Jump to content

ፉሢ

ከውክፔዲያ
ፉሢ እና ኢ ቺንግ

ፉሢ (ቻይንኛ፦ 伏羲) ወይም ፓውሢ (庖牺) በቻይና አፈ ታሪክ ዘንድ በጥንታዊ ዘመን መጀመርያው ንጉሥ ነበረ። መጻፍንና ማጥመድን እንደ ፈጠረ ይባላል።

ፉሢ የተወለደው በቢጫ ወንዝ ሸለቆ በቸንግጂ (ምናልባት የአሁን ላንትየን ወይም ትየንሽዌ) ይባላል። በቻይናዊ ትውፊት ዘንድ፣ ፉሢና እህቱ ኑዋ ብቻቸው ከማየ አይኅ አመለጡ። ከዚያ ወደ ኩንሉን ተራራ ሄደው ምልክት ከሰማያት እንዲታይላቸው ጸለዩ። ከተፈቀደላቸው በኋላ ተዳሩና እነርሱ የሰው ልጆችን ሁሉ ወለዱ። በተጨማሪ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እንዲበዛ፣ ፉሢና ኑዋ ሌሎችን ነገዶች ከሸክላ ይሠራሉ። ከዚያ ፉሢ በልጆቻቸው ላይ ለ115 ወይም 116 ዓመታት እንደ ንጉሣቸው ይገዛል። በተለመደው አቆጣጠር ይህ በ28ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ያሕል ይሆን ነበር። በመሞቱ እድሜው 197 ዓመት ሲሆን መቃብሩ እስከ ዛሬ ድረስ በኋያንግ መገኘቱ ይባላል።

ኑዋ እና ፉሢ በልማዳዊ ስዕል
«በመጀመርያው ኅብረተሠብ ገና አልኖረም። ሰዎች እናቶቻቸውን ብቻ እንጂ አባቶቻቸውን አላወቁም ነበር። ሲራቡ ምግብን ፈለጉ፣ ሲጠገቡም ቀሪውን ጣሉ። ሥጋቸውን ሙሉ ከነቆዳው ከነጽጉሩ ከነደሙም ይበሉ ነበር፤ በቆዳ ወይም በመቃ ይለበሱ ነበር። ያንጊዜ ፉሢ መጣና አሻቅቦ የሰማይን ምልክቶችን አሰላሰለ፤ በታችም የምድርን ድርጊቶች አሰላሰለ። ባልንና ሚስትን አዋኸደ፤ የለውጥ 5 ደርጃዎችን አስተዳደረ፤ የሰው ልጆች ሕግጋትንም አጸና። ስምንቱም ባለ 3 ምልክቶች ፈጠረ፣ ዓለሙን ለመግዛት።» -- ባን ጉ፣ ባይሁ ቶንግዪ

ከዚህ በላይ ፉሢ ማብሰልን፣ በመርበብ አሣን ማጥመድ፣ እና በብረት መሣርያ ማደን እንደ ፈጠረ ይባላል። የትዳርና የመስዋዕት ሥርዓቶችን አስቆመ። ባለ 3 ምልክቶች (ትራይግራም) የሚሠሩትን ኢ ቺንግ ፈጠረ። ደግሞ ጉ ጪን የተባለውን የሙዚቃ መሣርያ እንዳደረጀ ተብሏል።