Jump to content

ጋያነሸጎዋ

ከውክፔዲያ

ጋያነሸጎዋ ወይም ካያነረኮዋታላቅ ሕገ ሰላም») የሆደነሾኒ (ኢሮኳ) ኗሪ ብሔሮች የተባበሩበት ሕገ መንግሥት ነው። በተለመደው ታሪክ ዘንድ፣ በ1100 ዓ.ም. ገደማ አለቃው ደጋናዊዳ በዛሬው ኒው ዮርክ ክፍላገር የሚኖሩትን 5 ብሔሮች በዚህ ሕግ አባበራቸው። 5ቱ ብሔሮችም በስም ካንየንከሃካ (ሞሃውክ)፣ ኦንዮታአካ (ኦናይዳ)፣ ኦኖኝዳጌጋ (ኦኖንዳጋ)፣ ጋዮጎሆኖ (ካዩጋ)፣ እና ኦኖንዶዋጋ (ሰነካ) ናቸው። በኋላም በ1706 ዓ.ም. ስድስተኛ ብሔር ተስከሮራ ተጨመረላቸው።

የሆደናሾኒ ብሔራዊ ባንዲራ ከዋምፖም (ዶቃ) የተሠራው የጥድ ምልክትና የሕገ መንግሥት ምሳሌ ነው።

አሜሪካ ኗሪዎች ኅብረተሠብ እንደ አውሮፓውያን ኅብረተሠብ ፊዎዳል አገዛዝ ሳይሆን ዴሞክራስያዊ (ሕዝባዊ) ነበረ። ስለዚህ ይህ ሕግ በ1780 ዓ.ም. በተደረገው በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ላይ ሰፊ ተጽእኖ ነበረው። ለዚህም የሚቀርበው ታሪካዊ ሰነድ የላንካስተር ውል (1738 ዓም) ነው።

ይህ ሕግ የተመዘገበው በተጻፈ ቋንቋ ሳይሆን በዋምፖም (ትንንሽ የዛጎል ዶቃዎች) አማካይነት ይታወስና ይወረስ ነበር። በኋላ ዘመን ነው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ። ሕጉ በ117 አንቀጾች ይከፈላል። የተባበሩት ሆደነሾኒ ብሔሮች የጥድ ዛፍ ምሳሌ ናቸው። እያንዳንዱ ጎሣ ወይም ነገድ በመንግሥት አመራር የተወሰነ ሚና ያጫውታል።

ምሳሌ አንቀጾች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  • አንቀጽ 37፤ ስለ ጦር አለቆቹ፦ ለያንዳንዱ ብሔር አንድ የጦር አለቃ ይኖራል፣ የጦር አለቆች ተግባር መልዕክት ወደ ማህበር አለቃዎቻቸው ለመውሰድና በአደጋ ጊዜ መሣርያ ለመያዝ ነው። በማኅበሩ ጉባኤ ሂደት ውስጥ እነሱ አይካፈሉም፤ ነገር ግን ሂደቱን ተመልክተው የማህበር አለቃ ስኅተት ቢሠራ ኖሮ የጦር አለቆች የሕዝቡን አቤቱታ ይቀበሉ፤ የሴቶችንም ማስጠንቀቂያ ያደርሱለት። መልእክት ወደ ማኅበር አለቃቸው ለማቅረብ የፈለጉት ሰዎች ሁሉ በብሔራቸው ጦር አለቃ በኩል ነው የሚያቀርቡት። የሕዝቡ ጉዳዮች፣ ጥያቄዎችና ሀሣቦች በማኅበሩ ጉባኤ ፊት ማቅረብ ምንጊዜ የርሱ ተግባር ነው።
  • አንቀጽ 101፤ ስለ ምስጋና በዓላት፦ ለምስጋና በዓላት የተወሰኑት አስተዳዳሪዎች ተግባር ለባዓሎች የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ነው። የታወቁት ምስጋና በዓላት እንዲህ ናቸው፤ የበጋ ምስጋና፣ የስኳር ዛፍ ምስጋና፣ የቀይ እንጆሪ ምስጋና፣ የእንጆሪ ምስጋና፣ የበቆሎ መዝራት ምስጋና፣ የበቆሎ ኩትኮታ ምስጋና፣ የአረንጓዴ በቆሎ ትንሽ በዓል፣ የበሠለ በቆሎ ትልቅ በዓል፣ እና የፍጹም መከር ምስጋና ናቸው።
  • አንቀጽ 107፤ የመኖሪያ ግልነት ስለ መጠበቅ። የመኖርያ ባለቤት ወይም ኗሪ እቤት አለመገኘቱን የሚያሳወቅ ልዩ ምልክት ለ5ቱ ብሔሮች ሕዝብ ሁሉ ተከብሮ ይኖራል። ይህንንም የሚያሳውቀው ምልክት ዘንበል ያለ ወይም የተደገፈ ምሰሶ ወይም ምርኩዝ ይሆናል። እንዲህ ያለ ምልክት ያየ ሰው ሁሉ እቤቱ ውስጥ የመኖር መብት ከሌለው ወዲዚያው ቤት በቀን ወይም በሌሊት መግባት አይፈቀድም፤ ነገር ግን እስከሚቻል ድረስ ተራቅቆ ጉዳዮቹን ይፈጽም።

የውጭ መያያዣዎች (በእንግሊዝኛ)

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]