Jump to content

ዘውዱ ጌታቸው

ከውክፔዲያ
ዘውዱ ጌታቸው

ዘዉዱ ጌታቸው (አዲስ አበባ 1952 -አዲስ አበባ ታኅሣሥ 18 ቀን 1997 ዓ.ም)፣ ኤች.አይ.ቪ|ኤድስን በሚመለከት ፀጥታና ዝምታ በሰፈነበት ወቅት ራሱ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይፋ በማዉጣት «ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ» ! ብሎ ኤች.አይ.ቪ|ኤድስን ለመዋጋት የተነሳ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነበረ። ዘውዱ ጌታቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በመስፍን ሀረር ትምህርት ቤት ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋክልቲ በመግባት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱንም አጠናቋል። በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት እንዲሁም በዚላ፥ በበርታ፥ በሱርና፥ በሶጀት ኮንስትራክሽን ድርጅቶች በመካኒክነት ሠርቷል።

«እኔ ከቫይረሱ ጋር የምኖር ነኝ።» በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብን በአደባባይ ለማስተማር መውጣት እጅግ በጣም ጥቂት ቆራጦች ብቻ የሚደፍሩት ተግባር በነበረበት ጊዜ ብቅ ብሎ ለአገር የሚጠቅም ታላቅ ተግባር ሲያከናውን የቆየ ሰው ነበረ። ዘውዱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ማህበር «ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያን» በ1990 ዓ.ም. ከአሥር ጓደኞቹ ጋር በመመስረት ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች መብታቸውን ለማስከበር እንዲታገሉ ከማሰባሰቡም በላይ ኤች.አይ.ቪ|ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል። ራሱ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይፋ አውጥቶ በማሳወቁ ምክንያት ይደርስበት የነበረውን አድልኦና ማግለል በቆራጥነት በመፋለም ዛሬ ኤች.አይ.ቪ|ኤድስን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኙ አዎንታዊ ለውጦች ከፍ ያለ ድርሻ አበርክቷል። ዘውዱ ጌታቸው በአገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተስፋ ጎህን በመወከል የኤች.አይ.ቪ|ኤድስ ችግር በአገራችን እያደረሰ ያለውን እዉነታ በመናገርና ለበሽታዉ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ጥሯል። በተጨማሪም «ተስፋ ብርሃን በኤድስ ወላጅ አልባ ሕፃናትና ወጣቶች ማህበር»ንም በመመስረት ኤች.አይ.ቪ|ኤድስን የሚያስከትለውን ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ በመታገል አያሌ ታዳጊዎችን ከመበተን አድኗል። ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በኤች.አይ.ቪ ምክንያት በስራ ቦታ የሚደርሰውን አድልኦና ማግለል ይበልጥ ለመታገል ወደ ማህበር ለመምጣት ያልደፈሩትን ወገኖች በስልክና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች የምክር አገልግሎት ለመስጠትና ከኤች.አይ.ቪ|ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ሰብአዊ መብት እንዲከበር ይበልጥ ለመታገል «አዲስ ምዕራፍ» የተባለ ድርጅት አቋቁሟል። እስከ ሕልፈተ ሕይወቱ ድረስ ሠርቷል። ዘውዱ ጌታቸው ባደረበት ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎች በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ45 ዓመቱ ታህሣሥ 18 ቀን 1997 ዓ.ም. ከዚህ አለም በሞት ተለይቱዋል።