Jump to content

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ

ከውክፔዲያ
ዶ/ር ማርቲን ሉጠር ኪንግ

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒዮር (እንግሊዝኛ፦ Dr. Martin Luther King Jr.) (1921-1960 ዓም) ስመ ጥሩ አመሪካዊ የክርስትና ሰባኪና የብሔራዊ መብቶች እንቅስቃሴ መሪ ነበሩ።

ህልም አለኝ (I have a dream)

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር በ1963 እ.ኤ.አ.ዋሽንግተን ዲሲ አደባባይ ለተሰበሰቡት አድማጮቹ በሰው ልጅ የነፃነትና የእኩልነት ታሪክ ውስጥ ሲጠቀስ የሚኖረውን "ህልም አለኝ" የተሰኘ ንግግሩን አሰማ፡፡ የዚህን ንግግር ኃያልነትና ጥልቀት ለመረዳት ንግግሩ የተደረገበትን ዘመን ታሪክ መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ጊዜው ሩቅ አይደለም - ማርቲን ሉተር ኪንግ በአደባባይ ለጥቁሮች ጥላቻ ባላቸው ነጮች ከተገደለ እንኳን ገና ሃምሳ ዓመት መሙላቱ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ቅሪቶቹ በተለያየ መንገድ የሚንፀባረቁት በነጮችና በጥቁሮች መካከል የሚደረግ አድልዎ ማርቲን ሉተር ኪንግና መሰሎቹ በኖሩበት ዘመን ህጋዊ ሽፋን ያገኘ ድርጊት ነበር፡፡ ጥቁሮች በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ ሰው ሊኖረው የሚገባው የሰውነትና የዜግነት መብቶች ተነፍገዋቸው ነበር፡፡ ጥቁሮች ፡-

  • ከነጮች ጋር በአንድ ት/ቤት የመማር፣ ምግብ ቤት ፣ መፀዳጃ ቤት፣ የህዝብ ትራንስፖርት የመሳሰሉትን መጠቀም አይፈቀድላቸውም ነበር
  • በፖለቲካዊ ምርጫ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ መሳተፍ አይችሉም ነበር፡፡

እነዚህ በአደባባይ ከሚደረጉት መዋቅራዊ መድልዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ በነጭ ግለሰቦች የሚፈፀሙ ፀያፍ የአድልዎና የጥላቻ ተግባራት ከዝርዝር በላይ ናቸው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና የትግል አጋሮቹ ይህ ሰው በተፈጥሮው ሰው ስለሆነ ብቻ ሊያገኘው የሚገባውን የተፈጥሮ መብት ጨምሮ በአገሪቱ ህገ-መንግስት (እነርሱ የሪፐብሊኩ መስራች አባቶች (Founding Fathers) ብለው በሚጠሯቸው ግለሰቦች) የተፃፉትን መርሆች የሚቃረን መዋቅራዊም ሆነ ግለሰባዊ አድልዎ ኃይል ያልተቀላቀለበት አመፅ (Non-Violent Protest) በሆነ የትግል መንገድ ለማስቀረት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡

ምንም እንኳን ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና መሰሎቹ አመፅ-አልባ የትግል ስልትን ቢመርጡም እነርሱ የሚታገሉት የነጮችን የበላይነት የሚያራምደው መዋቅራዊ ስርዓትም ሆነ ግለሰቦች ይህን አመፅ-አልባ ትግል ለማስቀረት የተከተሉት መንገድ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ነበር፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን ጨምሮ በዚህ አመፅ-አልባ ትግል ውስጥ የተሳተፉት ጥቁሮች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል ተገድለዋል፡፡

ዛሬም ድረስ መዋቅራዊ ዘረኝነት (Systemic Racism) በአሜሪካ ጣጣው ያበቃ አይመስልም፡፡ በየግዛቶቹ ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ አመፆችና ግድያዎች የየዕለት ዜና ዘገባዎች መሆናቸው አላበቃም፡፡

