ጌታመሳይ አበበ

ከውክፔዲያ

ጌታመሳይ አበበ ታዋቂ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዘፋኝ ሲሆን ያለው የጠለቀ የማሲንቆ ዕውቀትና ችሎታው የማሲንቆው ሊቅ የሚል መጠሪያ አጎናፅፎታል። ጌታመሳይ አበበ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በአፍሪቃ በመዟዟር የኢትዮጵያን የባሕል ጨዋታ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያንፀባረቀ አንጋፋ የባሕል ተጫዎች ነው።

የሕይወት ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጌታመሳይ አበበ በአሩሲ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ አልባሶ በተባለ ቦታ በ፲፱፻፴፭ ዓ.ም. ተወለደ። ባለማሲንቆው ጌታመሳይ በሙያው ተለክፎ እጁን ለሙዚቃ የሰጠው ገና አንድ ፍሬ ልጅ ሳለ በሚኖርበት ሠፈር አካባቢ ሠርግና ክርስትና ሲኖር ማሲንቆ ይጫወቱ የነበሩትን በማየት ልቡ እጅግ ከተነሳ በኋላ ነው። ጌታመሳይ በግል ጥረቱ እንጨት እያጎበጠ የፈረስ ጭራ በማሰር ማሲንቆ መጫወት በመቻሉ ስሜቱ ወደዚህ ሙያ እንዲያመራ አስገደደው። ጌታመሳይ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ከሀገር ቤት መጥቶ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ልምምድ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በአንዳንድ ተፅዕኖዎች ምክንያት ቲያትር ቤቱን ተሰናበተ። በ፲፱፻፶፮ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል የኢትዮጵያ ኦርኬስትራ እንደተቋቋመ ተቀጥሮ በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል። በ፲፱፻፷ ዓ.ም. ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተዛወረ።

ጌታመሳይ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ከዘፋኝነት በተጨማሪም የቲያትር ሙያን ሊማር በመቻሉ ከአስር በላይ በሚሆኑ ቲያትሮች ከዕውቅ አርቲስቶች ጋር በመሆን ሠርቷል። ለዚህም ማስረጃ ሊሆኑ የሚችሉት በአቤ ጉበኛ «የደካሞች ወጥመድ»፣ በብርሃኑ ዘሪሁን «የለውጥ አርበኞች» እና በጌታቸው አብዲ «ስንት አየሁ» ከብዙ ትቂቶቹ ናቸው።

የሥራዎች ዝርዝር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጌታመሳይ እስካሁን ከሁለት መቶ የማያንሱ ዜማዎችን ተጫውቷል። ከእነዚህም ውስጥ «ሆብዬ እመጣለሁ»፣ «ሀገር መውደድ ማለት»፣ «ዳይመኔ»፣ «የመኖሪያ ቤቴ» እና «የኔ ሀያል» የተባሉት ዜማዎች በአድማጭ ዘንድ ያላቸው ተወዳጅነት ከፍተኛ ነው።

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]