ጉንጉኑም
ጉንጉኑም ከ1844 እስከ 1817 ዓክልበ. ድረስ (ኡልትራ አጭር) የላርሳ መጀመርያ ንጉሥ ነበረ።
በኋላ በተጻፈው «የላርሳ ነገሥታት ዝርዝር» በተባለው ጽላት ዘንድ፣ ከጉንጉኑም አስቀድሞ የላርሳ ነገስታት ናፕላኑም፣ የምጺዩም፣ ሳሚዩም እና ዛባያ ነበሩ። ከሥነ ቅርስ ግን እነዚህ ሰዎች በላጋሽ ዙሪያ የገዙት የአሞራውያን አለቆች እንደ ነበሩ ይመስላል፣ እንጂ «ንጉሥ» ለሚለው ማዕረግ አልደፈሩም። ጉንጉኑም የሳሚዩም ልጅና የዛባያ ወንድም እንደ ነበር ከጽሑፎቻቸው ይታወቃል።
ለዘመኑ ከ፳፰ የዓመት ስሞቹ ሁላቸው በሙሉ ታውቀዋል። ከነርሱም መካከል፦
- 1844 ዓክልበ. ግ. - «ጉንጉኑም ንጉሥ የሆነበት ዓመት»
- 1842 ዓክልበ. ግ. - «ባሺሚ የጠፋበት ዓመት»
- 1840 ዓክልበ. ግ. - «አንሻን የጠፋበት ዓመት»
- 1835 ዓክልበ. ግ. - «ሁለት ታላቅ ምልክታትና የመሽከሚያ ወምበር እንደ ስጦታ ወደ ናና ቤተ መቅደስ (በኡር) ያመጣበት ዓመት»
- 1826 ዓክልበ. ግ. - «በአማልክት ትዕዛዝ ማልጊዩም በመሣርያዎች የተሸነፈበት፣ የመንግድ ቤት የያዘበት፣ የተራራ ቦይ ምንጭ የከፈተበት ዓመት»
ጉንጉኑም የላርሳን ነጻነት ከኢሲን መንግሥት አዋጀ። መጀመርያ ፱ የዓመት ስሞቹ ስለ ላርሳ ጣኦት (ኡቱ) ሲጠቀሱ፣ ከ፲ኛው ዓመት(1835 ዓክልበ.) ጀምሮ የኡር ቤተ መቅደስ ይጠቀሳል። ስለዚህ ጉንጉኑም ዑር ከኢሲን ግዛት የያዘው በዚያ ወቅት ያህል እንደ ነበር ያስረዳል። በ፲፫ኛው ዓመት (1832 ዓክልበ.)፣ የኢሲን ንጉሥ ሊፒት-እሽታር ሴት ልጅ ኤኒንሱንዚ የዑር መቅደስ ጣኦት ሴት ካህን ሆና እንድትሾም አረጋገጠ። ለዚህ ሹመት መመረጧ ደግሞ በሊፒት-እሽታር ዓመት ስም ይዘገባል።
በ1826 ዓክልበ. ማልጊዩምን ከማሸነፉ በላይ «የመንገድ ቤት» እንደ ያዘና ቦይ እንደ ከፈተ ይዘገባል። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በሊፒት-እሽታር ጽላቶች ይጠቀሳሉ። የሊፒት እሽታር ሻለቃ ናና-ኪአጝ በጻፉለት ደብዳቤ ዘንድ፣ ፮ መቶ የጉንጉኑም ወታደሮች «የመንገድ ቤት» ይዘው አዲስ ቦይ ሊከፈቱ ነው ሲል የሊፒት-እሽታርን እርዳታ ይለምናል። በሊፒት-እሽታር መልስ ፪ ሺህ ጦረኞች፣ ፪ ሺህ ቀስተኞች፣ እና ፪ ሺህ ባለ ዶማዎች መላኩን አመለከተ። ሆኖም ጉንጉኑምን ድል እንዳደረጉ አይመስልም።
ጉንጉኑም በግዛቱ ውስጥ ላርሳን፣ ዑርን፣ ኒፑርንም ጨምሮ «የሱመርና የአካድ ንጉሥ» ለሚለው ማዕረግ ይግባኝ አለ። ሆኖም የኢሲን ነገሥታት ተወዳዳሪዎች ሆነው ለዚያው ማዕረግ ይግባኝ ይሉ ነበር።
የጉንጉኑም ተከታይ አቢሳሬ ሲሆን እርሱ የጉንጉኑም ልጅ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ አይታወቅም።
ቀዳሚው ዛባያ (የአሞራውያን አለቃ) |
የላርሳ ንጉሥ 1844-1817 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ አቢሳሬ |
- የጉንጉኑም ዓመት ስሞች
- የላርሳ ንገሥታት Archived ኦክቶበር 21, 2012 at the Wayback Machine (እንግሊዝኛ)