ዋሚ ቢራቱ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ለ100 አመታት- ሩጫ እና ዋሚ ቢራቱ

ዳግም ከበደ

በሸራተን አዲስ ሆቴል እኔና የስራ ባልደረባዬ ተገኝተናል። በዚያ የተገኘንበት ምክንያት «የሩጫ ትራኩ» ጀግና አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ነበሩ። እርሳቸውም መልካም ስብእና እና ጠንካራ ተክለ ሰውነት ተላብሰው እንደኛው በዚያ ይገኛሉ። የዝግጅቱ አስተናባሪዎች አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚን በህይወት እያሉ ሀገራቸው እና ለህዝባቸው ላደረጉት ሁሉ ለማመስገን ሰፊ ስራዎችን እየሰሩ ነው። ጥር 11 ለሚውለው ልደታቸው በርካታ ስራዎች እያከናወኑ ነው። የኛም እዛው መገኘት ስለ ልደት አከባበራቸው ሁኔታ መግለጫ ለመከታተል ነበር። ፍፁም ጠንካራ ተክለ ሰውነት፣ማራኪ ትህትና እና አስገራሚ እንቅስቃሴያቸውን በቦታው ተገኝቶ ለተመለከተ እድሜያቸውን ይጠራጠራል። ጠጋ ብሎ ሰላም ላላቸው ከመቀመጫቸው ተነስተው ጉንጫቸውን በመሳም «የኔን እድሜ ይስጣችሁ ተባረኩ» ይላሉ። ልጃቸው ጃጋማ ዋሚም አጠገባቸው ቆሞ «ተዉት ይነሳና ሰላም ይበላችሁ። በዚህ እድሜው እኔ የማልሰራውን ጅምናስቲክ ነው የሚሰራው። ጠንካራ ነው» በማለት ከመቀመጫቸው ተነስተው ሰላምታ ሲሰጡ የሚሳቀቁትን እንግዶች ያበረታታል። ሁኔታው እጅግ የሚያስገርም እና ደስ የሚል ነበር። ይህ ከሆነ አንድ ቀን አልፏል። በእለቱ የአትሌት ዋሚን ልደት የፎቶ አውደ ርእይ፣ የዶክመንተሪ ፊልም፣ በተወለዱበት ቦታ የሩጫ ውድድር እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ በደማቅ ስነ ስርአት በተከታታይ ጊዜ እንደሚከበር ተረድተን ተለያይተናል። የልደት በአሉ ከዚያን ቀን ጀምሮ መከበር ይጀምር ነበር። በቀጣዩ ቀን ከቤት ተነስቼ ወደ ስራ እየሄድኩ ነው። ትናንት በአትሌት ዋሚ የልደት ዝግጅት ላይ የነበሩትን ሁነቶች እያስታወስኩ የትራፊክ መጨናነቁን እየሸወድኩት ነበር። የነበርኩበት የታክሲ ሹፌር ሙዚቃውን ዘግቶ ራዲዮኑን ከፈተ። አጋጣሚ ሆኖ ዝግጅቱ አንድ የስፖርት ፕሮግራም ላይ ነበር። ይዞት የቀረበው ዜና ግን የሚያስደነግጥ ነበር። «ማርሽ ቀያሪው አትሌት ሻለቃ ምሩፅ ይፍጠር ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። ጀግናው አትሌት ብዙ የሰራ ግን ያልተዘመረለት ነበር» ይላል። እውነትም ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ እና የሚያስቆጭ አይነት ነበር። ትናንት የአትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱን ስለማክበር እያወራን በነጋታው ተመሳሳይ ጀግናችንን አጣነው። ሁኔታው እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስገርምም ነበር የሆነብኝ። በራዲዮው ላይ የሚያወሩት ሁለት የስፖርት ጋዜጠኞች ደግሞ «ኢትዮጵያን በአለም አቀፍ መድረክ ላይ በክብር ባንዲራዋን ያውለበለቡትን ጀግኖቻችንን በሚገባ ሳናከብር እና ሳናመሰግን መቅረታችን የሚያስቆጭ ነው» በማለት አበክረው ይናገራሉ። ሀሳባቸው ገዢ እና ትክክል ነበር። ነገር ግን አንድ ሌላ ሀሳብ ከፊት ለፊቴ ተደቅኖ ይሞግተኝ ጀመር። እነዚህ ታዋቂ የስፖረት ጋዜጠኞች ትናንት አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱን ለማክበር እና ለማመስገን በተጀመረው ዝግጅት ላይ አልነበሩም። ስለ ሁኔታውም አልዘገቡም። ታዲያ ዛሬ የአትሌት ሻለቃ ምሩፅ ይፍጠር