ፊልጶስ አረባዊ

ከውክፔዲያ
የሮሜ ንጉሥ ፊልጶስ ምስል

ፊልጶስ አረባዊ236 እስከ 241 ዓ.ም. ድረስ የሮማ መንግሥት ንጉሠ ነገስት ነበረ።

«አረባዊ» የተባለው ቤተሠቦቹ ከአረቢያ ስለመጡ ነበር። እሱ በ196 ዓ.ም. አካባቢ በሶርያ አውራጃ ተወለደ።

በሮሜ ንጉሥ አሌክሳንድር ሴቬሩስ ዘመን ፊልጶስ የፕራይቶርያን ጠባቂዎች (የንጉሡ ልዩ ዘበኞች ክፍል) አባል ሆነ። በኋለኛውም ንጉሥ በ3ኛ ጎርዲያኖስ ዘመን በ235 ዓ.ም. ፊልጶስ የዘበኞች አለቃ ሆነ። ይኸው ንጉሥ ግን ልጅ ስለ ሆነ፣ ፊልጶስ እንደራሴ የሚመስል ሚና አጫወተ። ከዚህ ትንሽ በኋላ ጎርድያኖስ ሞተና ፊልጶስ በዚያን ጊዜ ንጉሥ ሆነ። በዚያው ጊዜ የሮማ ነገሥታት ሁሉ የተነሡ በሠራዊት ፈቃድነት ነበርና።

ንጉሥ ፊልጶስ ሰላም ከፋርስ መንግሥት ጋር ካዋጀ በኋላ በጀርመናዊ ጎሣዎች ላይ ዘመቻ አደረገ። በየጊዜው ሠራዊቶቹ ጣውንት ንጉሥ በማቆም ያምጹ ነበር፤ ነገር ግን ሳይከናውኑ ቆይተዋል። በ240 ዓ.ም. የሮሜ ሺህኛው አመት በዓል አፈጸመ። ለዚህ በዓል አንድ ሺህ የጨዋታ ወታደሮች (gladiator) እና ብዙ እንስሶች መስዋዕት ሆኑ። በሚከተለው አመት ግን አንዱ ሠራዊት አለቃቸውን ዴቅዮስ ንጉሥ ሆኖ ስላቆሙት፣ ፊልጶስ ከነሱ ጋር ለመታገል ሂዶ ተገደለና ዴቅዮስ የዛኔ ንጉሥ ሆነ።

በኋለኛው ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘንድ፣ ንጉሥ ፊልጶስ አንድ ጊዜ ፋሲካ በዓል ለማስታወስ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ። ሳይገባም ጳጳሱ ንስሐ እንዲገባ አደረጉት ተባለ። ከዚህ በላይ በየወቅቱ በክርስትያኖች ላይ የተካሄዱት እልቂቶች በፊልጶስ ዘመን የተቋረጡ ይመስላል። ስለዚህ ይህ ንጉሥ ምናልባት የሮማ የመጀመርያው ክርስቲያን ንጉሥ ባይሆንም እንኳን የክርስትና ተቆርቋሪ ሊባል ይቻላል ባዮች አሉ። ሆኖም በዘመኑ በወጡ መሐለቆች መሠረት እምነቱን ከሮማ አረመኔ ሃይማኖት መቸም የቀየረ አይመስልም።