Jump to content

እንደምን አደራችሁ

ከውክፔዲያ

እንደምን አደራችሁ

አለቃ ሀሳባቸውን በሰምና ወርቅ በመግለጽ ጥበባቸው ተወዳዳሪ የላቸውም ይባላል። ታዲያ አንድ ቀን አንድ አውቃለሁ ባይ ሰውዬ ስለእርሳቸው ቅኔያዊ አነጋገር ምንም ቦታ እንደማይሰጥና በቅኔ ቢሰድቡት እርሱ ደግሞ ከዚያ በላይ በቅኔ መልሶ ሊሰድባቸው እንደሚችል ጉራውን ይነዛል። ጉራውንም የሰሙት ሰዎች አይ አንተ ሰው! ስለማታውቃቸው ይሆናል እንጂ የሚቻሉ አይደሉም። ይሰድቡሀል። ለማንኛውም ከፈለካቸው ወደገበያው መሄጃ መንገድ አከባቢ ስለማይታጡ ብቅ ማለት ትችላለህ ይሉታል። ሰውዬውም ቢያገኛቸው ለቅኔያቸው የሚሰጠውን መልስ እያሰላሰለ አህያውንም እየነዳ ወደ ገበያ ሲሄድ ያገኛቸዋል። ከዚያም ሰውዬው «አለቃ እንደምን አደሩ?» ይላቸዋል። አለቃም ትኩር አድርገው ያዩትና የተንኮል ሰላምታ መሆኑን በመረዳት «እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ! እናንተስ ደህና አደራችሁ ወይ?» ብለው በትህትና ለሰላምታው መልስ ሰጥተው ይሸኙታል። ሰውዬውም ስላልተሰደብኩኝ መስደብ የለብኝም ብሎ እየተኩራራ ይመለስና እነዚያን ሰዎች ያገኛቸዋል። ኧሃ ከአለቃ ጋር ተገናኛችሁ? ምንስ ብለው ሰደቡህ? ሲሉት እርሱም አይ ምንም አልሰደቡኝም እንዲያውም በትህትና ሰላምታ ተለዋወጥን። እኔን ሊሰድቡኝ አይችሉም ብያችሁ የለም? አለ። እስቲ እንዴት ነበር የተባባላችሁት ሲሉት አይ እኔ አለቃ እንዴት አደሩ ስላቸው እሳቸውም በትህትና አንገታቸውን ዝቅ አድርገው “እግዚአብሄር ይመስገን እናንተስ እንዴት ናችሁ ነው” ያሉኝ አላቸው። ሰዎቹም ካንተ ጋር ሌላ ሰው ነበረ ወይ ሲሉት ኧረ የለም አህያዬን እየነዳሁ እሄድ የነበርኩ እኔ ብቻ ነበርኩኝ ሲላቸው አይ ወንድሜ ! አንድ ሰውማ እንዴት አደራችሁ አይባልም አንተን ከአህያህ ጋር አንድ አድርገው በመቁጠር ነው እንዴት አደራችሁ ያሏችሁ ብለው የሰውየውን መሸነፍ እና አህያ መባል አበሰሩለት አሉ። በዚህ የተናደደው ይህ ሰው አለቃን ሊበቀላቸው ወስኖ ከቤታቸው አቅራቢያ ካለው ጥሻ ውስጥ ተደብቆ ይቆያቸውና ማታ ሲገቡ በሽመል አንድ አምስት ጊዜ አቀመሳቸውና የልቡን አድርሶ ሄደ። በበነጋው አለቃ ቤተክርስቲያን እየሄዱ ሲያነክሱ ያዩአቸው ሰዎች ምነው አለቃ ቢሉአቸው «አህያ ረገጠኝ» ብለው አሉ ይባላል።