ካዲዝ

ከውክፔዲያ
ካዲዝ
Cádiz
ካዲዝ በምሽት
ከፍታ 11
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 128,554
ካዲዝ is located in እስፓንያ
{{{alt}}}
ካዲዝ

36°32′ ሰሜን ኬክሮስ እና 6°17′ ምዕራብ ኬንትሮስ

ካዲዝ (እስፓንኛCádiz) በደቡብ እስፓንያ የሚገኝ ጥንታዊ ከተማ ነው። የካዲዝ ክፍላገር መቀመጫ ሲሆን 130፣000 ያህል ሰዎች ይኖሩበታል። በአካባቢው ዙሪያ 500፣000 ሰዎች አሉ።

ይህ ከተማ ምናልባት ለጥንታዊነት በአውሮፓ ከሁሉ የላቀ ይሆናል። የተመሠረተው በፊንቄ (ከነዓን) ሰዎች ሲሆን፣ በ1112 ዓ.ክ.ል.በ. እንደ ሆነ የሚል ልማድ አለ።

በከነዓን ቋንቋ ስሙን «ጋዲር» (גדר ማለት ግምብ፣ ግድግዳ) አሉት። በኋላ ዘመን ግሪኮች ይህን ወደ Γάδειρα /ጋዲራ/፣ /ጋዴራ/ ቀየሩት። በሮማይስጥም ስሙ Gades /ጋዴስ/ ተብሎ በአረብኛ ደግሞ ይህ قادس /ቃዲስ/ ሆነ።

የጥንቱ ጋዲር ለፊንቄ ነጋዴዎች ከታርቴሶስ (ተርሴስ) ጋር ሲነግዱ እንደ ንግድ ጣቢያ ይጠቅማቸው ነበር። ከዚህ በላይ መጽሐፈ ኩፋሌ ምዕ. 9 የቦታውን ጥንታዊነት ይመሠክራል። በአማርኛ ትርጉም በ9፡11፣ 13 («ጋዴት» በሚል አጻጻፍ)፣ እና 25 («ጋዲር» ተጽፎ) መሠረት ሥፍራው በካም ርስትና በያፌት ርስት መካከል ያለው ጠረፍ የሚወስን ነው። ይህ ማለት ቅርብ የሆነውና በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል የሚገኘው የጂብራልታር ወሽመጥ ሳይሆን አይቀርም።

የፊንቄ ጣኦት 'መልቃርት' በዚህ ከተማ ትልቅ ቤተ መቅደስ ነበረው። በግሪኮች አስተያየት የመልቃርት መታወቂያ ከጀግናው ሄራክሌስ ጋር አንድላይ ነበር፤ ይህ ሄራክሌስም የጋዲራ መስራች መሆኑን አመኑ። በዚህም ቤተ መቅደስ ውስጥ ሁለት ግዙፍና ታላላቅ የነሐስ ዓምዶች ይገኙ ነበር። እነኚህ ዓምዶች 'የሄራክሌስ ዓምዶች' እንደ ነበሩ በሰፊ ይታመን ነበር።

በ500 ዓክልበ. ገደማ ከተማው ለቃርጣግና ግዛት ወደቀ። ሃኒባል ከዚህ ደቡብ እስፓንያ ዘመቻ ያድርግ ነበር። በ213 ዓክልበ. ግን ከተማው ለሮማ መንግሥት ሠራዊት ወደቀ። 'ጋዴስ' ተብሎ ትልቅ ከተማ ሆነ። በ5ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. ጀርመናዊው ሕዝብ ዊዚጎቶች በወረሩ ጊዜ በጥንታዊ ሕንጻዎች ላይ ብዙ ጥፋት አደረጉ። በ704 ዓ.ም. እስላሞች ያዙትና ስሙን 'ቃዲስ' አሉት። ዘመናዊ ስም 'ካዲዝ' ከዚህ የወጣ ነው። በመጨረሻ በ1254 ዓ.ም. የካስቲል ንጉሥ 10ኛ አልፎንሶ እስላሞቹን አስወጣቸው።