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና አጋሮቹ ይህንን ጥቁሮቹን ከሰውነትና ከዜግነት በታች ያደረጋቸውን ስርዓት ለማስቀረት አመፁ፡፡ አንዱ የአመፁ መገለጫ የአደባባይ ሰልፍ ማድረግ ነውና በሀገሪቱ ዋና ከተማ በዋሽንግተን ዲ.ሲ አደባባይ ብዙ ሺዎች ሆነው ተሰለፉ፡፡ በዚህ የ1963 እ.ኤ.አ. የአደባባይ ሰልፍ ላይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር "ህልም አለኝ" የተሰኘ ዝነኛ ንግግሩን አሰማ፡፡ በዚህ ንግግሩ ላይ እንዲህ አለ " … ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ የመጣነው የተሰጠንን ቼክ ልንመነዝር ነው፡፡ የሪፐብሊኩ መስራቾች አንፀባራቂ የሆኑትን ህገ-መንግስት (Constitution)ና የነፃነት አዋጅ (Declaration of Independence) በፃፉ ጊዜ ሁሉም አሜሪካዊ ወራሽ የሚሆንበትን የቃል-ኪዳን ሰነድ (Promissory Note) ነው የሰጡን፡፡ … ይሁን እንጂ አሜሪካ ለጥቁር ህዝቦቿ 'በቂ ስንቅ የለውም' የሚል ማህተም የተረገጠበት 'ደረቅ ቼክ' ሰጥታቸዋለች፡፡ ነገር ግን የፍትህ ባንክ ከስሯል ብለን ማመን አንፈልግም፡፡ በዚህ ሀገር ታላቅ የመጠቀም ዕድል ካዝና (Opportunity Vault) ውስጥ በቂ የሆነ ሀብት የለም ብለን አናምንም፡፡ ስለሆነም ዛሬ የነፃነትን ሀብትና የፍትህን ዋስትና የሚሰጠንን ይህንን ቼክ ልንመነዝር መጥተናል፡፡"

ምንም እንኳን ይህ የደረቅ ቼክ ይመንዘርልን ጥያቄ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን ህይወት ጨምሮ የብዙ ሰዎችን ህይወት ያሳጣ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ተመንዝሯል፡፡ ዛሬ ጥቁሮች ፡-

  • የመመረጥና የመምረጥ
  • ከነጮች ጋር በአንድ ት/ቤት የመማር፣ ምግብ ቤት ፣ መፀዳጃ ቤት፣ የህዝብ ትራንስፖርት የመሳሰሉትን የመጠቀም መብት አላቸው

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ያልተመነዘሩ ቀሪ የቼኩ ስንቆች አሉ፡፡ በግለሰብና በመዋቅራዊ ስርዓት የሚደረጉ መድሎዎች አሁንም አላቋረጡም፡፡ መሳሪያ ያልታጠቁ ጥቁሮች በታጠቁ ፖሊሶች ይገደላሉ፡፡ ጥቁሮች ከነጮቹ የበለጠ በአነስተኛ የህግ መተላለፍ ጥፋቶች የረዥም ዓመታት አሊያም የዕድሜ ልክ እስራት ይፈረድባቸዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን በስታርባክስ የቡና መሸጫ ሰው ለመጠበቅ የገቡ ሁለት ጥቁሮች ፖሊስ ተጠርቶ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ (ምንም እንኳን በኋላ የስታርባክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅም) ይህ አይነቱ አድልዎ BLM (Black Lives Matter) የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሚደረጉ ኃይል ካልተቀላቀለባቸው የአመፅ ታሪኮች እንደ ፋኖ ከሚጠቀሱ ባለታሪከኞች መካከል ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና አጋሮቹ የሆኑበት ዋነኛው ምክንያት የትግላቸው መነሻ ሰው በቆዳ ቀለሙ በማህበራዊ ህይወቱና በፖለቲካዊ ስልጣን ልዩነት የተነሳ አድልዎ ሳይደረግበት የሰውነት መብቱ ሊከበርለት ይገባል የሚል መሰረታዊ መርሆ በመያዛቸው ነው፡፡

ኢኮኖሚ ያደገም ሆነ ያላደገ ሀገርን የሚመራ ግለሰብም ሆነ ቡድን የዜጎችን ሰብዓዊና የዜግነት መብታቸውን ለማክበር ዘር፣ ሃይማኖትባህል ልማድና የቆዳ ቀለምን ለአስተዳደራዊም ሆነ ለፖለቲካዊ ጥቅምም ቢሆን መሰረት ሊያደርግ አይገባም፡፡