የዋልታ ወፍ

ከውክፔዲያ
የዋልታ ወፍ በአንታርክቲካ
የዋልታ ወፍ መኖሪያ

የዋልታ ወፍ (ፔንጒን) Sphenisciformes በአንታርክቲካ አካባቢ የሚገኝ የአዕዋፍ አስትኔ ነው። የማይበርሩ ጥቁርና ነጭ ወፎች ናቸው፤ ክንፎቻቸው በውቅያኖስ ውስጥ ለመዋኘት ተዘጋጅተዋል።

በውነት ሁላቸው በውርጭ አገር የሚገኙ አይደለም፣ በሞቀውም አገር ደግሞ የሚኖሩ አሉ። ባብዛኛው በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ውስጥ ብቻ የሚታዩ ሲሆን፣ አንዱ ዝርያ የጋላፓጎስ ዋልታ ወፍ ብቻ ከምድር ወገብ በስተሰሜን ይገኛል።

አብዛኛዎቹ ዝርያዎች በአሳ ወይም በሌሎች የባሕር ሕይወቶች የሚመገቡት በውሃ ውስጥ በሚዋኙበት ጊዜ ነው። ከሕይወታቸው ግማሹን በውቅያኖስ፣ ግማሹንም በየብስ ላይ ያሳልፋሉ።

ከሁሉ ታላቅ የሆነው ዝርያ ንጉሥ ዋልታ ወፍ (Aptenodytes forsteri) በአንታርክቲካ የሚኖር ሲሆን በአማካይ ቁመቱ ከ1.1 ሜትር እና ክብደቱ 35 ኪሎግራም ይሆናል። በጣም ትንሽ የሆነው ዋልታ ወፍ ዝርያ ትንሽ ሰማያዊ ዋልታ ወፍ Eudyptula minor በአውስትራሊያ ኗሪ ሲሆን፣ ይህም ቁመቱ 40 ሴንቲ ሜትር የሚያክል፣ ክብደቱ ከ1 ኪ.ግ. ይመዘናል። በጥንት በቅድመ ታሪክ እስከ ሰው ልጅ ቁመት ድረስ (1.8 ሜትር) የቆመ ታላላቅ ዝርያ («Anthropornis») በኒው ዚላንድ አካባቢ እንደ ኖረ ከቅሪተ አካሎች ታውቋል። በዘመናዊ ሳይንሳዊ ግመት ይህ ታላላቅ ዋልታ ወፍ ዝርያ ከ33 እስከ 45 ሚሊዮን ዓመታት ከአሁን በፊት ይመላለስ ነበር።

ሀ) ጥንት የጠፋ ታላቅ ፔንጒን፣ ለ) የሰው ልጅ፣ ሐ) የዛሬው ንጉሥ ፔንጒን።

እንግሊዝኛ፣ «ፔንጒን» የሚለው ስም መጀመርያው በ16ኛው ክፍለዘመን ሲታይ፣ ይህ የሌላ ወፍ አይነት ስም ነበረ። በስሜን ክፍለ-አለም ለታወቀ፣ ዋልታ-ወፍን ለመሰለ እንጂ በቅርብ ላልተዛመደው፣ አሁንም ለጠፋው ዝርያ ታላቅ አውክ (Pinguinus impennis) ይሰይም ነበር። ታላቅ አውክም በራሱ ላይ ነጭ ስለነበረው፣ ስሙ ከዌልስኛ /ፐን ጒን/ «ነጭ ራስ» እንደ ተሰጠ ይታስባል። በኋላ መርከበኞች ወደ ደቡብ ክፍለ አለም ሲጓዙ የዋልታ ወፉን ተመሳሳይነት አይተው እሱንም «ፔንጒን» ይሉት ጀመር። ይሁን ኢንጂ በሆላንድኛ ዋልታ ወፍ ደግሞ /ፈትጋንዝ/ «የስብ ዚዪ» ሊባል ይችላል፤ ስለዚህ «ፔንጒን» ከሮማይስጥ /ፒንጒስ/ «ስብ» እንደ ደረሰ የሚያስቡ አሉ።

አሁን የሚገኙ የፔንጒን ዝርያዎች ሁሉ በስድስት ወገኖች ይከፈላሉ፤ በነዚህም ውስጥ እንደ ምንጮቹ ልዩነት ከ17-20 ልዩ ልዩ ዝርዮች አሉ።