3 ሶበክሆተፕ
==
ሶበክሆተፕ ሰኸምሬ ሰዋጅታዊ | |
---|---|
3 ሶበክሆተፕ ጣኦትን ሲያመልክ | |
የግብጽ ፈርዖን | |
ግዛት | 1741-1701 ዓክልበ. ግ. |
ቀዳሚ | ሴት መሪብሬ |
ተከታይ | 1 ነፈርሆተፕ |
ባለቤት | ሰነብኸናስ፣ ነኒ |
ሥርወ-መንግሥት | 13ኛው ሥርወ መንግሥት |
አባት | መንቱሆተፕ |
==
ሶበክሆተፕ ሰኸምሬሰዋጅታዊ ግብጽ በ2ኛው ጨለማ ዘመን (13ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ1741 እስከ 1701 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የሴት መሪብሬ ተከታይ ነበረ።
በቶሪኖ ቀኖና ዘንድ ሶበክሆተፕ ሰኸምሬሰዋጅታዊ ለ፬ ዓመት ብቻ ሲለን ለእርሱ ብዙ ሐውልቶችና ቅርሶች ስለሚታወቁ ይህ ስኅተት ይመስላል። ከታወቁት ሐውልቶች መካከል አንዳንድ የቀዳሚው የሴት መሪብሬ ሐውልት ሆነው ነበር፣ ስሙ በመሪብሬ ስም ላይ ተቀረጸ። አንዳንድ የተገኘው ማህተም «የንጉሥ ሊቅ መኮንን ሶበክሆተፕ፣ የንጉሥ ሊቅ መኮንን መንቱሆተፕ ልጅ» አለበት። እንዲሁም ፓፒሩስ ቡላቅ 18 በተባለው ሰነድ «ሶበክሆተፕ» የሚባል «የንጉሥ ሊቅ መኮንን» አለ። የዚህ ፈርዖን አባት ስም «መንቱሆተፕ» መሆኑ ከብዙ ሌላ ጽላት ስለታወቀ፣ ሶበክሆተፕ ፈርዖን ከሆነ በፊት ይህን ወታደራዊ ማዕረግ እንደ ያዘ ይመስላል። ስለዚህ ሶበክሆተፕ በመንፈቅለ መንግሥት እንደ ተነሣ ይታስባል።
ሶበክሆተፕ ፈርዖን በሆነው ጊዜ፣ የፈርዖን ስም «ሰዋጅታዊ» (ሁለቱን አገራት የሚያፈራ) ወሰደ፤ ይህም ምናልባት የጌሤም ሥርወ መንግሥት በዚህ ጊዜ በመጨረሱ ሁለቱ አገራት (ላይኛና ታችኛ ግብጽ) ዳግመኛ ስለ ተወሐዱ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ዘመን በተጻፈ በአንዱ ሰነድ የባርዮች ዝርዝር አለ። በተለይ ትኩረት የሚስበው አንዲቱ ሲፓራ የተባለች ባርያ ስለ ተዘረዘረች። በብዙ ሊቃውንት አስተሳሰብ ይህች ሲፓራ በሙሴ ልደት ወቅት በኦሪት ዘፍጥረት 1:15 የተጠቀሰችው ዕብራዊት አዋላጅ ልትሆን ይቻላል፤ ሶበክሆተፕም የተወለዱት ዕብራውያን ወንዶች ወደ አባይ ወንዝ እንዲጣሉ ያዘዘ እርሱ ይሆናል ባዮች ናቸው። ይህም በመጽሐፈ ኩፋሌ ውስጥ ከተገኘው ዜና መዋዕል ጋር ልክ ይስማማል።
የሶበክሆተፕ ጨቲ (ጠቅላይ ሚኒስትር ያህል) ረሠነብ (የአንኹ ልጅ) ነበረ። በተረፈ የሶበክሆተፕ እናት ዩኸቲቡ ተባለች፣ ወንድሞቹም ስነብና ኻካው፤ እኅቱም ረኒሰነብ፣ ሚስቶቹ ሰነብኸናስና ነኒ ተባሉ። የነኒ ሴት ልጆች ዩኸቲቡ ፈንዲ እና ደደታኑቅ ነበሩ። በኩፋሌ እና በሌሎች ምንጮች ዘንድ ሙሴን ያዳነችው ግብጻዊት ልዕልት ተርሙት ተባለች።
ቀዳሚው ሴት መሪብሬ |
የግብፅ (ጤቤስ) ፈርዖን | ተከታይ 1 ነፈርሆተፕ |
- K.S.B. Ryholt: The Political Situation in Egypt during the Second Intermediate Period, c. 1800 – 1550 BC, Carsten Niebuhr Institute Publications, vol. 20. Copenhagen: Museum Tusculanum Press, 1997 (እንግሊዝኛ)