Jump to content

ዛር

ከውክፔዲያ
ባለ ዛር ሴት የዶሮ መስዋዕት ስታቀርብ -- ግብጽ አገር

ዛር በምስራቅ አፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያና ሱዳን አካባቢ የተለመደ የመንፈሶች ስብስብ እና በዚህ ስብስብ ዙሪያ ያለ ዕምነትና ተግባር ነው። በተመሳሳይ መልኩ የዛር እምነት የግሪክ እና ሮሜ ወረራ ሰለባ ባልሆኑት የግብጽ ክፍሎች፣ በተለይ በደቡባዊ ግብጽ የሚዘወተር ነው[1]። ከዚህ በተረፈ የዛር እምነት በጅቡቲኤርትራሶማሊያ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢራን ድረስ የዛር እምነት፣ በብዙ ዓይነት ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሲሰራበት ይታያል[2]፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ዛር፣ ለሚያምኑት ሰዎች፣ የማይታይ ግን የወደፊቱን ማየት የሚችል፣ የዓለምን ችግር ሊፈታ እስኪችል ሃይል ያለው፣ ከስጋ ደዌ በሽታዎች ውጭ ማናቸውንም በሽታዎች ማዳን የሚችል፣ በአንጻሩ ደግሞ የማያከብሩትን ሰዎች መጉዳት፣ መግደልና ማጥፋት የሚችል መንፈስ ነው[3]

የአእምሮ በሽታ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሆኖም ግን ይህ የዛር መንፈስ ብዙ ጊዜ የሚታየው በድሃውና በተጨቆነው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ተመራማሪዎች ከዚህ ተነስተው የዛር መንፈስ የሚመጣው ከመጨቆን፣ ክበታችነት ስሜት፣ እንዲሁም የፍላጎት አለሟሟላት ከሚፈጥረው የአእምሮ ቀውስ ነው[4]። ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ በዚሁ በሽታ ሲጠቁ ይታያሉ። ደቡባዊ ግብጽም ውስጥ ሴቶች ለዛር የበለጠ ተጠቂ እንደሆኑ ይጠቀሳል[5]እስራኤል አገር ያሉ ሃኪሞች የዛር በሽታን ከሳይንስ አንጻር በቀላሉ ሊያክሙት እንደቻሉ ጥናታቸው ያስረዳል [6]። በእስራኤል አገር የሴቶች መብት የመከበር ሁኔታ ሲታይ በዛር የሚጠቁ ኢትዮጵያውያን እንደቀደሞው አብዛኞቹ ሴት ከመሆን ይልቅ ወንዶቹም ሴቶቹም እኩል የመጠቃት ሁኔታ አሳይተዋል[7]

ዛር በባለ-ዛሮች እይታ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የዛር አመጣጥ አፈ ታሪክን አጥኝው ራይደልፍ ሞላቨር መዝግቦት ይገኛል። እንደ አፈ ታሪኩ አገላለጽ፣ አዳም እና ሔዋን ከገነት ከተባረሩ በኋላ 30 ጥንድ ልጆች የነበሯቸው ሲሆን አንድ ቀን እግዚአብሔር ሊጠይቃቸው ሲመጣ 15ቶቹን እና ቆንጆ የሆኑትን ልጆቻቸውን በዋሻ ደብቀው 15ቱን ጥንድ ብቻ ለእግዚአብሔር አሳዩ። እግዚአብሔርም በማዘን ዋሻው ውስጥ ያሉት 30ዎቹ ቆንጆ ልጆች እስከ ዘላለሙ እማይታዩ ይሁኑ ብሎ ተራገመ። እኒህ እንግዲህ የዛር መንፈስ ወይንም ዛር ሆኑ[8]

እንደ አፈ ታሪኩ እንግዲህ ዛሮች የሰው አይነቶች እንጂ አጋንንቶች አይደሉም። እንደሰው ሁሉ፣ ገሚሶቹ ዛሮች ጥሩ ሲሆኑ ገሚሶቹ ደግሞ መጥፎ ናቸው። የዛር አለቆች እርስ በርሳቸው ሲዋለዱ ሃይለኛ ዛር ሲወልዱ ዛሮችና የዛር አሽከሮቻቸው ሲዋለዱ ደግሞ የዛር ውላጅ ይፈጥራሉ፡፡ በአፈ ታሪኩ መሰረት እነዚህ የዛር ውላጆች ሃይላቸው አነስተኛ ነው ማለት ነው። ዛር ጠሪዎች ዛሮችን በስማቸው ሊያውቁዋቸው ይችላሉ፤ ከነዚህ ስሞች ውስጥ ጠቋር፣ ግራኝ፣ አንበሶ፣ ከድር... ይጠቀሳሉ [9]

አፈ ታሪኩ የዛርን ወደኢትዮጵያ መምጣት በዓፄ ካሌብ ዘመን ያደርገዋል። ዓፄ ካሌብ ስልጣናቸውን ሲለቁ ዓፄ ገብረ መስቀልን የሚታየው አለም ንጉስ አርገው ሾሙ። የገብረ መስቀልን ወንድም ወልደ እስራኤልን ደግሞ የማይታየው አለም (የዛሩ አለም) መሪ አድርገው ሾሙ። ወለተ እስራኤል እንግዲህ እስካሁን ዘመን የመንፈሳዊው አለም ገዢ ነው [10]

  1. ^ http://www.touregypt.net/featurestories/zar.htm
  2. ^ Oromos, Slaves, and the Zar Spirits: A Contribution to the History of the Zar Cult Richard Natvig The International Journal of African Historical Studies Vol. 20, No. 4 (1987), pp. 669-689
  3. ^ Torrey, E. Fuller. "The Zar Cult in Ethiopia." Proceeding of the third International Conference of Ethiopian Studies, Addis Ababa 1966. Addis Ababa: Haile Sillassie University.(1966)
  4. ^ Lewis, Herbert S. "Spirit Possession in Ethiopia: An Essay in Interpretation." In Proceedings of the Seven International Conference of Ethiopian Studies. University of Lund, 26-29 April 1982. ed. Sven Rubenson. Uppsala: SIAS, 1984
  5. ^ http://www.touregypt.net/featurestories/zar.htm
  6. ^ http://www.ncbi.nlm.nih.gov/pubmed/7926995
  7. ^ http://www.ncbi.nlm.nih.gov/pubmed/7926995
  8. ^ Reidulf Knut Molvaer Socialization and social control in Ethiopia (1995) page 42
  9. ^ Reidulf Knut Molvaer Socialization and social control in Ethiopia (1995) page 42
  10. ^ Reidulf Knut Molvaer Socialization and social control in Ethiopia (1995) page 42