አንድ ሺህ አንድ ሌሊቶች

ከውክፔዲያ

አንድ ሺህ አንድ ሌሊቶች (አረብኛ፦ أَلْف لَيْلَة وَلَيْلَة‎‎ /አልፍ ለይለ ዋ-ለይለ/፣ «ሺህ ሌሊትና ሌሊት») በአረብኛ የታወቀ ዝነኛ ጥንታዊ ልብ ወለድ አፈ ታሪኮች፣ አድባሬ ተረቶችና ትውፊቶች ክምችት ነው።

ጽሑፉ በመዋቅሩ በአረብኛ ከ800 ዓም ግድም መኖሩ ታውቋል። ከዚያ አስቀድሞ ታሪኩ በመካከለኛ ፋርስኛ እንደ ተገኘ ይታመናል፤ ይህ ትርጉም ግን አልተረፈልንም። ያው ፋርስኛ ጽሑፍ ደግሞ በሳንስክሪት ክምችቶች በተለይም በፓንቻታንትራ («አምስቱ ድርሰቶች») እና በቡዲስም ጽሑፍ የጃታካ ተረቶች ላይ እንደ ተመሠረተ ይታመናል። (የጃታካ ተረቶች እስካሁን በጤራቫዳ ቡዲስም ዘንድ እንደ ቀኖናዊ እምነት ጽሑፍ ይቆጠራሉ።)

ስለዚህ የአንድ ሺህ አንድ ሌሊቶች ጽንሰ ሀሣቦች ምናልባት በሕንድ አገር ከ6ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ጀምሮ ሊታይ ይቻላል። በጊዜ ላይ፣ ከትርጉም እስከ ትርጉም፣ ከቅጂ ወደ ቅጂ፣ ከዘመን እስከ ዘመን፣ አዳዲስ አፈ ታሪኮች ይጨመሩበት ነበር፤ በመጨረሻም ወደ አውሮፓዊ ልሳናት ሲተረጎም ሌሎችም ታሪኮች ተጨመሩበትና በዓለም ዙሪያ የተወደደ አዝናኝ ሥነ ጽሑፍ ሆነ።