1 ቱትሞስ

ከውክፔዲያ

==

ቱትሞስ ዓኸፐርካሬ
የ፩ ቱትሞስ ምስል
የ፩ ቱትሞስ ምስል
የግብጽ ፈርዖን
ግዛት 1513-1501 ዓክልበ.
ቀዳሚ 1 አመንሆተፕ
ተከታይ 2 ቱትሞስ
ባለቤት ንግሥት አሕሞስሙትኖፍረት
ሥርወ-መንግሥት 18ኛው ሥርወ መንግሥት
አባት ?

==


፩ ቱትሞስ ዓኸፐርካሬ (ግብጽኛ፦ /ጀሁቲመስ/) በጥንታዊ ግብጽግብጽ አዲስ መንግሥትና የ18ኛው ሥርወ መንግሥት ፈርዖን ሲሆን ምናልባት 1513-1501 ዓክልበ. የገዛ ነበረ።

ቱትሞስ የቀዳሚው የ1 አመንሆተፕ አልጋ ወራሽ ተደርጎ ነበር፣ ዝምድናው ግን በእርግጡ አይታወቅም። የቱትሞስ እናት ስም ሰንሰነብ እንደ ነበር ይታወቃል። በቀዳሚው በአመንሆተፕ ዘመን ፱ኛው አመት የሥነ ፈለክ ሊቃውንት የውሻ ኮከብ (ሲሪዩስ) የተነሣበት ቀን ስለ ዘገቡ፣ የቱትሞስ ዘመን በ1513 ዓክልበ. ያህል እንደ ጀመረ ሊታወቅ ይቻላል።

የጦር አለቆቹ አሕሞስ ወልደ አባና እና አሕሞስ ፐን-ነኽበት ሁለቱ በመቃብር ጽሑፎቻቸው ውስጥ በኩሽ መንግሥትና በ «ናሓሪን» (ምሥራቅ ሶርያ) ላይ በዓኸፐርካሬ ዘመን እንደ ዘመቱ ዘግበዋል። በናሓሪን አገር ግብጻውያን ሠረገሎች፣ ፈረሶችና ባርዮችን ማረኩ። የመርከብ ኃይል አለቃ አሕሞስ ወልደ አባና እንደ ገለጸው፣ ፈርዖኑ መጀመርያ በረጨኑ (ምዕራቡ ሶርያ) ደርሶ ከዚያ በናሓሪን ዘመተ። ወደ ደቡብ በከነዓን/እስራኤል የሚቃወሙት ሕዝብ ባይጠቀሱም፣ ግብጻውያን በመርከብ በሶርያ እንደ ደረሱ ይቻላል። በኋላም የ3 ቱትሞስ ጽላት እንዳለ፣ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ በ1 ቱትሞስ ድሮ ጽላት አጠገብ ሌላ ጽላት አቆመ። «ናሓሪን» ማለት ከኤፍራጥስ ማዶ ወይም አራም-ናሓራይን ሲሆን ከትንሽ በኋላ ይህ የአዲሱ ሚታኒ መንግሥት መጠሪያ ሆነ፤ ኗሪዎቹም ያንጊዜ ሑራውያን ተባሉ። እንዲሁም የውሃ ሰዓት ፈልሳፊውና የከዋክብት መርማሪው አመነምኸት በጻፈው መግለጫ የ«መተኒ» (ሚታኒ) ዘመቻ ሲጠቅስ፣ ማለቱ ይኸኛው የ1 ቱትሞስ እንደ ነበር ይታመናል።

የሶርያ ዘመቻ በ፪ኛው ዓመት (1512 ዓክልበ. ገደማ)፣ የኩሽ ዘመቻ በ፩ኛውና ፫ኛው ዓመቶቹ (1513 እና 1511 ዓክልበ.) እንደ ተከሠቱ ይታመናል። በኩሽ ኖቢያ ጠረፉን ከ፪ኛው የአባይ ሙላት (ቡሄን አምባ) ወደ ደቡብ ከ፬ አባይ ሙላት ደቡብ እስካለው ድረስ አስፋፋው።

የዘመኑም ፰ኛውና ፱ኛው ዓመቶች የሚጠቀሱ ቅርሶች ስለ ተገኙ፣ የማኔቶን መረጃ 12 ዓመት 9 ወር እንደ ቆየ ሆኖ ይህ እንደ ትክክል ያህል ተቀብሏል።

ተከታዩ 2 ቱትሞስ ልጁ በንግሥቱ ሙትኖፍረት ነበር። በሌላ ንግሥቱ ንግሥት አሕሞስ ደግሞ ሴት ልጁን ሃትሸፕሱት ወለደ፤ እርሷም የ2 ቱትሞስ ንግሥትና ወደፊትም በራሷ መብት የግብጽ ንግሥት ሆነች።

ቀዳሚው
1 አመንሆተፕ
ግብፅ ፈርዖን
1513-1501 ዓክልበ.
ተከታይ
2 ቱትሞስ