ሞት እጅግ እንዳንገበገባቸው እየተቀባበሉ ያወራሉ። መቼም ሞት አይቀርም ሁሉም ወደዚያው ነው። ሆኖም አፋችን ከተግባራችን ቢቀድም የተሻለ ይሆናል። ማዘን ባይከለከልም አላግባብ ቁጭት ማስመሰል ይሆናል። ከነዚህ ጋዜጠኞች ጋር የተቃርኖ ስሜቴ እንዲህ እያለ ቀጠለ። አትሌት ሻለቃ ምሩፅ ይፍጠርን ብናጣውን ሌላ ተመሳሳይ ማመስገን እና ማክበር ያለብን ጀግና በእጃችን አሉ «አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ»፤ ይህ ለሁላችንም ሁለተኛ እድል ነው። ሌላ የሚኖረን አይመስለኝም። አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ማናቸው

አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ የተወለዱት በ1909 ዓ.ም በቀድመሞው ሸዋ ከፍለ አገር በመናገሻ አውራጃ በሱሉልታ ወረዳ በአካኮና መናበቹ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው። ፓስፖርታቸው ላይ የተመዘገበው የአድሜ መረጃ እና ሌሎች ሰነዶች እንደሚናገሩት ከሆነ ጥር 11 ድፍን 100 አመት ይሞላቸዋል። በሩጫ መድረክ ላይ የነገሱትን ዋሚ ቢራቱ ወደዚህች ምደር ያመጧቸው እናታቸው ወይዘሮ ወርቄ አያና እና አባታቸው ቢራቱ በራቄ ናቸው። ዋሚ ጠንከር እያሉ ሲመጡ በመንደራቸው ላይ ቤተሰባቸውን ከብት በመጠበቅ እንዲሁም አንዳንድ የእርሻ ስራዎችን በማከናወን ይረዱ ነበር። ተሮጦ ዝነኛ እንደሚኮን እንዲሁም ሰዎችን ሌሎች ተፎካካሪዎችን መብለጥ እንደሚችሉ ያወቁት ባጋጣሚ ነበር። በሩጫ አገር ማስጠራት እንደሚቻልም እንደዚሁ። አጋጣሚውን የፈጠሩት ደግሞ እናታቸው ናቸው። ወይዘሮ ወርቄ አንዳንድ ነገሮች ለመሸማመት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። አስፈላጊውን ሁሉ ካከናወኑ በኋላም ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ። ልጅ ዋሚ ደግሞ እናታቸው ሸክፈው የመጡትን እቃ ተቀብለው ወደ ቤት ይገባሉ። በዚህ እቃ ተጠቅልሎበት የመጣ ጋዜጣ እጃቸው ላይ ይገባል። ጋዜጣው የአንድ ሯጭ ምስልን ይዟል። ዋሚ ደግሞ በመንደራቸው ጋራ ተራራውን፣ ቁልቁለት ዳገቱን በሩጫ ሲቦርቁ ነው የሚውሉት። ሩጫ ስፖርት መሆኑን ተገንዝበውም እርሳቸው ጥሩ ሯጭ መሆን እንደሚችሉ በማመናቸው ልባቸው ይህን ማድረግ ይመኝ ጀመር። ይህ ከሆነ ከ 2ዓመት በኋላ ወንድማቸውን ሊጠይቁ ወደ አዲስ አበባ ጎራ አሉ። የወንድማቸው መኖሪያ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን በዚያች ገጠመኝም አዲስ ወታደሮች ሲመለመሉ ተመለከቱ። ምልመላውን ቆመው ሲመለከቱ አንድ ሃምሳ አለቃም ዋሚን ለምን አትገባም ብሎ ጥያቄ አቀረቡላቸው ።ከመስከረም 5 ቀን 1945 ዓ.ም ጀምሮ ወታደር ሆነው ተቀጠሩ። ስልጠናቸው ሲጨርሱ ዋሚ ሁለተኛ ክፍለ ጦር ተመድበው ወደ አስመራ ሄዱ። በወቅቱ ምልመላ ወታደሮችና ነባሮች በህብረት ሩጫ ይወዳደሩ ነበር ። በ10 ኪ.ሜ ዋቢ አንደ ኛ ሆነው ማሸነፍ ቻሉ ። በዚህም ምክንየት ስፖርት ላይ በመደበኛነት ቆዩ ። 1947 ዓ.ም ለዋቢም ሆነ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዩ ዓመት ነበር። ለሜሊቦርን ኦሎምፒክ ማጣሪ የሙሉ ማራቶን ውድድር ተዘጋጀ ፡፡ ከዚያ በፊት ማራቶን ተብሎ ይሮጥ የነበረው 15 ኪ.ሜ ብቻ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ማራቶኑ በመደበኛ 42 ኪ.ሜ ከ1950 ዓ.