የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፩

ከውክፔዲያ

ክፍል ፩[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በዚህ የመጽሃፉ ክፍል የዞራስተር ዋና ነጥቦች በስድስት ዋና ዋና ሃሳቦች ይጠቃላል።

  • የመጀመሪያው የዞራስተር ነጥብ አጠቃላይ ሜታፊዝክን መካድ ነው። ሜታፊዚክ ማለት በተጨባጩ አለም ጀርባ የማናየው፣ የማንዳሰሰው፣ የማናሸተው እውነተኛ አለም አለ በማለት ይህን አለም ለማግኘት የሚጥር የፍልስፍና ዘርፍ ነው። በዞራስተር አስተያየት አንድ አለም ብቻ አለ፡ እርሱም ተጨባጩ አለም ነው።
  • ሁለተኛው የዞራስተር ነጥብ የአይምሮአካል ክፍፍልን መካድ ነበረ። በተለምዶ ሰው አካል አለው ብንልም በዞራስተር አስተያየት ሰው እራሱ አካል ነው። የሰው ልጅ ከማይጨበጥ ምናባዊ ነገር (አዕምሮ) እና ከተጨባጭ ነገር (አካል) የተሰራ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከአካል የተሰራ ነው። በነደካርት የተነሳው ቀልበኛ ፍልስፍና የስውን ልጅ ከሁለት (አዕምሮና ሰወነት) ከከፈለ ወዲህ የስው ልጅ የስራ ውጤቶች ብዙ አመርቂ አልሆኑ፣ ይልቁኑ የጥንቶቹ ከያኒያን በ"ደማቸው የጻፉዋቸው መጽሃፎች" (በአይምሮ ከተጻፉ ዘመናዊ መጽሃፎች) በተለየ መልኩ ስሜት የሚነኩ እንደነበሩ አስተማረ። የሰው ልጅ "አዕምሮ" ከሆነ ወዲህ ስራው ሁሉ በቀመር የተወጠረና ምንም ስሜት የማይቀስቀስ ሆነ።
  • ዞራስተር ሙሉ በሙሉ የግለሰብ ነጻነትን ይደግፋል። ግብረገብ፣ የጋራ ሰላምና፣ ይሉኝታ ለዞራስተር ደንታው አይደሉም። የህይወት ኃይሎች በምንም አይነት መታፈን የለባቸውም። የተመረጡ ነፍሶች የመንጋወችን ግብረ ገብና ስርዓቶች ወደጎን ትተው የራሳቸውን ዋጋ/ህግ አውጥተው የራሳቸውን አላማ ለማስፈጸም ይታገላሉ። ትክክለኛው የህይወት ጣዕም በህግጋትና ግብረገብ የተጋረደ ሳይሆን ከኃጢያትጽድቅ ወዲያ ርቆ የሚገኝ ነው።
  • ሙሉው የግለሰብ ነጻነት "ሁሉ በሁሉ ላይ" ጦር እንዲያነሳ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ግን በዞራስተር አይን ምንም አይደለም ምክንያቱም ሁሉም ህይወት ያለው ነገር "ኃይልን ይፈቅዳል"፡ ሁሉም ህይወት ያለው ነገር እራሱን ያረጋግጣል፣ ለመኖሩም ምልክት ትግል ያካሂዳል። ሄራክሊተስ እንደጻፈ "ጦርነት የሁሉ ነገር አባት ነው"፣ በዞራስቱራ አስተያየት ያለፍልሚያ ምንም ጥቅም ያለው ነገር አይመጣም። ዞራስተር ለጓደኞቹ የሚመክረውም "በአደጋ ኑር!" እያለ ነበር። ፍቅረኛሞች እንኳ ሳይቀሩ ችግር ሊገጥም እንዲችል መረዳት አለባቸው፣ በፍቅር መጎዳት የሚፈራ ወይም ቂም የሚያሲይዝ ሳይሆን እራስን ለማሳደግና አዳዲስ ነገሮችን ለመረዳት የሚያገልግል ዕድል ነው። ጦርነት ተቀባይነት ያለው መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት ያለው ግብም ነው።
  • እራስን መወሰን ለዞራስተር ፍልስፍና ዋና ቁልፍ ነው። ይህ አለም ከላይም ሆነ ከታች ከጎንም ሳይቀር የተሰጠው ትርጉምም ሆነ ህግጋት የሉትም። ሁሉም ሰው የራሱን ትርጉምና ህግጋት በመፍጠር እራሱን ይወስናል። ሁሉም ሰው ልክ እንደሙሴ የራሱን ጽላት እንዲቀርጽ እንጂ ለሁሉም የሚሰራ ከላይ የተላለፈ ህግ የለም። ከዚህ አንጻር እራስን መወሰን ባንድ በተስተካከል የአለም ስርዓት ውስጥ ራስን መቻል ሳይሆን ከትርምስ ውስጥ የራስን አለምን እንደመፍጠር ነው።
  • ህይወት ሂደት እንጂ ሁኔታ አይደለም። አንድ የሰው ልጅ በሂደት ላይ ያለ እንጂ፣ ቆሞ ያለ የሆነ ነገር አይደለም። እራስን እንደ አንድ ቋሚ ነገር ማሰብ በዞራስተር ስህተት ነው። በመጠበቅ፣ እውቀትንና ሃብትን ዝም ብሎ በማከማቸት ህይወት አይኖርም፣ ይልቁኑ እራስን በየጊዜው በማሸነፍና እራስን በመቀየር ህይወት ይኖራል።

