ኬጥያውያን (መጽሐፍ ቅዱስ)

ከውክፔዲያ

ኬጥያውያን (ኬጢያውያን) ወይም «የኬጢ ልጆች» በመጽሐፍ ቅዱስከነዓን ከተገኙ ብሔሮች አንዱ ነበሩ።

አብርሃም ዘመን ኬጢያዊው ኤፍሮን የመቃብር ዋሻ በኬብሮን ለአብርሃም ሸጠ። ኤሳውም ከኬጢያውያን ሚስቶች እንዳገባ ይለናል። በመጽሐፈ ኢያሱ 1:4 «ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል» ሲለን፥ ይህ የኬጥያውያን አገር በከነዓን ስሜን ዳርቻ ከሊባኖስና ከኤፍራጥስ መካከል እንደተገኘ ከዚያም ወደ ምዕራቡ እንደ ዘረጋ ይመስላል።

መጽሐፈ መሳፍንት 1:26 ዘንድ እስራኤላውያን ቤቴልን በያዙበት ወቅት አንድ ሰው እንዲያመልጥ ፈቀዱ፣ እሱም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ «ሎዛ» የተባለ ከተማ ሠራ። በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ደግሞ ኬጢያውያን ከሃይለኛ ጎረቤቶች መካከል ከሶርያ ጋር ይጠቀሳሉ።

ከ1900 አ.ም. አካባቢ የሥነ ቅርስ ሊቃውንት በአናቶሊያ የተመሠረተ መንግሥት «ሐቲ» በተባለ አገር መኖሩን አወቁ። የሐቲ ሕዝብና የኬጢ ሕዝብ (ዕብራይስጥ «ሔቲ») አንድላይ እንደ ነበሩ ስለ ታሰበ የኬጢያውያን መንግሥት (እንግሊዝኛ Hittite /ሂታይት/) እስካሁን ይባላል። ቋንቋቸውም ኬጥኛ የሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ አባል መሆኑ ታውቋል። ተናጋሪዎቹ በመጀመርያ ከካነሽ ስለ ተነሡ ቋንቋቸውን «ነሺሊ» ይሉት ነበር። ከነሱ አስቀድሞ በሐቱሳስ ይኖር የነበሩት የሐቲ ሰዎች አሁን «ሐታውያን» ይባላሉ፤ ቋንቋቸውም ሐትኛ ወይም «ሐቲሊ» ሕንዳዊ-አውሮፓዊ ሳይሆን ሌላ ያልታወቀ አይነት ይመስላል።

ከኬጢያውያን መንግሥት ውድቀት (1170 ዓክልበ. ግድም) በኋላ፣ የኬጢያውያን ወይም «ሐቲ ሰዎች» ቅሬታ አንዳንድ ከተማ አገር በሶርያ ዙሪያ ያቆሙ ነበር። ስለዚህ በንጉሥ ሠሎሞን ዘመን የተጠቀሱት ኬጢያውያን እንደ ነበሩ ይመስላል። ነገር ግን አንዳንድ መምህሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ኬጢያውያን ከ«ኬጢያውያን መንግሥት»ም ሆነ ከሐታውያን ጋራ ምንም ግንኙነት የላቸውም ብለው ክርክር አቅርበዋል።