ም ሊሮጥ ተወሰነ። እያንዳንዱ ክፍለ ጦር ሶስት ሶስት ተወዳዳሪ ተመርጦ ከ8ኛ ክፍል ጦሮች 24 ተወዳዳሪ ተመረጠ ። በኋላ ግን የጦር ኃላፊዎቹ የሚፈልግ ሁሉ ይሩጥ ብለው አዘዙ። የተወዳዳሪዎቹ ቁጥር 50 ደረሰ። ውድድሩ ተጀመረ ዋሚ ያለ ምንም ችግር አንደ ኛ ሆነው አሸነፉ ፡፡ በቦታው የነበሩት ንጉሰ ነገስቱ አፄ ኃይለ ስላሴ ለአሸናፊዎቹ ዋንጫ አንዲሰጥ አዘዙ። ቀድሞ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ አሸንፈው የነበሩት ዋቢ ሶስት ዋንጫ ተሸለሙ ፡፡ በማራቶኑ ውድድር ዋሚን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆኑት ነጋሽ ቤኛ እንዲሁም ገብሬ ብርቄ አንድ አንድ ዋንጫ ተሸለሙ። የመጀመሪያው የማራቶን ውድድር በዋሚ ቢራቱ አሸናፊ ተጠናቀቀ። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጰያ ውስጥ በተዘጋጀው የማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆኑት አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ ናቸው። ከዚያን በኋላ እነ አበበ ቢቂላ ማሞ ወልዴ መድረኩን ነግሰውበታል። ይሁንና የዋሚ እና የመጀመሪው መስሪያ ቤታቸው ጦር ሃይሎች ጋር ብዙም መቆየት አልቻሉም ነበር። በአጋጣሚ ከቀዬአቸው ወጥተው የጦር ሃሐይሎች ዓባል የሆኑት ዋሚ ቤተሰቦቻቸውን ለማየት ፈቃድ ጠየቁ። የፈቃድ ጥያቄው ግን ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ዋሚና ጦር ሃይሎች ተኳረፉ። በዚህ የተነሳ በ1948 ዋሚ ክብር ዘበኛ ተቀጠሩ። 1949 ዓ.ም በልኡል መኮንን ሞት እንዲሰረዙ ተደረገ። ከ1950 እስከ 1952 በ5 ሺህ በ10 ሺህ እና በማራቶን ዋሚን የሚረታ ጠፋ። በተለይ በ1952 ዋሚ የማራቶን አንደኛነቱን ሲይዙ አበበ በቂላ 2ኛ ሆኖ ጨረሰ። ስለዚህም ዋሚ ቢራቱ እና አበበ በቂላ በሮም ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ተመረጡ። በወቅቱ ይህንን ሁሉ ስኬት ሲያስመዘግቡ ፌዴሬሽንም ሆነ አሰልጣኝ አልነበራቸውም። የስፖርት ጥትቅ የሚባል ነገርም እንደዚሁ። ይሁንና ዋሚ ራሳቸውንም ሆነ አበበ ቢቂላን እያሰለጠኑ አዲስ ታሪክ መሰራቱን ቀጠሉ፡፡ በወቅቱ በኦሎምፒክ ህግ መሰረት አንድ ሰው አሰልጣኝም ተወዳዳሪም መሆን ሰለማይችል አሰልጣኝ መቅጠር ግድ ሆነ። ስለዚህም ሰዊዲናዊው ሜጆሮኒ ስካና አበበን እና ዋሚን ለማሰልጠን ተቀጠሩ። ስዊዲናዊው አሰልጣኝ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአለም ምርጥ አትሌቶች የሚሆኑ ብላቴናዎችን እያሰለጠኑ መሆንን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም። እኚህ የባህር ማዶ አሰልጣኝ በአበበ እና በዋሚ ኢትዮጵያ አማካኝነት በረጅም እርቀት ሩጫ ድል እንደምታስመዘግብ እርግጠኛ ሆነው ነበር። ይህንንም ለንጉሱ በወቅቱ ቀርበው ተናግረው ነበር። ይሁንና ያን ሁሉ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በድንገት ታመሙ። የሮም ኦሎምፒክ ውድድር ስድስት ቀን ሲቀረው ኢትዮጵያ የተማመነችባቸው ጀግና 19 ቦታ ብጉንጅ ወጣባቸው። አሰልጣኙ ሁለተኛውን ምርጥ አትሌታቸውን አበበ ቢቂላን ለማሳለፍ ተገደዱ። ስለዚህም አበበ በሮም ጎዳናዎች ታላቁን ተልእኮ ለመሸከም እና ለመፈፀም ተገደደ።