ሶስቱ ሽግግሮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ሌላው የዚህ ክፍል ዋና ሃሳብ ሶስቱ ሽግግሮች ናቸው፡፡የሰው መንፈስ እውነቱንና እራሱን ለማወቅ 3 ከባድ ለውጦች እንደሚያካሂድ ዞራስትራ በዚህ ክፍል ሲያስረዳ፦
" እነሆ ነፍሳችሁ ሶስት ጊዜ ይሻገራል፡ እንኪያስ ግመል ነበራችሁ፣ ግመሉ አምበሳ፣ በመጨረሻ አምበሳው ህጻን ልጅ!"

ትርጉሙም የመጀመሪያው የመንፈስ ለውጥ ወደ ግመል ሲሆን ይህም "ትሁት መንፈስ"ን ያመላክታል፡ እራስን መካድ፣ በሃብት መቆጠብን፣ መታዘዝንና ችግርን መቋቋምን። ይህም ግመልን እራሷን ዝቅ አድርጋ የጭነት እንስሳ እንደሚያደርጋት ባህርይ ነው።

" ጫን ያለበት መንፈስ እንዲህ ይጠይቃል "ከሁሉ ነገር ከባዱ ምንድን ነው?" መልሶም "በጫንቃየ ላይ ጭነቴን አዝየ በጥንካሬየ ሐሴት ማድረግ አይደለምን? እራሴን በማዋረድ ኩራቴን መግደል አይደለምን? የዋህነቴን በማጋነን ጥበቤን መፎተት አይደለምን?"

ከዚህ የግመል አለም ወደ አንበሳነት የሰው መንፈስ ለሁለተኛ ጊዜ ይሻገራል። በዚህ ጊዜ ከጭነት ነጻ ይሆናል፣ ከላይ ወደታች በተዘርጋ የሃይል አሰላለፍ ቁንጮውን ለመያዝ ጥረት ያደርጋል፣ ራስ ገዝ ሆኖ ነጻነቱን በራስ ገዝነትና በሃያልነት ይደነግጋል። በታላቁ ዘንዶ ላይ ጦርነት ይክፈታል፣ የቀድሞውን ግብረገብ ጽንሰ ሃሳብ አውልቆ ይጥላል።

"ለራሱ ነጻነትን ለመቀዳጀት፣ በህግጋት ላይ ሳይቀር "እምቢ" ለማለት፣ ወንድሞች፣ ለዚያ ለዚያ አንበሳ ያስፈልጋል። አዳዲስ ህግጋትን የመፍጠር መብት እንዳለ ለማወቅ ለተሸካሚና ለአክባሪ ነፍሳት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ ተግባር ለነዚህ እንደ ማደን እና የሚታደን እንስሳ ስራ ነው።"

አንበሳ እንግዲህ የነበረውን እምቢ በማለት የሚያፈርስ እንጂ አዲስ የሚፈጥር አይደለም። ስለሆነም የሰው መንፈስ አዳዲስ ህግጋትን ለመፍጠር ለ3ኛ ጊዜ መሻገር ይኖርበታል። በዚህ የመጨረሻው ሽግግር መንፈሱ ከአንበሳ ወደ ህጻን ይቀራል። ህጻኑ አዲስ ጅማሬን፣ ንጹህ የዋህነትን የሚወክልና የድሮወቹን ህግጋት ድል ካደረገ በኋላ አዲስ ዋጋወችን ፈጣሪ ይሆናል።

"ሕጻን የዋህነት ነው፣ ያለፈውን መርሳትም ነው፣ አዲስ ጅማሬ፣ ጨዋታ፣ እራሱን የሚያሽከረክር ጎማ፣ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ፣ ቅዱስ የሆነ "አወ-ማለት"። አወ! ወንድሞች፣ የፈጠራ ጨዋታ ቅዱስ የሆነ "አወ" ማለትን ይጠይቃል፡ መንፈስ የራሱን ፈቃድ ይፈቅዳል፣ አለሙን ያጣ እንግዲህ የራሱን አለም ያገኛል።"

ሁሉ ነገር በህጻን ልጅ ተጀምሮ እንደገና በህጻን ማብቃቱ የኒሺን የዘላለም ምልልስ ጽንሰ ሃሳብ የሚያንጸባርቅ ነው። በዚህ የዘላለም ድግግሞሽ የሰው ልጅ እራሱን በማሽነፍ ከነበሩበት ድክመቶች ሁሉ ነጻ በመውጣት አዲስ አይነት ሰው -- የራሱ ህግ/ዋጋ ያለው የበላይ ሰው ይፈጥራል።

እኒህን ነጥቦች ለተመረጡ ተከታዮቹ ካስተማረ በኋላ ዞራስተር ወደተራራ ዋሻው እንደተመለሰ መጽሃፉ ያትታል። የዚህ ምክንያቱ ያለሱ ተጽዕኖ ተከታዮቹ በራሳቸው ውሳኔ የራሳቸውን ሃሳብ እንዲያዳብሩ ነው። አስተማሪነቱን ማቆሙም ይህን የፍልስፍናውን ግብ ላለማጣረስ ነበር።