Jump to content

ፍዮዶር ዶስቶየቭስኪ

ከውክፔዲያ

ፍዮዶር ሚኸየሎቪች ዶስቶየቭስኪሩስያ ምርጥ ደራስያን መካከል የሚቆጠር እና በአለም የሥነ-ጽሁፍ መድረክ አሻራውን ትቶ ለማለፍ የቻለ ሰው ነው። ከሱ በኋላ የተነሰ የአውሮጳ ጸሃፍያን፣ ፈላስፋወችና ስነ ልቡና ተመራማሪወች፣ ከፍሬድሪች ኒሺ እስከ ሲግመን ፍሮይድ፣ ከፍራንዝ ካፍካ እስከ ዣን ፖል ሳርት ድረስ ጉልህ የስነ-ሰብእ እና የስነ-ልቦና መርማሪነቱን መስክረውለታል።

ዶስቶየቭስኪ በሩስያ ዋና ከተማ ሞስኮ (መስኮብ) ውስጥ እ.ኤ.አ በኦክቶበር 30፣ 1821 ተወለደ። አባቱ ቀድሞ የጦር ሰራዊቱ ሃኪም የነበረ ሲሆን በጣም ጠጪ እና ጢሰኞቹም ላይ ግፍን ያበዛ እንደነበር ይወሳል። ይህም በመሆኑ ይመስላል በገዛ ጭሰኞቹ እጅ ህይወቱ ሊያልፍ የበቃው።

ዶስቶየቭስኪ በ1837 ዓ.ም በቅዱስ ፒተርስበርግ የጦር ምህንድስና አካዳሚ ተመዝግቦ ትምህርቱን በመከታተል በመኮንንነት ተመርቋል። አንድ አመት ያህል በመንግሥት ሥራ ላይ ከቆየ በኋላ ሙሉ ግዜውን በስነ-ጽሁፍ ላይ ለማዋል ሲል ከሥራው ተሰናብቷል።

የበኩር ድርሰቱ የሆነው "Poor Folk" በ1846 ሲታተም ወዲያው አድናቆትን ቢያስገኝለትም ብዙም ሳይቆይ በ1849 ዓ.ም የሩስያውን ንጉሥ ዛር ኒኮላስ ቀዳማዊን በመቃወም ወንጀል ተከሶ ወደ ዘብጥያ በመውረዱ የሥነ-ጽሁፍ ሥራው ሊቋረጥ በቅቷል። በተከሰሰበትም ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በጥይት ተደብድቦ ሊገደል ወደ መግደያው ከተወሰደ በኋላ ፍርዱ ተለውጦለት ወደ ሳይቤርያ በግዞት እንዲሄድ ተደርጓል። ኦምስክ በተባለች የሳይቤርያ ከተማ ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር ለ4 ዓመታት ያህል ታስሮ በሌላ የሳይቤርያ ግዛት እንዲሁ ለተጨማሪ 6 ዓመታት በውትድርና እንዲያገለግል ከተደረገ በኋላ ተለቆ ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ ለመመለስ በቅቷል። ከሞት አፋፍ ያመለጠበት ሁኔታ በስነ-ልቦናው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በስነ-ጽሁፉም ላይ የተንጸባረቀ ሲሆን "The Idiot" የተሰኘው ድርሰቱ በዚሁ ላይ የተመሰረተ ነበር።

ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተመለሰ በኋላ የበፊት ተወዳጅነቱን ለማስመለስ አፍታም አልወሰደበት። በ1862 ያሳተመው "Notes from the Dead House"፣ እንዲሁም ከሁለት አመት በኋላ ያሳተመው "Notes from the Underground" በጣም አድናቆትን ያተረፉ የሥነ-ጽሁፍ ትርፋቶቹ ሲሆኑ በመቀጠልም "Crime and Punishment" የተሰኘውን ልብ-ወለድ ድርሰቱን በ1866፣ "The Gambler"ን በ1867፣ "The Idiot"ን በ1869፣ እንዲሁም "Demons"ን በ1872 አሳትሟል። የስራዎቹ ሁሉ ቁንጮ የሆነው "The Brothers Karamazov" በ1880 ታትሟል። በተለይ "The Gambler" የተሰኘውን ድርሰቱን በ26 ቀናት ውስጥ ጽፎ እንዳጠናቀቀ ይነገራል።

በስነ-ጽሁፉ ስኬትን በስኬት ላይ የደረበው ዶስቶየቭስኪ በግል ህይወቱ ግን ደስታን ለማጣጣም አልታደለም። ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው የሚጥል በሽታ፣ በትዳሩ ደስታን ማጣት፣ እንዲሁም የገንዘብ እጦት (ቁማርተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳብሎ) ህይወቱን ስቆቃ የተመላው አድርጎበታል።

በህይወቱ የመጨረሻ ዘመናት ወደ ወግ አጥባቂነት እና ሃይማኖተኛነት እያዘነበለ ይሄደው ዶስቶየቭስኪ የኑባሬ ፍልስፍና (Existentialism) ቀደምት ከሆኑት ውስጥ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ። ዶስቶየቭስኪ ህይወቱ በ1882 ስታልፍ ከ52000 በላይ ሰዎች በቀብሩ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው የመጨረሻውን ስንብት አድርገውለታል። አጽሙም በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የአሌክሳንደር ኔቭስኪ ገዳም ውስጥ አርፏል።

ዋነኛ የድርሰት ስራዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

 • Poor Folk) (1846)
 • The Double: A Petersburg Poem (1846)
 • Netochka Nezvanova (1849)
 • The Village of Stepanchikovo or The Friend of the Family (1859)
 • The Insulted and Humiliated (1861)
 • The House of the Dead (1860)
 • A Nasty Story (1862)
 • Notes from Underground or Letters from the Underworld (1864)
 • Crime and Punishment (1866)
 • The Gambler (1867)
 • The Idiot (1868)
 • The Possessed, also known as Demons or The Devils (1872)
 • The Raw Youth or The Adolescent (1875)
 • The Brothers Karamazov (1880)
 • A Writer's Diary (1873-1881)

አጫጭር ታሪኮች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

 • White Nights (1848)
 • A Christmas Tree and a Wedding (1848)
 • An Honest Thief (1848)
 • The Peasant Marey (1876)
 • The Dream of a Ridiculous Man (1877)
 • A Gentle Creature, sometimes translated as The Meek Girl (1876)
 • A Weak Heart
 • The Eternal Husband