Jump to content

1 ሙርሲሊ

ከውክፔዲያ

1 ሙርሲሊ (ሙርሺሊሽ) ምናልባት 1536-1507 ዓክልበ. አካባቢ ከአያቱ 1 ሐቱሺሊ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ ነበር።

1 ሐቱሺሊ አዋጅ ሐቱሺሊ የሴት ልጁ ሐሽታያራ ልጅ ሙርሲሊን ወራሹን ያደርገዋል። የሙርሲሊ ንግሥት ካሊ ተባለች።

በኋላ ንጉሡ ቴሌፒኑ በጻፈው የቴሌፒኑ ዐዋጅ በተባለው ሰነድ የሙርሲሊ ዘመን እንዲህ ይተረካል፦

«ሙርሲሊ በሐቱሻ (ሐትሳሽ) ንጉሥ በሆነበት ጊዜ፣ ልጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ አማቶችሁ፣ ዘመዶቹና ጭፍሮቹ ደግሞ ተባበሩ። በኃይል ጠላት አገራት ተገዥ አደረጋቸው። አገሮቹን ወርሮ የባሕር ጠረፎች አደረጋቸው።
ወደ ሐልፓ ሔዶ አጠፋው፣ የሐልፓንም ምርከኞችና ምርቶች ወደ ሐቱሻ አመጣ። በኋላ ወደ ባቢሎን ሔዶ ባቢሎንን አጠፋ፣ ሑርያውያንንም ድል አደረጋቸው፣ የባቢሎንም ምርከኞችና ምርቶች በሐቱሻ ጠበቀ።»

እንዲሁም በባቢሎን ዜና መዋዕል «በሳምሱ-ዲታና ዘመን፣ ኬጥያውያን ወደ አካድ መጡ» ይላል።

ከሥነ ቅርስ ሙርሲሊ ኪዙዋትናን (የበኋላ ኪልቅያ) እንዳሸነፈ ይታወቃል። የሐለብ (የያምኻድ መንግሥት መቀመጫ) እና የባቢሎን ዘመቻዎችን ያብራሩት ቅርሶች አሉ። በአንዱ ጽላት ዘንድ ሙርሲሊ በያምኻድ ላይ የአባቱን ደም ቂም ማብቀል ነበረበት። የባቢሎን ጥፋት የባቢሎኒያ መንግሥት ውድቀት ነበር። ከዚያ (1507 ዓክልበ.) ካሣውያን የተባሉት ሴማዊ ያልሆነ ብሔር ባቢሎኒያን ወረሩ። የባቢሎን ስም ወደ «ካራንዱኒያሽ» ቀየሩት፤ እዚያ የጨለማ ዘመን ሆነ።

ሙርሲሊ ግን የባቢሎን ምርኮና የባቢሎን ጣዖት (ሕውልት ወይም ምስል) ዘርፎ ወደ ሐቱሳሽ ተመለሰ፣ በዚያውም ዓመት ሙርሲሊ በሤራ ተገደለ። የሤራው መሪ 1 ሐንቲሊ አዲስ ንጉሥ ሆነ፤ እሱም ንጉሣዊ «ዋንጫ ተሸካሚ» ሆኖ ነበር፣ እንዲሁም የሐንቲሊ ሚስት የሙርሲሊ እኅት ሐራፕሺሊ ነበረች።

ቀዳሚው
1 ሐቱሺሊ
ሐቲ ንጉሥ
1536-1507 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
1 ሐንቲሊ