ካሣውያን

ከውክፔዲያ

ካሣውያን (አካድኛ፦ ካሹ፣ ካሥኛ፦ ጋልዙ) በጥንት ከዛግሮስ ተራሮች (ኢራን) የመጣና ደቡብ መስጴጦምያን (ኢራቅን) የገዛ ብሔር ነበሩ።

ቋንቋቻው ካሥኛ የተጻፈ ቋንቋ እንደ ነበር አይመስልም፤ ስለርሱ ከስሞቻቸውና እጅግ ጥቂት ቃላት በስተቀር ዕውቀት የለንም። ከምናውቀው ትንሽ መጠን ግን ካሥኛ ከሌሎቹ ልሳናት ጋር ዝምድና እንደ ነበረው አይታስብም። የሴማዊ ቋንቋዎች ወይንም የሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቋንቋዎች ዘመድ አይመስልም።

ከባቢሎን ውድቀት (1507 ዓክልበ.) በፊት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በድሮ የአካድ ንጉሥ በናራም-ሲን ዘመን በተቀረጸ ዘገባ ዘንድ (2045 ዓክልበ.ግ.)፣ ካሣውያን ከተሸነፉት ጉታውያን ተባባሪዎች መካከል ተዘረዘሩ። ከዚህ በኋላ ግን ለ400 ዓመት ያህል ካሣውያን አልተጠቀሱም።

ከዚያ ካሣውያን መጀመርያ የሚጠቀሱ በባቢሎን ንጉሥ ሳምሱ-ኢሉና ፱ኛው ዓመት ስም «ሳምሱ-ኢሉና የካሣውያን ሥራዊት ያሸነፈበት ዓመት» ወይም 1654 ዓክልበ. ሊታይ ይችላል። እንዲሁም ተከታዩ አቢ-ኤሹሕ ምናልባት 1621 ዓክልበ. ግድም ካሣውያንን እንዳሸነፈ ዘግቧል።

በጥንታዊ ነገሥታት ዝርዝሮች በኩል የካሣዋያን ነገሥታት በንጉሥ «ጋንዳሽ» ጀመሩ። እንዲሁም በኒፑር በተገኘ በአንዱ ተማሪ ጽሑፍ ዘንድ (700 ዓክልበ ግ.)፣ «ጋዳሽ» ከ«ባባላም» ጥፋት በኋላ «የአለም አራት ሩቦች፣ የሱመርአካድና ባቢሎን ንጉሥ» ሆነ። ይህ ግን ከብዙ ዘመን በኋላ በመጻፉ እንደ ትክክል መረጃ አይቆጠረም። ብዙ መምህሮች አሁን እንደሚያስቡት፣ ከጋንዳሽ እስከ 2 አጉም ድረስ የተዘረዘሩት ነገሥታት ከባቢሎን ውድቀት በፊት በዛግሮስ ተራሮች የገዙት ነበሩ።

እነዚህም ቅድመኞቹ ካሣዊ ነገስታት ስሞች ከተለያዩ ጥንታዊ ዝርዝሮች ታውቀዋል። ዝምድናዎቹም ከአጉም-ካክሪሜ ጽላት ጽሑፍ ተገኝተዋል፦

  • ጋንዳሽ «26 ዓመት»
  • ታላቁ 1 አጉም «22 ዓመት»
  • 1 ካሽቲሊያሹ «22 ዓመት» «የታላቁ አጉም ልጅ»
  • አቢ-ራታሽ «የካሽቲሊያሽ ልጅ»
  • 2 ካሽቲሊያሹ ?
  • ኡዚጉሩማሽ «የአቢ-ራታሽ ልጅ ልጅ»
  • ሓርባ-<...>
  • <...>ኢፕ<...>
  • <...> (2 አጉም ካክሪሜ? «የኡሺጉሩማሽ ልጅ»)

