አንደማንቱኑም
አንደማንቱኑም ወይም አንደማቱኑም በሮሜ መንግሥት ዘመንና ከዚያ በፊት በኬልቶች መካከል የሊንጎናውያን ዋና ከተማ የአሁኑም ላንግረ ስያሜ ነበር። ይህ ስም በፔውቲንገር ሠንጠረዥና በሌሎች የጥንት መልካምድር ምንጮች ይጠቀሳል።
በኬልቶች ቋንቋ የስሙ ትርጉም «ከወንዛፍ በታች» (ከ«አንዴ-» በታችና «ማንቶ»- አፍ) እንደ መጣ ይመስላል። ሆኖም «-ማቱኑም» የሚል አጻጻፍ ትክክለኛ ቢሆን፣ ፪ኛው ሥር ምናልባት ማቱ («ጥሩ» ወይም «ድብ») ሊሆን ይችላል።
አካባቢው ወደ ሮሜ መንግሥት የተጨመረው በዩሊዩስ ቄሣር ዘመቻዎች ነበር። በሮሜ ንጉሥ አውግስጦስ ዘመን (35 ዓክልበ.-6 ዓ.ም.) ስሙ ከ«አንደማንቱኑም» ወደ «ሊንጎኔስ» (ከኗሪዎቹ ሊንጎናውያን ስያሜ የተነሣ) ተቀየረ። መጀመርያ ከተማው ለጋሊያ ሉግዱነንሲስ ክፍላገር ተያያዘ፤ ከዚያም ወደ ጋሊያ ቤልጊካ ክፍላገር ተጨመረ። በንጉሥ ዶሚቲያኑስ ዘመን ለጊዜ ወደ ጌርማኒያ ክፍላገር ተጨመረ፣ ከዚያም ወደ ሉግዱነንሲስ ተመለሰ።
የከተማው ኗሪዎች ቁጥር ምናልባት እስከ ፰ ሺህ ድረስ በዛ። በ፫ናው ክፍለ ዘመን ከደረሱት ሁከቶች የተነሣ ከተማ በግድግዳዎቹ ውስጥ ተሸሸገ። በሮማውያን ዘመን ከነበሩት ታላቅ ቤቶች ወይም መዋቅሮች አንዳንድ ለሥነ ቅርስ ታውቋል። በከተማው ዙሪያ የሸክላ፣ የድንጋይ እና የብረታብረት ሠሪዎች እንደ ተገኙ ይታወቃል። ከከተማው ውጭ ደግሞ አራት መቃብር ቦታዎች ወደየአቅጣጫው ተገኝተዋል።
ከተማው በዋና መንገዶች መሸጋገሪያ ላይ በመቀመጡ አይነተኛ ሚና ይጫወት ነበር። ከልዮን ወደ ትሬቭ የሚወስደው የአግሪፓ መንገድ በአንደማንቱኑም በኩል ሲያልፍ፣ በተጨማሪ ወደ ደቡብ ወደ በሳንሶንና ወደ ስሜን ወደ መትዝ የሚሄድ መንገድ ነበር። ሌላ መንገድ ደግሞ ወደ ስሜን-ምዕራብ ወደ ሬም ሄደ።
ታኪቱስ እንደሚጽፈ፣ በጨካኙ ንጉሥ ኔሮን ዘመን አንዳንድ ሰዎች በአመጽ ሲነሡ ሊንጎናውያን ግን ያንጊዜ አልተሳተፉም። ኔሮ ከተወገደ በኋላ፣ ተከታዩ ጋልባ በአመጹ ያልተሳተፉት ነገዶች ከነሊንጎናውያን በቂም ቀጣቸው። በቅርብ ጊዜ ሌላ አለቃ ኦጦ ጋልባን ገድሎ ዙፋኑን ያዘ። ሊንጊናውያን ግን በዚህ ትግል ሌላ አለቃ ዊቴሊዩስ ደገፉ። ይህ «የአራት ነገሥታት ዓመት» (62 ዓ.ም.) ይባላል፤ በመጨረሻም ዌስፓሲያኑስ አሸነፈና ንጉሡ ሆነ።
ነገር ግን ያንጊዜ የሊንጎናውያን ብሔር እንደገና ሌላ ሰው መሪያቸውን ዩሊዩስ ሳቢኑስ ለሮሜ ንጉሥነት ደገፉ። የጋሊያ ከተሞች ማኅበር በዱሮኮርቶሩም (ሬም) ተሰብስቦ ዓመጽ እንዲተውና ሰላም እንዲሆን መረጡ። ሳቢኑስ ስለዚህ ቤቱን አቃጥሎ ከከተማው ከሚስቱ ኤፖኒን ጋራ እንዲሸሽ ተገደደ፣ ለ፲ም አመታት በዋሻ ይጠጉ ነበር። ሰላማዊ በሆነበት ወቅት፣ ሳቢኑስና ኤፖኒን የዌስፓሲያን ይቅርታ ለመለመን ወደ ሮሜ ተጓዙ። ንጉሡ ግን እምቢ ብሎ ሁለቱን አስገደላቸው።
ከ250 ዓ.ም. ጀምሮ ፍራንኮች በዶሮኮርቶሩም (ሬም) እና አለማኒ በሉግዱኑም (ልዮን) ያስቸግሩት ነበር። ላንግረ ከነዚህ ቦታዎች መካከል በመሆን ሁለቱ ሠራዊቶች ያጠፉት ነበር። በ290 ዓ.ም. ግን ንጉሡ ኮንስታንቲዩስ የአለማኒ ጎሣ እዚህ በሊንጎኔስ ውግያ አሸነፋቸው። እንደ ትውፊቱ ንጉሡ በመጀመርያ ወደ ከተማው መሸሽ ሲሞክር፣ በሮቹ ግን ተዘግተው ስለ ሆኑ በገመዶች አማካይነት ከግድግዳው በላይ ማረግ እንደ ነበረበት ይባላል። ከዚያ የታደሰው ሥራዊት ከከተማው ወጥተው ምናልባት እስከ ፷ ሺህ ጠላቶች አጠፉ።
- Paul Maitrier, « Toponymie haut-marnaise, origine des noms Andematunnum et Lingones », in Cahiers Haut-Marnais, n°21, 1950, p. 26 ff. (ፈረንሳይኛ)