ግዝፈት
ግዝፈት ( mass) ማለት አንድ ቁስ አካል ያለው የቁስ ብዛት ማለት ነው።
ለምሳሌ ይዘቱ 20 ጊዜ ትልቅ የሆነ የወርቅ ጡብ ይዘቱ 1 ጊዜ ከሆነ የወርቅ ጡብ የበለጠ 20 እጥፍ ቁስ አካላት ይይዛል። ስለዚህ ግዝፈቱ 20 ጊዜ ትልቅ ነው ይባላል።
ግዝፈት በዓለም ላይ ለሚገኙ ማናቸውም አካላት የውስጥ ባሕርይ (intrinsic property) ነው። ስለዚህ የቁሶች ግዝፈት በቦታም ሆነ በሌላ ውጫዊ ምክንያት አይለዋወጥም።
ቁስ አካላት ያላቸውን ፍጥነት በጉልበት ካልተገደዱ በቀር አይቀይሩም። ፍጥነታቸው እንዳይቀየር የሚያሳዩት ዕልህ በአላቸው ቁስ ብዛት ልክ ነው። ስለዚህ ግዝፈት፣ «አንድ ቁስ የያዘውን ፍጥነት እንዳይቀይር የሚያሳየው ተቃውሞ ልኬት » ተብሎ ሊተረጎም ይቻላል ። ይህ ተቃውሞ በያዘው ቁስ ልክ መሆኑ የሳይንስ ሐቅ እና የለተ ተለት ተሞክሮ ነው። ስለዚህ በአጭሩ ግዝፈት ማለት መጠነ-ዕልህ ነው ተብሎ ሊተረጎም ይቻላል።
ለምሳሌ በእኩል ጉልበት ፣ ትንሽ እና ትልቅ ድንጋይ ለማንቀሳቅስ ቢሞከር፤ ትንሹ ያለብዙ ተቃውሞ ፍጥነቱን ሲቀይር ፣ ትልቁ ግን ዝግ ባለ ሁኔታ፣ በብዙ ተቃውሞና እልህ ይንቀሳቀሳል። ስለዚህ ትንሹ ድንጋይ ከትልቁ ድንጋይ ያነሰ ግዝፈት አለው ይባላል።
አንድ ነገር ያለው ግዝፈት (መጠነ ቁስ) የትም ቦታ እኩል ነው። ከባህር ወለልም ሆነ ከተራራ ላይ፣ አንድ ቁስ አንድ ዓይነት ግዝፈት አለው ምክንያቱም በአንድ አይነት ሁኔታ ፍጥነቱን ለመቀየር እኩል ጉልበት ስለሚጠይቅ። በሌላ አባባል፣ ለጉልበት እሚያሳየው ተቃውሞ የትም ቦታ እኩል ነው። በጠፈር ኦና ሳይቀር፣ ይህ ተቃውሞው አይቀየርም።
የቁስ አካላት ግዝፈት በየአቅጣጫው አይቀያየርም። የአንድ ነገር መጠነ ቁስ በሰሜን በኩል ቢለካና በምሥራቅ በኩል ቢለካ፣ ሁለቱም አንድ ዓይነት ሁነው ይገኛሉ። ሰለዚህ ግዝፈት አቅጣጫ የለውም።
ቁሶች አንድ ላይ ተጣብቀው ወይንም ተነጣጥለው ሊገኙ ይችላሉ። ተነጣጥለው ሲገኙ የቁስ ስብስብ ይፈጥራሉ። ተጣብቀው ሲገኙ ደግሞ የቁስ አካል ይፈጥራሉ። ሁለቱም ዓይነት ክስተቶች የቁስ ሥርዓት ይባላሉ።
የቁስ ሥርዓቶች አጠቃላይ ግዝፈት የተሰሩበት የእያንዳንዳቸው ቁስ-አካላት ግዝፈት ድምር ውጤት ነው። ስለዚህም 5ኪሎ መዳብና 4ኪሎ ቆርቆሮ ቢደባለቁ 4+5 = 9 ኪሎ ነሐስ ይሰጣሉ። 4 ኪሎ ድንጋይ እና 3ኪሎ ውሃ በአንድ ሳጥን ውስጥ ቢገኙ፣ የሁለቱ ቁስ አካላት ግዝፈት 7ኪሎ ይሆናል። የተሰሩበት ቁስ ምንም ለውጥ አያመጣም።
ይህ የመደመር ባህርይ በቁስ አካላት ላይ ሒሳባዊ ትንታኔ ለማካሄድ እጅግ ይረዳል። ስለሆነም አንድን ቁስ በዓይነ-ኅሊና imagination ለሂሳብ ትንታኔ በሚረዳ መልኩ እንደተፈለገ ለመበተንና ለማሰባሰብ ይቻላል። በዚህ መልኩ ጠቃሚ የሆነውን የቁሶች መጠነ እንቅስቃሴ (momentum) ለማስላት ይረዳል። በምሳሌ ለማየት፦ 10ኪሎግራም የሚመዝን አንድ ቁስ፣ ከአስር 1ኪሎግራሞች የተሰራ ነው። እያንዳንዳቸው 1ኪሎግራም ከ1000 ግራም የተሰራ ነው። እያንዳንዳቸው 1ግራም ከ1000 ሚሊግራም የተሰራ ሆኖ ይገኛል፣ ወዘተ... ስለዚህ 10ኪሎግራም መጠነ ቁስ ያለውን አንድ አካል፣ በዓይነ-ኅሊና ብቻ ወደ 10X1000X1000 = 10 ሚሊዮን ሚሊግራም ቁሶች መበተን ይቻላል።
