Jump to content

ቅዱስ መርቆሬዎስ

ከውክፔዲያ
የ03:40, 9 ሴፕቴምበር 2023 ዕትም (ከ202.64.124.197 (ውይይት) ተዘጋጅቶ)
(ለውጡ) ← የፊተኛው እትም | «የአሁኑን እትም ለመመልከት» (ለውጡ) | የሚከተለው እትም → (ለውጡ)
ቅዱስ መርቆሬዎስ

የሮም ንጉሥ የዳክዮስ ጦር ጠቅላይ አዛዥ
ሰማዕት
የተወለደበት ዘመን ፪፻፸፩ ዓም [1]
የትውልድ ቦታ ሮም
የመጀመሪያ ስሙ ፒሉፖዴር
የክርስትና ስሙ መርቆሬዎስ
የአባት ስም ሎሪዮ
የእናት ስም ክሪስቲና
ሃይማኖት ክርስትና
በዓለ ንግሥ ባረፈበት ቀን ኅዳር ፳፭ ቀን ፫፻፲ ዓም
የሚከበረው በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና በሁሉም ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት
ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
በምሥራቅም በምዕራብም ቤተክርስቲያኖች
ቤተ መርቆሬዎስን ይመልከቱ


የመጀመሪያ ስሙ ፒሉፖዴር ይባል የነበር ሲሆን ትርጔሜውም የአብ ወዳጅ ማለት ነው፤በሁለተኛው ትርጓሜ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው። የክርስትና ስሙ መርቆሬዎስ ሙያውም ውትድርና ዜግነቱም ሮማዊ ነው ። ይህ ታማኝ ምስክርነት የሰጠ ሰማዕት ወላጆቹ ጣዖት የሚያመልኩ አረማውያን ነበሩ።ከጊዜ ወደ ጊዜ የክርስትና እምነት እየተስፋፋ ስለ ሄደ ቤተሰቦቹም ክርስቲያኖች ሆነዋል። እሱም ካደገ በኋላ ተምሮና አምኖ ተጠመቀ ስመ ጥምቀቱም መርቆሬዎስ ተባለ ።

ጥንተ ነገሩ አባትና አያቱ ጣኦት በማምለክ ሲኖሩ ከእለታት በአንዲቱ እለት ለአደን ቢወጡ ገጸ ከለባት መጥተው የመርቆሬዎስን አያት ሲበሉ አባቱን ግን መልአከ እግዚአብሔር ታድጎታል ምክንያቱም ከሱ ባህርይ የሚወለድ ማር መርቆሬዎስ አለና። ከዚህም በኋላ እናቱና አባቱ የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆኑ በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተወለደና ስሙ ፒሉፓዴር ተባለ፡፡ እነዚያን ገጸ ከለባትም እግዚአብሔር ባህርያቸውን ገራም አድርጎላቸው የመርቆሬዎስ አባት አገልጋይ ሆነዋል። ኋላም ንጉሱ የገጸ ከለባቱን ኃይል ተመልክቶ የመርቆሬዎስን አባት የጦር አለቃ አድርጎታል፤ ገጸ ከለባቱም በጦርነት ጊዜ የቀደመ ባህርያቸው እየተመለሰ የመርቆሬዎስን አባት ይረዱት ነበር ማንምም አይችላቸውም ነበር። በአንድ ጦርነት ግን የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት በእግዚአብሔር ፈቃድ በጦርነት ተማርኮ በሌላ ንጉስ እጅ ገባ ይህንን የሰማው ንጉስ የመርቆሬዎስን እናት አገባለው በማለቱ የመርቆሬዎስ እናትና ብጹእ መርቆሬዎስ ወደ ሌላ አገር ተሰደዱ። የመርቆሬዎስ አባት ግን በተማረከበት ንጉስ ዘንድ ክርስቲያን መሆኑ ሲሰማ ተወዳጅነትን አግኝቶ ሹመትን አገኘ ኋላም ከብጹእ መርቆሬዎስና ከእናቱ ጋር በእግዚአብሔር ቸርነት ተገናኙና በአንድነት ኖሩ። የመርቆሬዎስ እናትና አባትም በአረፉ ጊዜ መርቆሬዎስ የአባቱን ሹመት ተቀብሎ በመርዶሳውያን አገር ላይ ተሾመ። ያ ገጸ ከልብም ከእርሱ ጋር ነበርና በውጊያ ጊዜ ማንም ሊቋቋመው አይችልም ነበር። የበርበር ሰዎችም በዳኬዎስ ንጉስ ላይ በተነሱ ጊዜ ንጉሱ ፈራ መርቆሬዎስም እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ በእጃችንም አሳልፎ ሊሰጣቸው አለውና አትፍራ አለው። ከዚህም በኋላም የእግዚአብሔር መላእክ በውጊያ ውስጥ የተሳለ ሰይፍ ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል አደረገ። ሰነፍ የሆነ ዳኬዎስ ግን ከጦርነቱ በኋላም ድልን የሰጡህ ጣኦቶቼ ናቸውና ለአማልክት ሠዋ አለው። መርቆሬዎስ ግን ትጥቁንና ልብሱን ወረወረለትና ንጉሱን እንዲህ አለው። እኔ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣኦታትም አልሰግድም። ከዚህ በኋላም ሰነፉ ዳዴዎስ ተቆጥቶ በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃየው። በሽመል የሚደበድቡት ጊዜ አለ፣ በቆዳ ጅራፍም የገረፉትም ጊዜ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ከታች እሳት አንድደው በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ቢገርፉት ደሙ ተንጠባጥቦ እሳቱን አጠፋው። እንዲህ ባለ ስቃይ ለ፭ ዓመታት ተሰቃይቶ መጨረሻ ላይ ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ተጋድሎውን ፈጽሞ በመንግስተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለ። ካልዕ ሊቀ ሰማዕትም ተባለ። ከእረፍቱ በኋላም ክርስቲያኖችን ይገድል፣ያሰቃይ የነበረውን፣ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይም የስድብን ቃል የተናገረውን ኡልያኖስን ተበቅሎ የገደለ፤ ቅዱስ ባስልዮስንና ቅዱስ ጎርጎርዮስን የረዳቸው እርሱ ተአምረኛው ድንቅ አድራጊው መርቆሬዎስ ነው።

