አባል:Eliasab/sandbox/ዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን

ከውክፔዲያ

ስለ ዋሻ ሚካኤል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዋሻ ሚካኤል (Washa Mikael, English) ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ በኩል የካ ከፍለ ከተማ ውስጥ ያለ ጥንታዊ እና በከፊል ወጥ ከሆነ ዓለት ተፈልፍሎ የተሰራ ቤተ-ክርስቲያን ነው:: አዲስ አበባ ከሚገኘው የእንግሊዝ ኢምባሲ በስተጀርባ ቲንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው ከፍታማ ቦታ ላይ ይገኛል:: ምንም እንኳ የአካባቢው ቄሶች በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ ቢናገሩም በአብዛኛው ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው ግን በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ ነው::

ታሪካዊ ዳራ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የአክሱም መንግስትና የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን:- አብርሃና አጽብሃ የአክሱም መንግስትን በጋራ ይገዙ እንደነበር የተለያዩ መጽሃፍት ይገልፃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጽሁፍም ይሄንን በተለያዩ መረጃዎች ይጠቅሳል፡፡ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ እንደተፃፈ በሚነገረው የድንጋይ ላይ ፅሁፍ አብርሃና አፅብሃ የሚያስተዳድሩት አገር ግዛት ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ዝርዝር እንደምንረዳው ግዛታቸው ሳባን /የመንን/፣ ኑባ /ሱዳንን/ እና ቤጃ /ደቡብ ግብጽ/ ድረስ ይደርሳሉ፡፡ ይህም እጅግ ሰፊ ግዛት እንዳላቸው ያስረዳል፡፡ ከየካ ሚካኤል የተገኘው /ያልታተመ/ መረጃ ይህንን ሀሳብ እንደሚከተለው ያጠናክራል::

“በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ወሰን በጣም ሰፊ ስለነበር ሁሉቱ ወንድማማቾች አክሱም ላይ ሆነው ሕዝባቸውን በቅርብ ለማስተዳደር ስለተቸገሩ እጣ ተጣጥለው ንጉስ አብርሃ አክሱም ላይ በመሆን ሰሜን ኢትዮጵያን፣ ንጉስ አጽብሃ ደግሞ ደቡብ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ሸዋ ውስጥ የረር ተራራ ላይ ቤተ መንግሥቱን ሰራ፡፡ በወቅቱ ቤተመንግሥቱን ለመሥራት ሲመጣ ማዕቀበ እግዚእ በሚባል ካህን ታቦት ሚካኤልን አሸክሞ አስመጥቶ ነበር፡፡ ይህንን አሸክሞ ያስመጣውን ታቦት ከየረር ተራራ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ባስፈለፈለው ዋሻ ውስጥ እንዳስገባው ይገልፃል፡፡”

በትግራይ ክልል በአብርሃና አፅብሃ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ከጅማ የአፅብሃ ሬሳ የመጣበት ነው የሚባለው የጠፍር አልጋ ይገኛል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ደቡብ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው አፅብሃ እስከ ጅማ መድረሱን ነው፡፡ ውቅር ቢተክርስቲያን መስራት ለአጽብሃ አዲስ አይደለም፡፡ በትግራይ ከውቁሮ ከተማ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ገረአልታ ውስጥ ገማድ በተባለ ስፍራ አብርሃና አጽብሃ ያሰሩት ነው የሚባል አብርሃ አጽብሃ በመባል የሚታወቅ ውቅር ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያኑ ገዳም ነው፡፡

ከየካ ሚካኤል የተገኘው /ያልታተመ/ መረጃ እንደሚገልፀው በትግራይ ውቅሮ አካባቢ የሚገኘው የአብርሃና አፅብሃ ውቅር ቤተክርስቲያን ከዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው በመግለጽ ታሪኩን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡-

