ተዳፋት
Appearance
ተዳፋት ከስድስቱ ቀላል ማሽኖች አንደኛው ሲሆን መጨረሻውና መጀመሪያው በተለያዩ ከፍታወች ከተቀመጠ ጠፍጣፋ ገጽታ ይሰራል። የዚህ ማሽን ዋና ጥቅሙ አንድን ከባድ እቃ በቀጥታ ከማንሳት በአንስተኛ ጉልበት ተመሳሳይ ስራን ለማከናወን በማስቻሉ ነው። እዚህ ላይ መረዳት ያለብን ምንም እንኳ አንስተኛ ጉልበት ብናወጣም ዕቃው የሚጓዝበት ርቀት ግን ቀጥታ ከማንሳት ይበልጣል። ባጠቃላይ መልኩ፣ ተዳፋት ከባድ ስራን በቀላል ጉልበት ለመስራት ያስችላል።
በአንድ ተዳፋት ላይ የተቀመጠ እቃ ሶስት አይነት መሰርታዊ ጉልበቶች ያርፉበታል፣ እነርሱም የመሬት ስበት፣ የተዳፋቱ ገጽታ በዕቃው ላይ የሚያሳርፈው ጉልበትና ሰበቃ ናቸው። ሲተነተኑና ሲሰሉ እንዲህ ይሆናሉ፡
- ቀጤነክ ጉልበት(N) - ይህ ጉልበት አመጣቱ እንዲህ ነው። እቃው በክብደቱ ምክንያት የተዳፋቱ ገጽታ (ጠለል) ላይ ጉልበት ያሳርፋል። በ3ኛው የኒውተን ህግ መሰረት ጠለሉ እቃው ላይ እኩልና ተቃራኒ ጉልበት ያሳርፋል። ዋጋውም mg cos θ ነው።
- የመሬት ስበት እቃው ላይ ወደ ታች የሚያሳርፈው ጉልበት (mg ) ሌላው ነው።
- እቃውና የተዳፋቱ ገጽታ እርስ በርሳቸው የሚያሳርፉት የሰበቃ ጉልበት (f) ሌላው ነው። ይህ ጉልበት ለተዳፋቱ ጠለል ትይዩ ነው።
የአንድ ተዳፋት የጥቅም መጠን እሚለካው የተዳፋቱን ገጽታ ርዝመት ለቁመቱ ስናካፍል የምናገኘው ቁጥር ነው። ለምሳሌ አንድ ተዳፋት ቁመቱ 1 ሜትር ቢሆን እና ርዝመቱ 5 ሜትር ቢሆን፣ የጥቅም መጠኑ = 5/1 = 5