ለምን መከራን ተቀበለ?

1 ስለመንግስተ ሰማያት ሐዋ14÷22

2 ሃይማኖትን ለመመስከር ማቴ10÷32

3 አርአያ ለመሆን

4 እውነትን በሐሰት መለወጥ ስላልፈለገ 2ተኛ ቆሮ 5÷13

ስለመርቆሬዎስ በአጭሩ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መርቆሬዎስም ማለት የእየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ሲሆን ይህም ቋሚ መጠርያ ስሙ ሆኖ ቀረ ። በእንግሊዞች የተጻፈው ገድለ ቅዱሳን ባዮግራፊ ኦፍ ሴንትስ እንደሚለው ዜግነቱ ኢጣሊያዊ ሲሆን ስሙንም መርኮርዮ ብሎታል የእባቱንም ስም ሎሪዮ የእናቱንም ስም ክርስቲና እንደሆነ ገልጿል ። በያመቱ ኅዳር ፳፭ ቀን የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ የአባቱን ስም ኖኅ የናቱን ስም ታቦት የራሱንም ስም መርቆሬዮስ እንደሆነ ይገልጻል ። በዚያም ዘመን ውትድርና የተወደደና የተከበረ ሙያ ስለነበር መርቆሬዎስም ዳክዮስ ለተባለ ንጉሥ ወታደር ሆነ ዕለት ከዕለት የሚያሳየው ወታደራዊ ሥነ ሥርዓትና በሚፈጽመው ጀብዱ ከሌሎች ወታደሮች ይልቅ ተወዳጅነትና ባለሟልነት አገኘ ፤ ዳክዮስ ጠላቱን ድል አድርጎ በተመለሰ ቁጥር ድል ያስገኘለትን እግዚአብሔርን ዘንግቶ ድል የሚያስገኝለት ጣዖት እየመሰለው ከጦርነት ሲመለስ ለጣዖት መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ ነበረው ከዕለታት አንድ ቀን ዳክዮስ መርቆርዮስን አስከትሎ ዘመተና ጠላቱን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ እንደ ልማዱ ለማይሰማውና ለማይናገረው ጣዖት ከስግደትና ከጸሎት ጋር የምስጋና መሥዋት አቀረበ ከደስታው ብዛት የተነሣ ብዙ እንሰሳት በየዓይነቱ እየመረጠ ሠዋ።