“ከንጉስ አጽብሃ ጋር የመጣው ታቦት የገባበት ዋሻ የተፈጥሮ ዋሻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ እንደሚገኙት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍለው ከታነፁት ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ዓይነት በኢትዮጵያ ፊደል “ሀ” ቅርጽ የታነፁ ሲሆን በቤተክርስቲያን የፊደል ትርጉም “ሀ” ማለት “ህልዎቱ ለአብ እምቅድም ይትፈጠር ዓለም” ወይም “የአብ መኖር ከአለም አስቀድሞ ነው” ማለት ነው የሚለውን አባባል ለማስረዳት ተብሎ የታነፀ ነው ይላል፡፡” በሌላ በኩል አንዳንድ የታሪክ ተመራማሪዎች የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን በደቡብ ሸዋ ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ በአለምገና ቡታጅራ መንገድ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 66 ኪሎ ሜትር አካባቢ ከምትገኘው አዳዲ ማሪያም ውቅር አብያተ ክርስቲያን ጋር በመመሣሠሉና ይህ ደግሞ በንጉስ ላሊበላ ዘመን እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዚያ ዘመን የተሰራ ነው ይላሉ፡፡

በአዳዲ ማሪያም የሚገኘው የታሪክ ማስታወሻ ንጉስ ላሊበላ የአዳዲ ማሪያምን ከቋጥኝ ድንጋይ እንደፈለፈለውና ሥራውን ሲጨርስ በራዕይ ተመርቶ ወደ ላሊበላ እንደተመለሰና እዚያ ሲደረሰ እንደሞተ ይተርካል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሶስት ወሩ በሚያሳትመውና ሰላምታ ተብሎ በሚጠራው ቋሚ የበረራ መፅሄት ዊሊያም ዴቪድሰን የተባሉ የታሪክ ተመራማሪ የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስትያን የ700 ዓመት እድሜ እንዳለውና አሰራሩም ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሰራር ጋር እንደሚመሳሰል ይገልፃሉ፡፡

በየትኛው ዘመን እንደተሰራ ለማወቅ የአርኪዎሎጂ ጥናት መደረግ ስላለበት የነሱን የወደፊት የጥናት ውጤት መጠበቁ ወሳኝ ቢሆንም ከየካ ደብረሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ያገኘነው ያልታተመ ፅሁፍ የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስትኑ ከላሊበላ ጋር በማመሳሰል ማቅረብ የኢትዮጵያን ሀይማኖት ጥንታዊነት በሚፃረሩ ሀይሎች የሚወራ ነው በማለት ይቃወማሉ፡፡

አብርሃና አፅብሃ ከአባታቸው ታዜር ከእናታቸው ሶፍያ (አይዋል) ታህሳስ 19ቀን 312 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ አባ ሰላማ (አባ ከሣቴ ብርሃን) በ28ኛ ዓመታቸው አጠመቁዋቸው፡፡ አብርሃና አጽብሃ ከአባ ሰላማ ጋር በመሆን ክርስትናን በግዛታቸው አስፋፍተዋል፡፡ በዘመናቸው 6ዐ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሳነፁና ከዚህም ውስጥ 44 ቤተክርስቲያናት ፍልፍል ቤተክርስቲያናት ናቸው፡፡ በስማቸው ቤተክርስቲያን ታንፃል፡፡ በየወሩ በ4ኛው ቀንና በየዓመቱ ጥቅምት 4 በአክሱም ፅዮንና መርጦ ለማርያም ቤተክርስትያናት በዓላቸው ይከበራል፡፡

እንደ ነገሥታቱ ገድል በ32ዐዎቹ ንጉስ አጽብሃ በየረር ተራራ ላይ የገነባው ቤተ መንግሥትና ከቤተመንግሥቱ በስተ ሰሜን አቅጣጫ የተገነባው ውቅር ቤተክርስቲያን በአባ ከሣቴ ብርሃን የመጀመሪያው ጳጳስ ተባርኮ ተመረቀ፡፡28

አብርሃና አጽብሃ የጀመሩትን ክርስትናን የማስፋፋት ሥራ በተከታዮችም ነገሥታት የቀጠለ ሲሆን በ6ተኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ካሌብና በአፄ ገ/መስቀል የንግስና ዘመን በበለጠ ተስፋፍቷል፡፡ በ6ተኛው ክ/ዘመን በተለይ ዘጠኙ ቅድሳን ከመጡ በኋላ ክርስትናን የማሠራጨቱ ሥራ ይበልጥ ተስፋፍቷል፡፡

