Jump to content

ፐርል በክ

ከውክፔዲያ

ፐርል በክ በስነ-ጽሁፍ የኖቤል ተሸላሚ (1938) ለመሆን የበቃች አሜሪካዊት ደራሲ ናት። በክ ጁን 26 ቀን 1982 ዓ.ም በምእራብ ቨርጂኒያ ሂልዝቦሮ በተባለ ቦታ ተወለደች። ወላጆቿ ፕሬስብቴርያዊ ሚሲዮኖች የነበሩ ሲሆን ብዙውን የሚሲዮን ስራቸውን በቻይና ነው ያሳለፉት። በዚሁ የተነሳ በክ ከልጅነቷ ጀምሮ እንግሊዝኛን ብቻ ሳይሆን ቻይንኛንም አቀላጥፋ ትናገር ነበር።

ትምህርቷን በ1914 እንዳጠናቀቀች ወደ ቻይና ነው ያቀናችው። በ1915 የወደፊት ባሏ ከሚሆነውን ከጆን ሎሲንግ በክ ጋር ተገናነች። በ1917 ጋብቻቸውን ከፈጸሙ በኋላ ኑሯቸውን ናንሹ በተባለችው የገጠራማዋ አንህዌ ግዛት አደረጉ። በዚሁ ቆይታዋ ነው ወደፊት የሥነ-ጽሁፍ ስራዋ ጉልላት ለመሆን የበቃውን ስሙር መሬት (The Good Earth) ለተባለው መጽሃፏ የሚሆናትን መረጃ የሰበሰበችው።

በክ ጽሁፎቿን ማሳተም የጀመረችው ከ1920ዎቹ ጀምራ ሲሆን አጫጭር ስራዎቿ "The Nation"፣ "The Chinese Recorder"፣ "Asia" እና "The Atlantic Monthly" በተሰኙ መጽሄቶች ታትመውላታል። የመጀመሪያው ወጥ ልብ-ወለድ ድርሰቷ (East Wind, West Wind) በ1930 በጆን ዴይ ኩባንያ ታትሟል። የጆን ዴይ ኩባንያ አሳታሚ የነበረው ሪቻርድ ዋልሽ ኋላ ላይ (1935) የፐርል በክ ሁለተኛ ባሏ ለመሆን በቅቷል።

በ1931 ጆን ዴይ ኩባንያ የፐርል በክን ሁለተኛ ወጥ ልብ-ወለድ ድርስት የሆነውን ስሙር መሬትን አሳተመ። ይኸው ሥራዋ በተከታታይ በ1931 እና በ1932 ዓ.ም በገበያ ላይ አንደኛ ተፈላጊ ሆኖ ለመዝለቅ የቻለ ሲሆን ለሷም በ1935 ዓ.ም የፑሊትዘር ሽልማት እና የሃዌልስ ሜዳልያ አስገኝቶላታል። ስሙር መሬት በ1937 ዓ.ም በኤም.ጂ.ኤም አማካይነት በፊልም መልክ ተቀናብሮ ለተመልካች ቀርቧል። ከዛ በተከታታይ ሌሎች ድርሰቶችን ለአንባቢ አቅርባለች። በክ በ1938 ዓ.ም በስነ-ጽሁፍ የኖቤል ሽልማትን በመቀበል የመጀመሪያዋ (ሴት) አሜሪካዊት ሆናለች።

ፐርል በክ በ1973 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ ከ70 በላይ ስራዎቿ ታትመውላታል። መቃብሯም ፔንሲልቬንያ ውስጥ በክስ በተባለው ቀበሌ ይገኛል።