Jump to content

ጎቶንያል

ከውክፔዲያ
ጎቶንያል፣ 1549 ዓም እንደ ተሳለ

ጎቶንያል (ዕብራይስጥ፦ עָתְנִיאֵל /ዖትኒየል/፣ ግሪክኛ፦ Γοθονιήλ /ጎጦኒዬል/) በመጽሐፈ መሳፍንት 3:9-11 መሠረት የእስራኤል ፈራጅ ነበር።

መጽሐፉ እንደሚተርከው ዕብራውያን ለስምንት አመት ለመስጴጦምያ (አራም-ናሓራይም) ንጉሥ ኲሰርሰቴም ከተገዙለት በኋላ፣ ለእግዜር ስለ ጮኹ እርሱ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልን እንደ መሪ አስነሣላቸው። ጎቶንያልም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እስራኤላውያን ንጉሥ ኲሰርሰቴምን ድል ለማድረግ ቻሉና ጎቶንያል ከዚያ ለአርባ ዓመት በሰላም መራቸው። ይህ ዘመን ምናልባት ከ1497 እስከ 1457 ዓ.ክ.ል.በ. ያሕል ሊሆን ይችላል።

ከጎቶንያል አርባ ዓመታት በኋላ፣ የእስራኤል ልጆች እንደገና ክፉ ስለ ሠሩ፣ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ኤግሎም ከነሞዓባውያን፣ አሞንአማሌቅ ጋራ አበረታባቸው፣ ለርሱም ለ18 ዓመታት አገለገሉ። እነዚህም ከሴም የተወለዱ አረመኔ ብሔሮች ነበሩ።

ስለ ጎቶንያል ቤተሠብ ያለን መረጃ በመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 15:15-17 እና እንደገና በመሳፍንት 1:11-13 ይጠቀሳል። በዚያ ታሪክ ኢያሱ ፈራጅ እየሆነ የጎቶንያል አጐት ካሌብ የሴት ልጁን የዓክሳ እጅ ቅርያትሤፍርን ከከነዓናውያን ለሚይዘው ጎበዝ ሚስት እንዲሰጣት የሚል ቃል ገባ። ይህን ያደረገው ጎበዝ ጎቶንያል ስለ ሆነ የአጐቱን ልጅ ዓክሳን አገባት ይላል። የቅርያትሤፍር ስም በኋላ ዳቤር እንደ ሆነ ይላል።

ኬብሮን አካባቢ የተገኙት ኗሪዎች እንደ ረዥም ዘመን ልማዳቸው የጎቶንያል መቃብር በአንድ የኬብሮን ዋሻ ውስጥ ይገኛል።