ከዚህ በተረፈ ከአጉም ካክሪሜ በፊት ስለ ነበሩት ስሞች ሌላ መረጃ አልተገኘም። ጋንዳሽ የ«ባባላም» ወይም ባቢሎን ገዢ ሳይሆን ፣ ምናልባት ከሳምሱ-ኢሉማ ጋር በ1654 ዓክልበ. ገደማ የታገለው አለቃ ይሆናል የሚል አስተሳሰብ አሁን ዘመናዊ ነው፣ ማስረጃ ግን ገና አልተገኘም። እንደገና «ካሽቲሊያሽ» የተባለ ንጉሥ በኻና አገር (ተርቃ) ዝርዝር ላይ ስላለ (1621-1599 ዓክልበ.ግ.) ምናልባት ካሣውያን ለጊዜው በዚያ ኤፍራጥስ ወንዝ አገር ላይ መቀመጫ እንዳገኙ ታስቧል።

በአጉም-ካክሪሜ ጽሑፍ ማዕረጉ «የካሣውያንና የአካዳውያን ንጉሥ፣ የባቢሎኒያ ንጉሥ፣ ቱፕልያሽን (ኤሽኑናን) የሰፈረው፣ የአልማንና የፓዳን ንጉሥ፣ እና የጉታውያን ሞኞች ንጉሥ» ይሰጣል። ከባቢሎን ውድቀት ቀጥሎ መጀመርያው እዚያ የነገሠው ይታስባል። ሌሎች ወደ ስሜን የተዘረዘሩት ብሔሮች - ኤሽኑና፣ አልማን፣ ፓዳን፣ ጉታውያን - ከዚያ በፊት በካሣውያን ገዥነት ሥር እንደ ሆኑ ይቻላል። የ«አልማን»ና «ፓዳን» መታወቂያዎች እርግጠኛ አይደሉም፤ አንዳንድ መምህሮች የዛግሮስ ብሔሮች ይሆናሉ ሲሉ፣ ሆኖም የፓዳን-አራም አገር (ካራን አካባቢ) ያሳስባሉ። በዚያ ወቅት ያኽል ግን ቋንቋቸው ከሕንዳዊ-ኢራናዊ ቅርንጫፍ የነበራቸው የሚታኒ መሳፍንት ግዛታቸውን በሑራውያን ላይ ስለ መሠረቱ፣ ካሣውያን ለረጅም በስሜን መስጴጦምያ እንደ ነገሡ አይቻልም።

ከባቢሎን ውድቀት (1507 ዓክልበ.) በኋላ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ1507 ዓክልበ. (ኡልትራ አጭር) የኬጥያውያን መንግሥት ንጉሥ 1 ሙርሲሊሐቲ አገር (አናቶሊያ እስከ ባቢሎን ድረስ ዘምቶ የባቢሎኒያ አሞራዊ መንግሥት አስጨረሰና የባቢሎን ዋና ጣዖት የማርዱክን ሐውልት ዘርፎ ወደ ሐቱሳሽ ተመለሰ። ከዚህ ማጥፋት በኋላ በመዝገቦች ጉድለት «የጨለመ ዘመን» ሊባል ይችላል። ከላይ የተጠቀሰው «አጉም-ካክሪሜ ጽላት» እንዳለ ከጊዜ በኋላ ካሣዊው ንጉሥ አጉም ካክሪሜ የማርዱክን ሐውልት ከ«ኻና አገር» አስመለሰው። «የማርዱክ ትንቢት» የተባለው ድርሰት ደግሞ ሐውልቱ በሐቲ አገር የቆየው ዘመን 24 አመት ነበር ሲል፣ ይህ ግን ከ1000 አመታት ያህል በኋላ በመጻፉ አጠያያቂ ይባላል።

የአጉም ልጅ ቡርና-ቡርያሽ 1480 ዓክልበ. ግድም ከአሦር ንጉሥ 3 ፑዙር-አሹር ጋር የደንበር ውል ተዋወለ። ከባቢሎን ደቡብ በድሮው ሱመር የተገኘው ግዛት «የባሕር ምድር» እንዲሁም ለካሣውያንና ለቡርና-ቡርያሽ ልጅ ኡላም-ቡርያሽ በ1463 ዓክልበ. ያህል ወደቀ። ከዚህም ዘመን ጀምሮ አሦር በስሜንና ካሣዊ ባቢሎን በደቡብ የመስጴጦምያ ዋና ኃያላት ሆኑ።