Jump to content

የሷሶን ግዛት

ከውክፔዲያ
የ20:31, 7 ኦክቶበር 2017 ዕትም (ከTil Eulenspiegel (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)
የሷሶን ግዛት፣ በ478 ዓ.ም.

የሷሶን ግዛት በስሜን ጋሊያ (የዛሬው ፈረንሳይ አገር) የተገኘና ከሮሜ መንግሥት ውድቀት (በ468 ዓ.ም.) በኋላ ትንሽ የቆየ የሮማውያን ግዛት ነበረ።

የሷሶን መንግሥት መነሻ የሮሜ ንጉሠ ነገሥት ማዮሪያኑስ449 ዓ.ም. አይጊዲዩስን የጋሊያ አውራጃ ዋና አለቃ እንዲሆን በሾሙበት ወቅት ሆነ።

5ኛው ክፍለ ዘመን የጀርመናውያን ብሔሮች ወደ ሮሜ ግዛት እየፈለሱ ነበር፣ በተለይም ቪዚጎቶች የተባለው ትልቅ ሕዝብ ለሮሜ ሰዎች እንደ ወታደሮች ስላገለገላቸው፣ መሬት በደቡብ-ምዕራብ ጋሊያ ተሠጥተው ነበር። ብዙ ጊዜ ሳያልፍ ግን የሮማውያን ሥልጣን እየደከመ እኚህ ቪዚጎቶች በራሳቸው ንጉሥ ሥር ሆነው ግዛታቸውን ያስፋፉ ጀመር። ስለዚህ አይጊዲዩስ የተቀበለው አውራጃ በስሜን ጋሊያ ሲሆን ወደ ጣልያና ወደ ሮሜ ያገናኘው ጠባብ ስርጥ ብቻ ነበር። ይህም ስርጥ ደግሞ በማዮሪያኑስ ዘመን በጀርመናውያን ነገዶች በመያዙ፣ የአይጊዲዩስ ግዛት ያንጊዜ ከሮሜ ተቋረጠ።

ኃይለኛው ጀርመናዊ ጦር አለቃ ሪኪመር453 ዓ.ም. ማዮሪያኑስን ካስገደላቸው በኋላ፣ አይጊዲዩስ ሥልጣኑን በጋሊያ ጠበቀው። በ455 ዓ.ም. ከፍራንኮች ጋር ተባብሮ፣ ቪዚጎቶቹን በኦርሌያን ውጊያ ድል አደረገ። በ456 ዓ.ም. ግን አይጊዲዩስ ተገደለ፤ ልጁም ሲያግሪዩስ ግዛቱን ወረሰ። ማዕረጉ በይፋ የሮሜ አገረ ገዥ ቢሆንም፣ ጀርመናዊ ጎረቤቶቹ «የሮማውያን ንጉሥ» ይሉት ነበር። መቀመጫውም በአሁኑ ሷሶን ከተማ (በሮማይስጥኖዊዱኑም) ነበረ። ስለዚህ በአንዳንድ ታሪክ ግዛቱ «የሷሶን መንግሥት» ወይም «የሲያግሪዩስ መንግሥት» ይባላል።

በሮሜ ጣልያ በ468 ዓ.ም. መጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ሮሙሉስ አውግስጦስ በጀርመናዊው አለቃ ኦዶዋካር ስለ ተሻሩ፣ የሮሜ ነገሥታት ሥልጣን በምዕራብ ተቋረጠ። ሲያግሪዩስ ግን የኦዶዋካርን መንግሥት ስላልተቀበለ፣ እርሱ በስሜን ጋሊያ ገዢ ሆኖ የሮሜ ሕግጋትን አስቀጠለ።

የፍራንኮች ንጉሥ 1 ቺልደሪክ473 ዓ.ም. ዐርፎ፣ ተከታዩ 1 ክሎቪስ የሲያግሪዩስ ጠላት ሆነና በጦርነት አገሩን በሙሉ ያዘ። በመጨረሻ የሷሶን ውጊያ (478 ዓ.ም.) ክሎቪስ ስያግሪዩስን አሸነፈ። ከዚህ በኋላ ግዛቱ ሁሉ ወደ ፍራንኮች መንግስት ተጨመረ።[1] ሲያግሪዩስ ወደ ቪዚጎቶች ቢሸሽም፣ ፍራንኮች ዛቻ ስለ ጣሉ ቪዚጎቶች መለሱትና ይሙት በቃ ተፈረደ።[2][3]

ዋቢ መጻሕፍት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]