ናኮችታንክ
ናኮችታንክ በዛሬው ዋሺንግተን ዲሲ ሥፍራ ከ1660 ዓ.ም. አስቀድሞ የተገኙ ኗሪዎች ከተማና ጎሣ ነበር። አሁን በዋሺንግተን ያለው ፈሳሽ አናኮስቲያ ወንዝ ስም ከ«ናኮችታንክ» የመጣ ነው።
ባካባቢያቸው የኖሩት የፒስካታወይ ጎሣ ጓደኞች ነበሩ፤ ቋንቋቸውም የተዛመደ ቀበሌኛ ነበረ። ከፖቶማክ ወንዝ ማዶ በአሁኑ ስሜን ቭርጂኒያ የነበረው ዶግ ብሔር እንዲሁም በዘርም ሆነ በልሳን ዘመዶቻቸው ነበሩ።
ናኮችታንክ መጀመርያ በእንግላንድ አለቃና ዠብደኛ ጆን ስሚስ በ1600 ዓ.ም. በካርታ ተመዘገበ። ያንጊዜ በጀጐል (የተሳሉ እንጨቶች አጥር) ተከበበ፤ ፹ ጎበዞችና በጠቅላላው ፫፻ ሰዎች ይኖሩበት ነበር። ሩቅ ነገዶች እስከ ኢሮኳ ብሔሮች ድረስ (ዛሬ ኒው ዮርክ) በጣም የተወደደውን የቢቨር (ኣቆስጣን የመሰለ ዘራይጥ) ቆዳ ለመነገድ ወደ ናኮችታንክ ይመጡ ነበር። የ«ናኮችታንክ» ትርጉም እንዲህ «የንግድ ከተማ» ማለት ነበር።
በ1614 ዓ.ም. የኢንግላንድ አለቃ ሄንሪ ፍሊት ከናኮችታንክ ተወዳዳሪ ከፓታዎመክ ብሔር ጋር ተባብሮ፣ በናኮችታንክ ላይ አደጋ ጣለ፣ ከተማውን አቃጠለና 18 ኗሪዎች ገደለ። በሚከተለው ዓመት የናኮችታንክ ጎበዞች ፍሊትን ማረኩት፣ ለ፭ ዓመታት ያዙትና ቋንቋቸውን አስተማሩት። በ1620 ዓ.ም. ፍሊት አመለጠ፤ በ1624 ዓ.ም. ወደ ናኮችታንክ ተመልሶ ፰፻ የአቋስታ ቆዳዎች ገዛ።
በአሁኑ ጆርጅታውን፣ ዲሲ ሠፈር ሌላ «ቶሖጋ» የተባለ መንደር ነበራቸው። በ1660 ዓ.ም. ያሕል ብዙዎች በተስቦ ዓርፈው የተረፉት ናኮችታንክ ኗሪዎች ወደ አናኮስቲን ደሴት በፖቶማክ ወንዝ ውስጥ ሐዱ፤ ይህም አሁን ቲዮዶር ሮዘቨልት ደሴት ይባላል። ከዚያ በኋላ የጎሣው ቅሬታ ከፒስካታወይ ብሔር ጋራ አንድላይ ሄደ።
- Burr, Charles R. "A Brief History of Anacostia, Its Name, Origin, and Progress", Records of the Columbia Historical Society, 1920. (እንግሊዝኛ)
- Williams, Brett. "A River Runs Through Us," American Anthropologist, 103:2 (June 2001). (እንግሊዝኛ)