ጋላጤስ

ከውክፔዲያ

ጋላጤስፈረንሣይ አፈ ታሪክ የኬልቶች (በጋሊያ፣ አሁንም ፈረንሳይ አገር) ንጉሥ ነበረ። ስለርሱ አገሩ አዲስ ስሙን «ጋሊያ» አገኘ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በግሪክኛ «ጋላቴስ» ተባሉ።

ጋላጤስ የኬልቴስ ተከታይ ሲሆን በአብዛኛው ምንጭ የሄርኩሌስ ሊቢኩስ ልጅ ይባላል፤ ይህ ሄርኩሌስ ሎምኒኒን ገድሎ ከኢቤሪያ ወደ ጣልያን በጋሊያ ሲያልፍ የኬልቴስን አንድያ ሴት ልጅ ጋላጤያ አግብቶ ጋላጤስን ወለደችለት ይባላል። የሄርኩሌስ ልጅ ጋላጤስ በጋሊያ ከነገሠ በኋላ ሄርኩሌስ የጣልያን ዙፋን ለሌላው ልጅ ቱስኩስ ትቶ ወደ ኢቤሪያ መንግሥት ተመለሠ። ይህ ቱስኩስ ለወንድሙ ለጋላጤስ ስጦታ እንዲሆን ሲኪልያ ደሴት ሰጠው። ጋላጤስም ሰፈረኞች ወደዚያ ሲኪሊያ ወሰደ ይባላል።

አንዳንድ የድሮ ፈረንሳይኛ ደራስያን ነገሩን ስተው የዚህ ጋላጤስ ሰፈረኞች ደግሞ ሳርማትያንና አናቶሊያን ወረሩ፣ በአናቶሊያም ገላትያ የተባለውን ክፍላገር መሠረቱ ይላሉ። ነገር ግን ኬልቶች ወደ ሳርማትያና ወደ ገላትያ የወረሩት ከዚህ በኋላ በ300 ዓክልበ. አካባቢ እንደ ነበር ይታወቃል። «ገላትያ» አገር በአናቶሊያ በዚያን ጊዜ ስሙን ያገኘው ኬልቶቹ በግሪክኛ «ጋላቴስ» ስለ ተባሉ ነው።

በሌሎች ታሪኮች ዘንድ ሄርኩሌስ እራሱ ለጥቂት አመት ከኬልቴስ ቀጥሎና ከልጁ ጋላጤስ በፊት «ኦግሚዮስ» ተብሎ በጋሊያ ነገሠ።

«የበልጅግ ክፍላገር ጥንታዊና ዘመናዊ ታሪክ» (1798 ዓ.ም. ተጽፎ) ስለ ጋላጠስ አስተዳደር ዝርዝር ያቀርባል። ሴት ልጅ እድሜዋ ፳ ዓመት ሲሆን በገዛ ፈቃድዋ ባልዋን እንድትመርጥ፣ ምርጫዋን የሙሉ ጋን ውሃ ለርሱ በመስጠትዋ እንድታመልከት ደነገገ። ባልዋም ቢሞት ሚስት ግማሽ ነዋዩን እንድትቀበል ደነገገ። ደግሞ የአገሩን ሥርዓተ ንግሥ መሠረተ፤ ንጉሡን በጋሻ ላይ እንዲያንሡት ልዩ ምልክታቸው ጦር እንዲሰጡት የሚል ነበር።[1]

ቀዳሚው
ኬልቴስ
ኬልቲካ / ጋሊያ ንጉሥ
1952-1909 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ናርቦን
  1. ^ 1798 ዓም የቤልጅግ ታሪክ