አበበ ኢትዮጵያን ሮም ላይ ወክሎ ሮጠ። ኢትዮጵያውያንን አላሳፈረም። ፌዴሬሽን የሌላት ትጥቅም የማታቀርበው ሀገር በባዶ እግሩ በሮጠው ሰው አሸናፊነት አዲስ ታሪክ አፃፈች። ብዙዎች «አንድ ጥቁር አፍሪካዊ   ጣሊያንን በባዶ እግሩ ወረራት» በማለት ከአድዋ ድል ጦርነት ታሪክ ጋር አያያዙት። ከውድድሩ በኋላ በባዶ እግሩ  ሮጦ ያሸነፈውን ጥቁር ሰው ጋዜጠኞች ጥያቄ  አቀረቡለት «በሀገሬ እኔ አይደለሁም፤ በህመም ምክንያት አሸናፊው አልመጣም አላቸው» ሲል አጋሩን ዋሚ ቢራቱን አንቆለጳጰሰው። አበበ በሮም ላይ ያስመዘገበው ድል ለአለም ህዝብ ድንቅ ቢሆንም አትሌት ዋሚ ቢመጣ ኖሮ ከዚህ በላይ ተአምር ታዩ ነበር በማለት በአስተያየቱ አለምን ይበልጥ አስደነቀ። 
በዋሚ መንገድ አበበ በቂላ ፣ማሞ ወልዴ ፣ምሩፅ ይፍጠር ፣ሃይሌ ገ/ስላሴ ፣ደራርቱ ቱሉ ፣ቀነኒሳ በቀለ ፣ፋቱማ  ሮባ ፣ብርሃኔ አደሬ ፣ጌጤ ዋሚ ፣ጥሩነሽ ዲባባ  ፣መሰረት  ደፋር  ፣ስለሺ ስህል  ፣ገንዘቤ ዲባባ የመሳሰሉ ጀግኖች መፍራታቸውን ብዙዎች ይናገራሉ። 

ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በተለያዩ የሩጫ መድረክ ላይ አገራቸውን ያስጠሩበት ድል አስመዝግበዋል። ከነዚህ መካከል በ1ሺ500፣3ሺ፣5ሺ፣10ሺ፣21ኪሜ፣25ኪሜ፣በ32ኪ.ሜ በአገር አቋራጭ እና የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ 51 የወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሀስ ሜዳሊያዎችን ማገኘት ችለዋል። ከዚህም ሌላ 21 ሰርተፍኬት፣ 4 ዲፕሎማ እና ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ወስደዋል። በተለያየ ወቅትም የኢትዮጰያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አስችለዋል። የሶምሶማ እሩጫ በአገራችን እንዲለመድ ለማድረገ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል። እኚህ አንጋፋ አትሌት ምንም እንኳን እድሜያቸው ቢገፋም በተለያየ ጊዜ ውድድሮችን እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ይታወቃሉ። ለጠንካራ ተክለ ሰውነታቸው እና በጤንነት ረጅም እድሜ መቆየታቸው ደግሞ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፋቸው ያመጣው ውጤት እንደሆነ ይነገራል። ከዚህ ጥንካሬያቸው መካከልም በእርጅና ዘመናቸው በታላቁ ሩጫ ላይ ተሳታፊ ሆነው ያለምንም ችግር ማጠናቀቃቸቸው ነው። ሻለቃ ባሻ ዋሚን ለማክበር ሻለቃ ባሻ ዋሚ የፊታችን ጥር 11 ድፍን 100 አመት ይሞላቸዋል። በአትሌቲክሱ ላይ ደግሞ ለ64 አመት ነግሰውበታል። የ100ኛ አመት ልደትና ሩጫ የጀመሩበት 64ኛ ዓመት በዓል በዶክሜንተሪ ፊልም፣ በስእል አውደ ርዕይ በስማቸው አደባባይና መንገድ በመሰየምና ወደ ትውልድ ከተማቸው በመሄድ ይከበራል። አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ሩጫን የተቀላቀሉት በውትድርና አገራቸውን እንዲያገለግሉ ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ ነው። ከዚያን ዘመን ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለአገራቸው ድልን በማስመዝገብ እንደ አበበ ቢቂላ ላሉ ብርቅዬ አትሌቶች አርአያ ቢሆኑም የሰሩትን ያህል አለመከበራቸውን በተለያየ ጊዜ ይገለፃል። አሁን ይህን ዝግጅት ለማድረግ ያሰቡት አካላትም ጀግኖቻችን በህይወት እያሉ እናክብራቸው የሚል ሀሳብ ሰንቀው ነው ስራውን የጀመሩት። እርሳቸውን ከማክበር እና ከመደገፍ ባሻገር የጥንካሬያቸውን ምስጢር ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ እድል ይፈጥራል።