የመርቆሬዎስ ጀግንነትን የሚገልጽ ስዕል

ሰማዕት የሆነበት ምክኒያት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ቅዱስ መርቆሬዎስም ይህን በማየቱ ሰው ድል ለሰጠው ለእግዚአብሔር በመስገድና እሱንም በማመስገን ፈንታ እንዴት ሰው ለሠራው ጣዖት ይሰግዳል ? በማለት ቅር ስላለውና አረማዊነቱንም በግልጽ ስላወቀ በዚህ ተቀይሞ ወደተዘጋጀው የድል ግብዣ ሳይሄድ ቀረ በዚሁ ጊዜ አብረው የዘመቱ ሌሎች የሠራዊቱ አባሎች እኛ ለምታመልከው ጣዖት ስንሰግድና ባደረከው ታላቅ ግብዣ ትእዛዝህን አክብረን ስንገኝ ታማኝ ባለሟልህ መርቆርዎስ ትእዛዝህን በመናቅና አንተን ባለማክበር እነሆ አልተገኘም እንዲያውም ለጣዖትህ መስገድ የማይፈልግ ሳይሆን አይቀርም አስተያየት ስጥበት ብለው በንጉሡ መሾምና መወደድ የሚፈልጉ ሰዎች አሳጡት።

ቅዱስ መርቆሬዎስ በጣር ግምባር ውጊያ ላይ

ዳክዮስም በመርቆሬዎስ ላይ የቀረበውን ክስ ካዳመጠ በኋላ መርቆርዎስን አስጠርቶ ስለምን ለጣዖት እንዳልሰገደና መሥዋዕት እንዳላቀረበ እንዲሁም ወደ ግብር እንዳልመጣ ጠየቀው ። እሱም ሳይፈራ በድፍረት እንኳንስ እኔ ለጣዖትህ ልሰግድና መሥዋዕት ላቀርብ አንተም እንዲህ በማድረግህ አዝናለሁ ብሎ መለሰለት ፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አመልካለሁ ፤ ለሱም እሰግዳለሁ ይኸው መሣሪያህንና ትጥቅህን ተረከበኝ ብሎ አውልቆ ወረወረለት።ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ መስቀል መሸከሙንና ወንጌል ይዞ የክርስቶስ ወታደርነቱን በመግለጹ ዳክዮስ በጣም ተናደደ በግርፋትና በእስራት እንዲያሰቃዩትም አዘዘ ። በእስር ቤት ሲሰቃይ ሳለ የሮም ዜጋ ሆኖ በመታሰሩና በመሰቃየቱ የሮም ዜጋ መታሰሩንና መሰቃየቱን ያወቁ መገረፉንም የሰሙ እንደሆነ ሮማውያን ታላቅ ኃይል ያስከትሉብናል የሚነሣውንም ዐመፅ ለመቋቋም ስለማይቻል ግዛታችን ሰፊ ነውና በጽኑ እስራትና በግዞት እንዲሰቃይ ወደ ቂሣርያ እንላከው ሲሉ ተማከሩ ። ዳክዮስና አማካሪዎቹ በዚሁ በመስማማታቸው ታማኙ ሰማዕት ወደዚችው አገር ተላከ ቂሣርያም የምትገኘው በምድረእስራኤል ነው ።

ማርቆሬዎስ በቄሣሪያ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በቂሣርያም እስር ቤት ስቃዩንና መከራውን ተቋቋመ ወንጌል እየሰበከና እስረኞችን ከአረማዊነት ወደ ክርስትና እምነት እየለወጠ ስላስቸገራቸው ኅዳር ፳፭ ቀን ፫፻፲ ዓ/ም በሰይፍ ተከልሎ በሰማዕትነት ዐረፈ። እንደ ቅዱስ መርቆሬዎስ ስለ ታማኝ ምስክር ዮሐንስ በራእዩ በም:፫፥፲፪ እንዲህ ሲል ጽፎታል፡

"ድል የነሣውን በአምላኬ መቅደስ ዐምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም የአምላኬን ከተማ ስም ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌም አዲሲቱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ..."ብሏል።

እርግጥም ቅዱስ መርቆሬዎስ ወደ አዲሲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል።
  1. ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሥንክሳር ወይም Ethiopian Synaxarium በኅዳር ፳፭ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል