Jump to content

1 ቴቲ

ከውክፔዲያ
«ሖር-አሐ» የሚታንበው ሰረኽ

ቴቲቶሪኖ ፈርዖኖች ዝርዝርና በአቢዶስ ፈርዖኖች ዝርዝር ዘንድ የግብጽ የቀድሞ ዘመነ መንግሥት ፪ኛው ፈርዖን ነበረ። በነዚህ ዝርዝሮች ዘንድ የ«ሜኒ» (ሜኒስ) ተከታይ ይባላል። በማኔጦን ዝርዝር ዘንድ ደግሞ በግሪክኛ የሜኒስ ልጅና ተከታይ ስም «አጦጢስ» ተብሎ ይጻፋል። ይህ ሜኒስ የመላው ግብጽ መንግሥት መጀመርያ ንጉሥ ሲሆን መታወቂያው በሥነ ቅርስሰረኽ ስም ሃይሮግሊፉ «ናርመር» ከሚታነበው ጋር አንድላይ እንደ ሆነ ሁሉ፣ እንዲሁም የናርመር ተከታይ ስም ሃይሮግሊፍ አጠራር በግምት «ሖር-አሐ» ወይም «አሐ» ታንቧል። ከሔሩ (ወይም ሆሩስ፣ ሖር) ወገን መሆኑ በጭላት ምልክት ይታያል።

የመኳያ ሠሌዳ መሥራት በዚሁ ዘመን ከበፊቱ መጠን እንደ ቀረ ይመስላል። የእናቱ ስም ኔትሆተፕ እና የዋና ሚስቱ ስም በነሪብ ከሥነ ቅርስ ታውቀዋል። ሁለተኛ ሚስቱ ኸንትሃፕ ደግሞ የተከታዩ የጀር እናት ነበረች።

የ«አሐ» ትርዒት በዝሆን ጥርስ ተቀርጾ

ማኔጦን እንደሚለን ይህ «አጦጢስ» ቤተ መንግሥት በሜምፊስ ሠራ፤ ከ«አሐ»ም ዘመን የሆነ መስተባ በዚያ ይታወቃል። ከዚህ በላይ አጦጢስ ጽሕፈት አስለማና የሥነ አካል መጽሐፍ እንደ ጻፈ ማኔጦን ይለናል። በሖር-አሐም ቅርሶች ላይ የድምጽ ምልክቶች (እንደ ፊደል) ጥቅም ተስፋፍቶ ነበር። በተጨማሪ የጥንታዊ ዘመን ጣኦት ጦጥ (ግብጽኛ፦ ጀሑቲ) የጽሕፈት፣ የሕክምናና የእውቀት አባት ስለ ተባለ፣ አምልኮቱ ምናልባት ከዚህ ንጉሥ አጦጢስ ትዝታ እንደ ደረሰ የሚል አስተሳሰብ ይኖራል[1]። «ጣኦት» የሚለው ግዕዝ ቃል (ሐሣዊ አምላክ ወይም ምስል) እራሱ ከዚህ «ጦት» ስም እንደ ደረሠ ይቻላል።

«ሖር-አሐ ደቂቀ ሴት አሸንፏል።»

ይህ ፈርዖን በአባይ ወንዝ ሸለቆ ዙሪያ በተገኙት ብሔሮች ላይ በተለይም በሴት ወገኖች ላይ እንደ ዘመተ ግልጽ ነው።

የፓሌርሞ ድንጊያ በተባለው ዜና መዋዕል ላይ የመጀመርያው ሁለት ፈርዖኖች ዘመናት በከፊል ሊታዩ ይችላሉ። ስሞቻቸው ግን ጠፍተዋል። በመጀመርያው ፈርዖን መጨረሻ ዓመት «፮ ወሮችና ፯ ቀኖች» ሲል ይህ በግብጻውያን አቆጣጠር ናርመር የተገደለበት ቀን ይሆናል። በሚከተለው ሳጥን «፬ ወሮችና ፲፫ ቀኖች» ሲል ይህ ተከታዩ ቴቲ ዘውድ የተጫነበት ቀን ይሆናል። ቀዳሚው ካረፈ አሥር ወሮች በኋለ ዘውዱ ተጫነው ማለት ነው።

በግብጽ አፈ ታሪክ «የሔሩና የሴት ክርክሮች» በሚባል ትውፊት ዘንድ፣ ከኦሲሪስ ዕረፍት በኋላ ወንድሙ ሴትና ልጁ ሔሩ የኦሲሪስን መንግሥት ለመውረስ ለሁለቱ ይግባኝ ስለ ነበራቸው፣ በአማልክት ጉባኤ ፊት ቀረቡ። «የአማልክት እናት» ኔት እና ጦት በተለይ በዚህ ጉባኤ ዋናዎቹ ናቸው። ከ፹ ዓመታት በኋላ መላውን ግብጽ ለሔሩ በብያኔያቸው ሰጡት።

ከፓሌርሞ ድንጊያ ምስክር ጋር ሲነጻጽር፣ ይህ አፈ ታሪክ ማለት የግብጽ ሁለተኛ ፈርዖን ቴቲ የሔሩ ወገን ወኪል ሆኖ በሴት ወገን ዕጩ ላይ ከ፲ ወሮች በኋላ በጉባኤ በእናቱ ኔትሆተፕ እርዳታ ለዙፋኑ እንደ ተመረጠ ሊሆን ይችላል። በአፈ ታሪክ ፲ ወሮቹ ግን ፹ ዓመታት ሆኑ። በፓሌርሞ ዜና መዋዕል ከዚህ ቦታ በስተቀር ከሁለት ዘመናት መካከል የብዙ ወሮች ልዩነት አይመለከትም።

የቴቲ («ሖር-አሐ») እና የሚስቶቹ መቃብሮች ከናርመር መቃብር አጠገብ ተገኝተዋል። ከፈርዖኑ ጋራ 36 ሎሌዎች አብረው ተቀበሩ (መስዋዕት ሆነው)።

ቀዳሚው
ናርመር (ሜኒስ)
ግብፅ ሁሉ ፈርዖን
3089-3080 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ጀር
  1. ^ William Palmer, Egyptian Chronicles Vol I p. 322.