በአክሱም ዘመነ መንግስት ዮዲት ጉዲት የተባለች በአክሱም ግዛት ያሉትን አብያተ ክርስቲያናትና ቄሶችን ማጥፋት በጀመረች ጊዜ የአክሱም ፅዮንን ጨምሮ አንዳንድ ታቦታት ወደተለያዩ ቦታዎች ተሰደዋል፡፡ ምናልባት እነዚህ የፀረ ክርስትና ሰዎች አጽብሃ ወዳሰራው ውቅር ቤተክርስቲያን ቢመጡም ታቦቱን የእምነቱ ተከታዮች እስከ 1838 ዓ.ም ድረስ ይዘው ሲሰደዱ እንደቆዩና በመጨረሻ ቡልጋ ውስጥ ከሚገኘው ኢቲሳ ተ/ሃይማኖት ገዳም የቅዱስ ሚካኤልን ጽላት እንዳመጡት ይነገራል፡፡

በየካ ደብረ ሣህል የሚገኘው የታሪክ ማስታወሻ የጽላቱን አመጣጥ ታሪክ እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡

“ንጉስ ሣህለ ሥላሴ (1805 - 1840 ዓ.ም) በነገሱ በ32ኛው ዓመት አባ ተስፋ ሚካኤል የተፀውኦ ስማቸው አባ ኦፎንቻ የሚባሉ መነኩሴ የቅዱስ ሚካኤልን ጽላት ቡልጋ ከሚገኘው ኢቲሳ ተ/ሃይማኖት ገዳም አምጥተው ግንቦት 13/1838 አስገቡት::”

ንጉስ ሣህለ ሥላሴ የሸዋ ንጉሥ ሆነው የገዙት ከ1805-1840 ዓ.ም ሲሆን በዚህ ዘመን በሸዋ ግዛታቸው ውስጥ እየተዘዋወሩ አንድነትና ሃይማኖትን በማስተማር ባላቸው ፅኑ ዓላማ ሠራዊታቸውን አስከትለው በ1826 ዓ.ም አካባቢ ከኢቲሳ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንደሄዱና የቀራኒዮ መ/ዓለም ቤተክርስቲያን ደብርን በ1826 ዓ.ም ተከሉ፡፡

በእሳቸው ዘመን ግንቦት 12 ቀን 1838 ዓ.ም በስደት ከቆየበት ኢቲሳ የቅዱስ ሚካኤል ጽላት መጥቶ ገባ፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ጽላት ከተመለሰ በኋላ ለአካባቢው ሰውና ለንጉሥ ሣህለሥላሴ ሠራዊት አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡

አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ሆነው ሲነግሱ ከተማቸው አንኮበር ነበረች፡፡ አባታቸው የጀመሩትን ወደ ደቡብ አቅጣጫ የመስፋፋትን መንገድ በመከተል እሳቸውም ወጨጫ ተራራ ላይ በድንኳን ካምፕ አድርገው ከነሠራዊታቸው ሰፈሩ፡፡ ወጨጫ ላይ በድንኳን ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ በ1886 ወደ እንጦጦ መጡና ከተማቸውን ከተሙ፡፡

ታዲያ ወጨጫም ሆነ እንጦጦ እያሉ የእንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን ከመተከሉ በፊት ወደ ዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተ ክርስቲያን እየተመላለሱ ያስቀድሱ ነበር ይባላል፡፡

በ1878 ውቅር ቤተክርስቲያኑ በአንድ በኩል በመደርመሱ አፄ ምኒልክ ካህናቱን፣ ጽላቱንና ቅርሶቹን ይጐዳብኛል በማለት ታቦቱን ከውቅር ቤተክርስቲያኑ ውስጥ አውጥተው እዚያው አካባቢ ባሰሩት መቃኞ ውስጥ አስገቡት፡፡ በመቃኞ ውስጥ እያሉ ለ7 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጽላት በ1895 አሁን የካ ሚካኤል ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ መቃኞ ተሰርቶለት ገባ፡፡ ውቅር ቤተክርስቲያኑ ግን ባለቤት የሌለውና ጠባቂ አጥቶ የከብቶች መዋያ በመሆን ሣርና ሙጃ በቅሎበት ይገኛል፡፡

ውቅር ቤተክርስትያኑን ለመጠገን የተደረጉ ጥረቶች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የዋሻ ውቅር ቤተክርስቲያን ታቦት በስደት የተለያዩ ቦታዎች ከዞረ በኃላ በመጨረሻ ከኢቲሳ በ1838 ዓ.ም. ወደ ነበረበት እንደተመለሰ ይነገራል፡፡ ታቦቱ ከተመለሰ በኃላ ውቅር ቤተክርስቲያኑ ለአካባቢው ህብረተሰብና ለንጉሳዊ ቤተሰቦች በተለይም ለንጉስ ሳህለ ስላሴና ለአጼ ምኒልክ የክርስትና አገለግሎት እየሰጠ ቢቆይም በ1878 ውቅር ቤተክርስትያኑ በከፊል በመደርመሱ አፄ ምኒልክ በታቦቱና በቄሶቹም ላይ አደጋ እንዳይደርስ ታቦቱን በማስወጣት በመቃኞ እንዲቆይ አደረጉት፡፡37

