Jump to content

አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ

ከውክፔዲያ
ቅዱስ አቡነ አረጋዊ
ደብረ ዳሞን በዘንዶ ላይ ሆነው እደወጡ
ታላቅ የክርስትና ሃይማኖት አባት
የተወለዱት በአራት መቶዎቹ አጋማሽ አካባቢ
የትውልድ ሀገር ሮም
የአባት ስም ንጉሥ ይስሐቅ
የእናት ስም ቅድስት እድና
በዓለ ንግሥ ጥቅምት ፲፬ ቀን
የሚከበሩት በመላው የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥንክሳር
የተሰወሩት ጥቅምት ፲፬ ቀን በኢትዮጵያ


(ዝክረ ቅዱሳን) አቡነ አረጋዊ በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው "ንጉሥ ይስሐቅ" እና "ቅድስት እድና" ይባላሉ ።

የተወለዱበት አካባቢም ሮም ነው ። ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ። በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል። "የት ልሒድ?" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከስምንቱ ጋር ከቃልኬዶን ጉባዔ በኋላ በ፬፻፶፩ ዓም ወደ ኢትዮጵያ መጡ ። ከዘጠኙ ቅዳሳን ወደ ኢትዮጵያ ከሮምና ከመካከለኛው ምሥራቅ ከፈለሱት አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው ።

አቡነ አረጋዊ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ የተገኘ በ፲፯ኛው ክፍለ ዘመን የተሳለ የቅዱሳኑ ምስል

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሃገራችን የመጡ በአራት መቶ ሰባዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጽሐፍትን እየተረጎሙ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል ። አቡነ አረጋዊ ለብዙ ጊዜ በዓት ፍለጋ ደክመዋል ። በመጨረሻም ደብረ ዳሞ ማርካቸዋለች ።

አቡነ አረጋዊ የመሠረቱዋት ደብረ ዳሞ

የሚታወቁበት ተአምራቸው

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እያስተማሩና እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ሲደርሱ ወደ ሰማይ ቀጥ ያለች ተራራ ሰው በምንም መንገድ ሊደርስባት ወይም ሊወጣባት የማይቻለውን ቦታ እሳቸው ተመኙዋት ። ከዚያም "አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ" እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር ፺፣፺፩:፲፩ - ፲፮ ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና ፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል ። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል ፡፡ ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል ፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል ፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም ፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላች ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላ ግን ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል ፡፡

ባጭሩ ከተጋድሎዋቸው

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ምናኔ ወይም የምንኩስናን ኑሮ ሥነስርዓት በማስፋፋታቸውና በማስተማራቸው "አቡሆሙ ለመነኩሳት ዘኢትዮጵያ - የኢትዮጵያ መነኩሳት አባት" ይባላሉ ። ወንጌልን በማስተማር ፣ መጸሐፍትን ወደ ግዕዝ በመተርጎም ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል ፣ ማለት ግዕዝ አጥንተው ጠንቅቀው ያውቃሉ ማለት ነው ። ከሚወዱት ወንድማቸው ጋር ለብዙ ዓመታት በመለያየታቸው የተጻጻፉት ደብዳቤም ተሰባስቦ ፣ መንፈሳዊ ትምህርት (ዕውቀት) ያዘለና ነፍስ ፈዋሽ ገድላቸው ሆንዋል ። ዓፄ ገብረመስቀልና ቅዱስ ያሬድም ወዳጆቻቸው ነበሩ ። በደብረ ዳሞም ተራራ ግርጌ የኪዳነምሕረትን ቤተክርስቲያን ለሴቶች ገዳም አድርገው ሰተዋል ። ቀዳሚዋ መኖክሴም የሆኑት እናታቸውቅድስት እድና ናቸው።

በመጨረሻ ሕይታቸው

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ለሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት (የገዳም አባት ወይም አለቃ) ሾመውላቸው ጥቅምት አሥራ አራት ቀን በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ እንደሄኖክ እንደ ኤልያስ ተሰውሯል ፡፡

ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ
የዚሁ መደብ ዋና መጣጥፍ ኢትዮጵያ ነው።
በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ Ethiopia የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።
በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ Christianity የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።