ለንፅፅር ያክል፤ ሁላቸውም የቁሶች ባህርዮች እንደዚህ ዓይነት ለሒሳብ የተስማማ ጸባይ የላቸውም። ለምሳሌ ድቡልቡልነት የሎሚ ጸባይ ሆኖ ሳለ በዓይነ-ኅሊናም ሆነ በተግባር የአንድን ሎሚ ድቡልቡልነት መከፋፈል ሆነ መደመር አይቻልም። ለመክፈል ቢሞከር ድቡልቡልነቱ ይጠፋል። ስለዚህም ሒሳባዊ ትንታኔ የለውም።
ግዝፈት በ SI ስርዓት መለኪያው kilogram (ኪሎግራም) በምህጻረ ቃል kg (ኪ.ግ.) ነው። ምንም እንኳ በተለምዶ ይሄ የመለኪያ አሃድ ለክብደት መለኪያ ቢውልም፣ ትክክል ግን አይደለም። የነገሮች ክብደት ሲለዋወጥ፣ ግዝፈታቸው ግን ውስጣዊ ባህርይ ስለሆነ ፈጽሞ አይለዎጥም።
ክብደት ከግዝፈት የሚመነጭ ግን የተለየ የሳይንስ ጽንሰ-ሐሳብ ነው። ግዝፈት ያላቸው ማናቸውም ነገሮች እርስ በርሳቸው እንደሚሳሳቡ የተፈጥሮ ኅግጋት ጥናት ያዎቀውና ያጸናው ሐቅ ነው። ስለዚህ ክብደት የጉልበት መጠን ሲሆን፣ ግዝፈት ግን የቁስ ብዛት ነው።
በመሬት ላይ የሚኖር ማንም ቁስ፣ በመሬት ይሳባል። ይህ ጉልበት፣ የቁሱ ክብደት ይባላል። ትልቅ ግዝፈት ያላቸው ነገሮች፣ በግስበት ሕግጋት ምክንያት በትልቅ ጉልበት ይሳባሉ፣ ትንሽ ግዝፈት ያላቸው ደግሞ በትንሽ። ስለዚህ ክብደትና ግዝፈት የተለያዩ ፅንሰ-ሐሳቦች ቢሆኑም ተመጣጣኝ ዝምድና ግን አላቸው። ልዩነታቸው እና አንድነታቸው ልክ የአንድ ነገር ቁመት እና ጥላው እንዳላቸው ግንኙነት ነው። የአንድ ነገር ቁመት ምንጊዜም እማይቀየር ሆኖ ሳለ፣ ጥላው ግን እንደ ፀሐይዋ አሰፋፈር ይለያያል። እንደዛም ሆኖ ቁመቱና ጥላው ተመጣጣኝ ዝምድና ይኖራቸዋል። ረጅም ነገር ረጅም ጥላ፣ አጭር ነገር አጭር ጥላ እንዳለው ሁሉ።
የአንድ ቁስ ክብደት ከግዝፈቱ ቢመነጭም ክብደቱ በተለያየ ቦታ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። በተፈጥሮ ኅግጋት መሠረት፣ አንድ ቁስ ወደ መሬት ማህከል እየተጠጋ በሄደ ጊዜ፣ መሬት በላዩ ላይ የምታሳርፍበት ስበት እየጨመረ ይሄዳል። በተቃራኒ ከመሬት እየራቀ ሲሄድ ክብደቱ ይቀንሳል። ስለሆነም ብልጥ ነጋዴ፣ አንድ የወርቅ አምባር ተራራ ላይ ገዝቶ፣ ያን አምባር የባህር ወለል ላይ ቢሸጠው፣ ክብደቱ ስለሚጨምርለት፣ ብዙ ትርፍ ሊያገኝ ይችላል። ማንም እንደሚገነዘበው ግን፣ አምባሩ በምንም ዓይነት አልተቀየረም፣ ያልተቀየረው ነገሩ፣ ግዝፈቱ ይባላል። በውስጡ የያዘው የወርቅ ብዛት፣ ወይንም የቁስ ብዛት ምንጊዜም አንድ አይነት ስለሆነ። ምንም እንኳ ክብደቱ ቢቀያየርም።