እስክስታ
እስክስታ ትኩረቱ የትከሻ እንቅስቃሴ የሆነ፣ ነገር ግን የእግር እንቅስቃሴንም የሚያካትት የውዝዋዜ አይነት ነው። እስክስታ የሚለው ቃል እስክስ ከሚለው እንደተመዘዘ ይታመናል። እስክስ ማለት አንድን ነገር ያለ መቆራረጥ ወይንም ፍስስ በሚል መልኩ መስራት እንደማለት ነው። ስለዚህም የትከሻ አካባቢ ንቅናቄ የውሃ አወራረድን ወይንም የፏፏቴ ጅረትን በመወከል ይከወናል።
ከላይ ከተሰጠው ትርጓሜ አንጻር አብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ የውዝዋዜ አይነቶች በእስክስታ ስር ሊጠቃለሉ ይችላሉ። ልዩነታቸው እንግዲህ በየትኛው የሰውነት ክፍል ላይ ትኩረት እንደሚሰጡ ነው። የጉራጌ እስክስታ ለምሳሌ ከትከሻ ይልቅ ለእግር እንቅስቃሴ ትኩረት ይሰጣል፣ የ ሸዋ እስክስታ (ምንጃር እስክስታ) እንዲሁ ለእግር ትኩረት ሲሰጥ፣ የወሎ እስክስታ (ሆታ) ወደ ትከሻ ያደላል። የጎጃም እስክስታ (እንቅጥቅጥ፣ ዝናብ፣ ድረባ)እና የጎንደር እስክስታ (ዋንጫ ልቅለቃ፣ ደበኔ እስክስታ) ወደ ላይ ሰውነት ክፍል እንቅስቃሴ እያደላ ይሄዳል። የትግራይ እስክስታ (እስታሌላይ፣ አውርስ ) በመዘዋወር ላይ ሲያተኩር እስክስታን እንደ ቤት መምቻነት ይጠቀማል። የኦሮሞ እስክስታ (ረጋዳ፣ ሻጎየ፣ ኢጪሳ )እንዲሁ እስክስታንና የጭንቅላት እንቅስቃሴን ለቤት መምቻነት ይጠቀማል። ስለሆነም፣ እስክስታ፣ ሰፋ ባለ ሁኔታ ሲተረጎም ብዙ አይነት ውዝዋዜዎችን አጠቃሎ ሊተረጉም ይችላል።
እስክስታ ከኢትዮጵያም ባለፈ በአሜሪካውያን ዘንድ እንደ አዲስ የውዝዋዜ አይነት ሲተገበር ይታያል። በተለይ የሃርሌም ሼክ የሚባለው እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ውዝዋዜ የሚመነጭ ነው።
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |