱ። በመጀመርያ «ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይምዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፤ የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፤ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴሶን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ» (ቁ. 5-7)። እነኚህ በሲዲም ሸለቆ ዙሪያ የነበሩት አገሮች ናቸው።

ከዚያ የሲዲም ሸለቆ 5 አመጻኛ ነገስታት ለውግያ ተሠለፉ። እነርሱም የሰዶም ንጉሥ ባላ፥ የገሞራ ንጉሥ ብርሳ፥ የአዳማ ንጉሥ ሰነአብ፥ የሰቦይም ንጉሥ ሰሜበር እና «ዞዓር የተባለች የቤላ» ንጉሥ ነበሩ። 4 ነገሥታት በ5 ነገሥታት ላይ ስለ ሆነ፣ ይህ ብዙ ጊዜ «የነገሥታት ጦርነት» ተብሏል።

በውግያው የሲዲም ሸለቆ ሓያላት ተበተኑና የነኮሎዶጎምር ሠራዊት ከብታቸውንና ብዙ ምርከኞች ዘርፈው ሔዱ። ከነዚህም ውስጥ የአብራም ዘመድ የሆነው ሎጥ ተማረከ።

ሰለዚህ አብራም በሰማው ጊዜ፣ 318 ሎሌዎቹን አሠለፈና እስከ ዳን (በስሜን ከነዓን) ድረስ ተከተላቸው። አገኝቷቸው መታቸውና አብራም እነኮሎዶጎምርን አሸንፎ እስከ ሖባ ድረስ (በደማስቆ ሶርያ አካባቢ) አሳደዳቸው።

መጽሐፈ ኩፋሌ ይህ ታሪክ በአጭሩ ሲሰጥ፣ የሰናዖር ንጉሥ ስም አማልፋል ተጽፎ ይታያል (11:33)።

የ«አምራፌል» ስዕል በ1900 ዓም ግድም በሩስኛ በታተመ የአይሁዶች መዝገበ ዕውቀት እንደ ታየ፤ እንዲያውም ግን ይህ የሃሙራቢ ቅርስ ይሆናል።

ኩኔይፎርም ጽሕፈት ማንበብ ዕውቀት ለብዙ መቶ ዓመት ጠፍቶ፣ እንደገና ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተፈታ። ከዚያ በፊት፣ አንድ የመስጴጦምያ ነገሥታት ዝርዝር በግሪክ ከተወረሱት መዝገቦች ታውቆ ነበር። በዚያው ዝርዝር ላይ አንድ ንጉሥ «አራሊዩስ» ወይም «አራልዮስ» ተብሎ ይገኛል። ይህ አራልዮስና የመጽሐፍ ቅዱስ አምራፌል አንድ ሆነው በረጅም ዘመን መምህሮች ተቆጠሩ።

ኩኔፎርምን ማንበብ ከተቻለ በኋላ፣ በ1880 ዓ.ም. ጀርመናዊው መምህር ኤበርሃርት ሽራደር የአምራፌል መታወቂያ ከባቢሎን ንጉሥ ሐሙራቢ ጋር አንድላይ ይሆናል የሚለውን ሃልዮ አቀረበ። ይህ ሃሣብ ቀድሞ በብዙዎች ተቀባይነት ነበረው።

አሁን ግን ይህ መታወቂያ በሰፊ አይታስብም። ባቢሎን በመካከለኛው መስጴጦምያ የተነሣ ከተማ ሲሆን ደቡብ መስጴጦምያ በሙሉ ከእርሱ «ባቢሎኒያ» ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ ከ1800 ዓክልበ. በኋላ ነበር። አብርሃም በኖረበት ዘመን ግን፣ «ባቢሎን» መቸም አይጠቀስም፣ ይልቁንም የደቡብ መስጴጦምያ መጠሪያ በዚያን ጊዜ «ሰናዖር» ተባለ። ስለዚህ የአብርሃም ወቅት ከባቢሎን ቀድሞ በነበረው በሱመር ነገሥታት ዘመን ይመስላል።

በመጽሐፉ ዘንድ፣ የኤላም ንጉሥ አለቃቸው ቢመስልም፣ የአምራፌል ስም ከሁሉ መጀመርያ (14:1) የተጠቀሰበት ምክንያት አይታወቅም። እስከሚታወቅ ድረስ፣ ከሱመር ነገሥታት ሁሉ በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ የዘመተ ንጉሥ ከሉጋል-አኔ-ሙንዱ በስተቀር አንዳችም አልነበረም። የዚሁ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ መንግሥት (2152-2107 ዓክልበ. ግድም) ከነዓንን፣ ሶርያንና ኤላምንም እንደ ጠቀለለ በአንድ ሰነድ ላይ ተቀረጸ።