ጥላሁን ገሠሠ
ጥላሁን ገሠሠ | |
---|---|
መረጃ | |
የትውልድ ስም | ጥላሁን ገሠሠ ንጉሤ |
የልደት ቀን | መስከረም 19 ቀን 1933 ዓ.ም. |
ያረፉበት ቀን | ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. |
የሥራ ዘመን | ከ1948 - 2001 ዓ.ም. |
ክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ (መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፴፫ እስከ ፳፻፩ ዓ.ም.) ዝነኛ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ጀግና ነበር ።
ከእናቱ ከወ/ሮ ጌጤ ጉሩሙ እና ከአባቱ ከአቶ ገሠሠ ንጉሤ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጠመንጃ ያዢ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር የመስቀል ዕለት ተወለደ። እድሜው - 14 ዓመት እንደሆነ ከአያቱ ጋር እንዲኖር ወደ ወሊሶ ተወሰደ በዚያም በራስ ጎበና በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ጀመረ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍቅር እይሳየ ሄደ ። አያቱ ግን ትኩረቱን በሙሉ በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ይመክሩት ነበር። የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ የነበሩት ሱዳናዊው አቶ ሼዳድ የጥላሁንን የሙዚቃ ፍቅር በማየት ወደ ሱዳን እንዲሄድና በዚያም ሙዚቃ እንዲያጠና ይመክሩት ነበር። ጥላሁን ወደ ሱዳን ባይሄድም ምክራቸውን ግን ትልቅ ቦታ ስጥቶት ነበር። ከ[19[ሀገር ፍቅር ቲያትር]] ወ/ሮ ንጋትዋ ከልካይ እና አቶ ኢዮኤል ዮሃንስ ሌሎችም የሃገር ፍቅር ተዋንያን በትምህርት ቤታቸው ትርኢት ሊያሳዩ በመጡ ጊዜ ይህን እድል በመጠቀም ጥላሁን ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር ከአቶ ኢዮኤል ጋር ባደረገው ውይይት በሙዚቃ መግፋት ከፈለገ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለበት መከሩት። ጥላሁን ትምህርቱን አቋርጦ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አቀና። ኩብለላውን በእግር የጀመረው ለአያቱ ሳይነግር ስለነበር ከቤት ሲጠፋ አያቱ ለአጎቱ ሁኔታውን በመንገር ጥላሁንን ይጠብቁ ጀመር። ጥላሁንም የአሥራ አምስት ኪ/ሜ መንገዱን ጨርሶ ቱሉ ቦሎ ደረሰ ከዚያም ከአክስቱ ከወ/ሮ ተመኔ ባንቱ ቤት አድሮ ወደመጣበት ወደ ወሊሶ አያቱ ዘንድ ተይዞ ተመለሰ ። በሙዚቃ ፍቅር በጣም የተቃጠለው ጥላሁን አያቱ ቤት አንድ ቀን ብቻ በማደር ጉዞውን እንደገና ወደ አዲስ አበባ አቀና በዚህ ጊዜ ግን በጭነት መኪና ላይ በመንጠልጠል ነበር። ጥላሁን አዲስ አበባ እንደገባ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ። በዚያም ጥቂት አመታት ከሰራ በኋላ ወደ ክብር ዘበኛ ባንድ በመቀላቀል ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን በቃ። ሆኖም በ ፲፱፻፶፫ ዓ/ም "የታሕሣስ ግርግር"ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር ። ለጥቂት ጊዜም ታስሮ ተፈትቷል። ከዚያም ወደ ቀድሞው ሀገር ፍቅር በመመለስ ተወዳጅና ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። ግርማዊ ቀዳማዊ፡ኃይለ፡ሥላሴ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤትን በጎበኙበት ጊዜ ሦስት ጊዜ ወጥቶ ዘፍኗል ንጉሠ ነገሥቱም "ጥሩ ድምጽ አለህ፣ እንዳታበላሸው" የሚል አስተያየትም እንደሰጡት ይነገራል ። የጥላሁን ብዙዎቹ ስራዎቹ የአማርኛ ዘፈኖች ሲሆኑ የተወሰኑ ዘፈኖችን ደግሞ በኦሮምኛ እና በሱዳንኛ ዘፍኗል። ጥላሁን ለኢትዮጲያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት በቅቷል ሌላም ህይወቱን በሙሉ ለሙዚቃ በማበርከቱ ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና የብዙህን መገናኛ ሽልማት ድርጅት «የሙሉ ዘመን» ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። ክብር ለዶክተር ጥላሁን ገሰሰ
ጥላሁን ባደረበት የስኳር በሽታ የትንሳዔ ዕለት ሚያዝያ ፲፩ ቀን፣ ፳፻፩ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
- "ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ
- ይህ ነው የሞትኩኝ ለት የኔ ማስታወሻ
- ውበቷን ሳሞግስ የለምለም ሃገሬን
- ማንም አይዘነጋም በጩሀት መኖሬን
- ዜማ እንጉርጉሬም የግሌ ቅላጼ
- ተቀርጾ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ
- ያስቀየምኩት ቢኖር የጠላኝ በቁሜ
- ድምጼን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አጽሜ
- እኔን ለበደሉኝ ሰርዣለሁ ቂሜን
- በኔም የከፋችሁ ይቅር በሉት አጽሜን"