ዓፄ ምኒልክም በእቴጌ መነን አነሳሽነት ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ በመውረዳቸው በእንጦጦ ዙሪያ የሰፈረውም ሰራዊት እነሱን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ሰፈረ፡፡ የዋሻ ሚካኤል ታቦትም ባለበት በመቃኞ በመሆን ለአካባቢውና ለአዲስ አበባ ህዝብ አገልግሎት ቢሰጥም በተለይ በቁጥር በርካታ ለሆነው ለአዲስ አበባ ህዝብ በመራቁ ከ17 ዓመታት ቆይታ በኃላ አጼ ምኒልክ አሁን የካ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው ቦታ ከእንጨት ባሰሩት መቃኞ ውስጥ የካቲት 17/1895 ዓ.ም. አስገቡት፡፡

በመቀጠልም ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ከአባታቸው ሞት በኃላ በአቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ መሰረቱን አስጀምረው አሁን የሚታየው ቤተክርስቲያን ከ1920 -1923 ዓ.ም. ተሰርቶ በመጠናቀቁ የጥንታዊው የሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ፅላት ህዳር 12 1923 ወደ አዲሱ ህንፃ ገባ፡፡38

ከዚህ በኋላ ይህንን ውቅር ቤተክርስትያን እንደ ቅርስ ለማቆየት የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ከ1968-1980 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ተክለሀይማኖት የፈረሰውን ውቅር ቤተክርስቲያን ሲጎበኙ ባዩት ነገር በመደመም ከፍራሹ 50 ሜትር ርቀት ላይ የፃዲቁ አቡነ ተክለሀይማኖት ታቦት አስገብተው ደብሩን ደብረመንክራት ብለው ሰየሙት፡፡ በመቀጠልም በዋሻው ላይ ካቴድራል በማሰራት እንደ ደብረሊባኖስ ገዳም ሊያደርጉት ቢያስቡም ሀሳባቸው ከግብ ሳይደርስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡39 የዚህ ደብር መቋቋም በአንድ በኩል በዛ አካባቢ ላሉት ምዕመናን የክርስትና አገልግሎት ለመስጠት፤ በሌላ በኩል ከፊል አካሉ የፈረሰው የዋሻ ውቅር ቤተክርስትያን ጥበቃ እንዲያገኝ በማሰብ ይመስላል፡፡

ከዚህ ሙከራ በኃላ የውቅር ቤተክርስቲያኑን መጠገን፣ ማደስና እንደገና ለተለያዩ አገልግሎት መጠቀምን በሚመለከት የተነሳው በ1993 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ ዓ.ም. ሊቀ ትጉሃን መምሬ ከበደ ኃ/እየሱስ የዋሻ ደበረ መንክራት ተ/ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ስለ ፍራሽ የዋሻ ሕንፃን ጥገና በሚመለከት የሙያ ትብብር መጠየቃቸውንና በዚህም መሰረት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የታሪካዊ ቅርሶች እንክብካቤና ጥገና መምሪያ ለሊቀ ትጉሃን መምሬ ከበደ ኃ/እየሱስ የዋሻ ደበረ መንክራት ተ/ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳደሪ በመምሪያው የተዘጋጀውን የመጠለያ ዲዛይንና ዝርዝር ግምት በደብዳቤ ቁጥር 09/ቅጥ - 16/20 ሚያዝያ 4/1993 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ ሸኚነት መላኩን ገልጿል፡፡40

የየካ ደብረሳህል ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን ይህንን ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ የታሪካዊ ቅርሶች እንክብካቤና ጥገና የተላከውን መረጃ በማያያዝ ፓትሪያርኩ ጥገናው እንዲጀመር መመርያ እንዲሰጡን የሚል ደብዳቤ ለፓትሪያርኩ ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ቅርሱን ባለበት ሁኔታ ጠግኖ ለቱሪስት መስህብ ለማዋልና ለትውልድ ለማቆየት በርካታ መፃፃፎች ቢደረጉም እስካሁን አልተተገበረም፡፡ ለዚህ ዋና ምክንየቱ የገንዘብ ዕጥረትና የአመራር ቁርጠኝነት እንደሆነ ይነገራል፡፡

የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ገፅታ የሚያሳዩ ምስሎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ወጥ የሆነ የቤተክርስትያን አሰራር ህግ አለው፡፡ ቤተ ክርስትያኑ ሲገነባ ቅኔ ማህሌት፣ መቅደስና ቅድስት የተባሉ ክፍሎች በዋናነት ይኖሩታል፡፡

በዚህ በፈራረሰው የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተ ክርስትያን እነኚህ ክፍሎች ተለይተው እስካሁን ይታያሉ፡፡ ከነኚህ ሌላ የክርስትና ቤት /የጥምቀት ቤት/፣ እቃ ቤት፣ ሁለት በሮች፣ በግራና በቀኝ አምስት አምስት መስኮቶች በድምሩ አስር መስኮቶች፣ አሉት፡፡ ቤተክርስትያኑ ከነበሩት 12 አምዶች የአምስቱ አምዶች ቅርፅ ጎልተው ይታያሉ፡፡ በእነኚህ አምዶች ላይ የሀረግ ምስል ተቀርፆበታል፡፡ እነኚህ ክፍሎችና የአሰራር ጥበቡ በወቅቱ የነበረውን የውቅር ቤተክርስቲያኑን አሰራር ያመለክታሉ፡፡

ምስል1:- ወደ ዋሻ ውቅር ቤተክርስትያን የውስጥ ክፍል የሚያስገባው መግቢያ ከፊትለፊት በቅርበት ሲታይ

የዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን ፍራሽን ለቱሪስት መስህብነት መጠቀም[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራውና አሁን ግማሽ አካሉ የፈረሰው የዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቅሪት በቱሪዝም መስህብነት አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ቅርስ በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ነው የሚባል አገልግሎት ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

የዋሻ ሚካኤልን እንደ ቱሪስት መዳረሻ የበለጠ ለመጠቀም አንዳንድ ችግሮች ያሉበት ሲሆን ከችግሮቹም ውስጥ፡-

  • በኋላ ከተሰራውና ከተራራው ግርጌ ላይ የሚገኘው የካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ወደ ዋሻው ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ በእግር ብቻ የሚያስኬድ ሲሆን 45 ደቂቃ የሚፈጅ ወደ 3 ኪሎ ሜትር ያህል የሚሆን መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በተራራ ላይና ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ ለጉብኝት የሚመጡትን ቱሪስቶች በአካባቢው ባሉ ወጣቶች ችግር እየተፈጠረባቸው መሆኑ፣ ይህንን ሀሳብ በሰላምታ መፅሄት ላይ ፅሁፍ ያቀረቡት ዊሊያም ዳቪሰን ይጋሩታል፣
  • ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ባልታወቀ ምክንያት በ1878 የፈረሰ በመሆኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ያለምንም ጥገና በዚሁ ከቀጠለ ከዚህ የከፋ ችግር የሚደርስበት መሆኑ፣
  • በመገናኛ ወደ ኮተቤ ኮሌጅ ሲኬድ፣ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲደረስ፣ ወደ ግራ መታጠፊያ ላይ ወደ ዋሻ ሚካኤል ውቅር ቤተክርስቲያን የሚወስደውን መንገድ የሚያመለክት ታፔላ ወይም ሌላ መጠቆምያ አለመኖሩ፣
  • መገናኛን አልፎ ወደቤተክርስቲያኑ የሚወስደው መንገድ በመኪና ቦታው ድረስ የሚያደርስ መንገድ ሲኖረው 3ዐዐ ሜትር ያህል በአስፋልት የተሰራና ለመኪና አመቺ የሆነ መንገድ ሲኖረው የተቀረው በግምት ከ2.7 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ መንገድ ለመኪና በጣም አስቸጋሪና በዝናብ ወቅት በትራንስፖርት መሄድ ወደማይችልበት ሁኔታ መድረሱ፣
  • አካባቢው ትንሽ ወጣ ያለ በመሆኑና ከፍታ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የውኃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ መኖሩ፣
  • በአካባቢው ምንም ዓይነት የመፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ የጽዳት መጓደል መኖር፣
  • ይህንን የድንጋይ ፍልፍል ቤተክርስቲያን ለመጠበቅ የሚያስችል የተጠናከረ አጥር አለመኖሩ፣
  • በፍራሽ ቤተክርስቲያኑ ከብቶችና በጎች የሚውሉበት ከመሆኑም በላይ ውስጣዊ ክፍሎቹም ሆኑ ውጫዊ ክፍሉ በሳር በመሸፈኑ ለቱሪስት ሳቢ አለመሆኑ፣

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች መፍትሔ ካላገኙ የዚህ የፍልፍል ቤተክርስቲያን የቱሪስት መስህብ ሆኖ ያገለግላል ብሎ ማለት አያስደፍርም፡፡ በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለማቃለል ደረጃ በደረጃ የሚሠሩ ሥራዎችን በመተለምና በማስቀመጥ ችግሮቹን ከዋናው ቅርሱ አስተዳዳሪ ከየካ ደብረ ሳሕል ቅዱስ ሚካኤል፣ ከደብረ መንክራት አቡነ ተ/ሃይማኖትና ከቤዛዊት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አስተዳደር፤ ከየካ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ከየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹ የሚቃለሉበትን የመፍትሄ ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርቤአለሁኝ፡-

  • በቱሪስቶች ላይ በቡድን በመደራጀት መንገድ ላይ እየጠበቁም ሆነ መጐብኛ ቦታ ድረስ በመዝለቅ የቱሪስቶችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉትን ግለሰቦች በቱሪስቶች ላይ ከሚያደርሱት አደጋ ውጪ የሀገርን ገጽታ የሚያበላሽ ስራ እየሰሩ በመሆኑ ከክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት፣ ከፖሊስ ጽ/ቤት፣ ከደንብ አስከባሪና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን ወንጀለኞቹ ታድነው ትምህርት የሚያገኙበትና አልታረም ባሉት ላይ እርምጃ የሚወሰድበት መንገድ ቢፈለግ፡፡
  • ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚያወጣው መንገድ በበጋም ሆነ በክረምት ማስኬድ እንዲችል ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመሆን ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት መንገዱን እንዲስተካክል ቢደረግ፣
  • የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከክፍለከተማው የሀገርህን እወቅ ክበባትና የወጣቶች ሊግ ጋር በመተባበር የውቅር ቤተክርስቲያኑ ግቢና ውጪ ፅዳት ቢጠበቅና ሳርና ቅጠላ ቅጠል የሸፈናቸው አካባቢዎች ቢጠረጉ፣ የዝናብ መውጫ ቦዮች ቢቆፈሩለት፣
  • በኢፌድሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያዎች መስህቡን ጠግኖ ለቱሪስት መስህብና ለመጪው ትውልድ ለማቆየት እንዲቻል ያጠናው የጥገና ዲዛይን ጥናት ከደብሩ አስተዳደዳር፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ከክፍለ ከተማው ባህልና ቱሩዝም ቢሮ ጋር በመሆን ተግባራዊ ማድረግ፣
  • በተወሰነ ቁጥርም ቢሆን ወደ አካባቢው ለጉብኝት የሚሄዱት ቱሪስቶች መጠቀሚያ የሚውል የመፀዳጃና የውሃ አገልግሎት፣ የስጦታ እቃዎች መደብር፣ ሚኒ ካፌ ቢዘጋጅ፣
  • በአሁኑ ሰዓት አካባቢው በጥበቃ ሥር ያለ ቢሆንም የየካ ደብረ ሣህል ቤተክርስቲያን አስተዳደር ቅርሱን በተጠናከረ አጥር በማሳጠር ለቦታው የተሻለ እንክብካቤ ማድረግና ቋሚ ዘበኛ ቢቀጠርለት፣
  • ከላይ እንደተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያኑ አመሰራረትን አስመልክቶ ከተለያዩ ጽሁፎችና ግለሰቦች የተለያዩ አስተያየት የሚሰጥ ሲሆን ይህንን በተመለከተ የበለጠ ጥናት በማካሄድ ትክክለኛውን ታሪክ በማውጣትና ለአስጐብኚዎች በማስጨበጥ የተጠናና አንድ ዓይነት ታሪክ ማሳወቅ ስለሚገባ ጥልቅ ጥናት በማጥናት ለአስጐብኚዎች ስልጠና ቢሰጥ፣

ዋቢ መጽሃፍት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]