Jump to content

ኤንመባራገሲ

ከውክፔዲያ
የ08:29, 9 ፌብሩዌሪ 2023 ዕትም (ከInternetArchiveBot (ውይይት | አስተዋጽኦ) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)

ኤንመባራገሲ (ወይም መ-ባራገሲ፣ ኤን-መን-ባራገ-ሲ፣ ኤንመባራጊሲ) በ24ኛው ክፍለ ዘመን አክልበ. ግድም የኪሽ ንጉሥ (ሉጋል) በሱመር ነበረ። በሱመር ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ፣ «የኤላምን ጦር ያጠፋው» ሲባል 900 ዓመታት (?) ከነገሠ በኋላ በኡሩክ ንጉሥ በዱሙዚድ፣ አሣ አጥማጁ እጅ እንደ ተማረከ ይላል። እንዲያውም ከ2384-2383 ዓክልበ. ያሕል በኪሽ ላይ እንደ ነገሠ ይመስላል።

የኤንመባራገሲ መንግሥት ለመስጴጦምያ መጀመርያው በሥነ ቅርስ የተረጋገጠው ነው። በኒፑር ከተማ ፍርስራሽ ስሙ በአራት የአልቤስጥሮስ ስብርባሪ ላይ «መባራግሲ ሉጋል ኪሽ» ተብሎ ተገኝቷል[1]፤ እርሱም በዚያ ከተማ መጀመርያውን ቤተ መቅደስ እንዳሠራ የቱማል ዜና መዋዕል የተባለው ሱመርኛ ሰነድ ይለናል።[2]

የኤንመባራገሲ ስም እንደገና በ«ቢልጋመሽና አጋ» (ከሱመርኛው የጊልጋመሽ ትውፊት አንድ ምዕራፍ) ይገኛል፤ በዚህ ጽላት ኡሩክን የከበበው የኪሽ ንጉሥ አጋ አባት ይባላል። የአጋ መንግሥት ደግሞ ከሥነ ቅርስ ተረጋግጧል። የሱመር ነገሥታት ዝርዝር እና የቱማል ዜና መዋዕል በዚህ ይስማማሉ፤ በሁላቸው ዘንድ የኤንመባራገሲ ተከታይ ልጁ አጋ ነው ይላሉ። የኪሽ ንጉሥ ኤንመባራገሲ በኡሩክ ንጉሥ በዱሙዚድ እጅ ከተማረከ፣ ከዚያም የዱሙዚድ ተከታይ ጊልጋመሽ ከልጁ ከአጋ ጋር ከታገለ፣ እንግዲህ የኡሩክ ነገሥታት ዱሙዚድና ጊልጋመሽ ታሪካዊ ኅልውና እንደነበራቸው መገመት ይቻላል።

በኋላ ዘመን፣ የኡር ንጉሥ ሹልጊ በጻፈ መዝሙር ጊልጋመሽን በማመስገን ሲሄድ፣ ጊልጋመሽ እራሱ ኤንመባራገሲን የማረከውና ያሸነፈው ነበር ይላል። ይህ ግን ከሌላው ምንጭ ጋር አይስማማም፤ ኤንመባራገሲ የተማረከው ጊልጋመሽን በቀደመው በዱሙዚድ መሆኑ ስለሚባል።

ጊልጋመሽ ትውፊት በሌላ ምዕራፍ፣ ጊልጋመሽ «እኅቱን» ኤንመባራገሲ ለአስፈሪው አውሬ ለሁምባባ እንደ ሚስት ያቀርባል። ስለዚህ ስለ ኤንመባራገሲ ጾታ ትንሽ ክርክር ቢነሣም፣ በአብዛኛው ዘንድ ይህ ለቀልድ የተጻፈው አይቀርም።

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  1. ^ "የኤንመባራገሲ ቅርሶች". Archived from the original on 2021-12-06. በ2018-03-22 የተወሰደ.
  2. ^ "The Electronic Text Corpus of Sumerian Literature; ETCSLtranslation : t.2.1.3; The history of the Tummal". Archived from the original on 2018-09-24. በ2008-04-22 የተወሰደ. የቱማል ዜና መዋዕል (እንግሊዝኛ)