የማርያም ቅዳሴ

ከውክፔዲያ

አባ ሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ አምላክን ስለ ወለደች ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ የደረሰው የቁርባን ምስጋና ይህ ነው ። ልመናዋ በረከትዋ ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን ።

የማርያም ቅዳሴ

ዘቅዱስ ሕርያቆስ
የቅዱስ ሕርያቆስ የንግሥ ቀን ጥቅምት ፪ (ያረፈበት)
የትውልድ ሀገሩ ግብፅ (ብኅንሳ)
የተወለደበት ዘመን ዘመነ ሊቃውንት (ከ፫፻ እስከ፬፻ ዓ.ም) ማለት ነው


፩ ፤ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን ። ከመንፈስህ ጋር አምላካችንን አመስግኑት ። እውነት ነው ይገባዋል ። ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ ። በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን ።
፪ ፤ ልቦናዬ በጎ ነገርን አወጣ ።ልቦናዬ በጎ ነገርን አወጣ ። ልቦናዬ በጎ ነገርን አወጣ ።
፫ ፤ እኔም የማርያምን ቅዳሴ እናገራለሁ ። በማብዛት አይደለም በማሳነስ ነው እንጂ ። እኔም የድንግልን ውዳሴ እናገራለሁ ። መዘንጋት ባለበት ቃል በማስረዘም አይደለም ። በማሳጠር ነው እንጂ እኔም የድንግልን ገናንነትዋን እናገራለሁ ።
፬ ፤ ዛሬ በዚች ቀን በፍቅርና በትሕትና ግሩም በሚሆን ምሥጢር ፊት እቆማለሁ ። በዚህ ማዕድና ቁርባን ፊት ።
፭ ፤ መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቁርባን ነው ። በበግ በጊደርና በላም ደም እንደ ነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም እሳት ነው እንጂ ።
፮ ፤ ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቦናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው ። ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው ።

ገፅ ፩