አዳል

ከውክፔዲያ
የአዳል ሱልጣኔት

አዳል ሱልጣኔት ተብሎ ይታወቅ የነበረው ግዛት በመካከለኛው ዘመን (ከ1415 - 1577 ዓ.ም.) የነበረ በመጀመሪያዎቹ ከ1415–1559 መሪዎቹ የወላስማ ሱልጣኖች የአርጎባዎች እና የብዙ እስልምና ተከታይ ጎሳዎች ድብልቅ የነበረ ግዛት ነው። አንዳንድ ተመራማሪወች አብዛኛው አዳል የአፋር ጎሳዎች ተዋጾ ነበረበት ሲሉ [1] አንዳንዶች ደግሞ ባብዛኛው ከዲር እና ዳሩድሶማሌ ነገዶች የተውጣጣ ነበር ይላሉ[2]። የአዳልን ሱልጣኔት አብዛኛ ጎሳ ስብጥር ክርክር ይውደቅ እንጂ በርግጥም ሱልጥኔቱ የብዙ ጎሳዎች ስብስብ እንደነበር ግን ክርክር የለም። .

. . . . . . ........................ ............. ........


ስለ አዳል ሱልጣኔት በትንሹ (ከ1415- 1577 ዓ.ል.)

በአብዱ እንድሪስ (ከሚሴ)

አስራ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ነጋሲ የነበረው ወጣቱ አጼ ዳዊት በ1413 ዓ.ል. በአጠገቡ በነበረው የኢፋት ሱልጣኔት ላይ ሀይለኛ ጥቃት ከፈተ። የሱልጣኔቱ ገዠ የነበረውን ሱልጣን ሰዓደዲንን በዜይላ ከተማ ከገደለው በኋላም ኢፋትን ከአጼው ግዛተ መንግስት ጋር ቀላቀለው። ሆኖም አጼ ዳዊት በቁጥጥር ስር ካዋለው የኢፋት ግዛት በሙሉ ሀይሉ ለመግዛት የቻለው ከአዋሽ ወንዝ በስተምዕራብ ያለውን ብቻ ነው። ከወንዙ በስተ-ምስራቅ ያለውና እስከ ዘይላ ድረስ የተንጣለለው ምድር ወዲያውኑ ነበር ከእጁ ያፈተለከው። አባታቸው በዘይላ ሲገደል በስደተኝነት ወደ የመን የሸሹት አስራ አንዱ የሰዓደዲን ልጆች በ1415 ዓ.ል. ከስደት ተመልሰው በምስራቃዊው የኢፋት ግዛት ላይ አዲስ ሱልጣኔት መሰረቱ። ዋና ከተማቸውን ከሀረር አጠገብ በነበረችውና “ደከር” በምትባለው መሬት ላይ ቆረቆሩ። ዳግማዊ ሰብረዲን የሚባለውን የሰዓደዲን ልጅ በወላስማው ወንበር ላይ ካስቀመጡ በኋላ ህልውናቸውን በይፋ አበሰሩ። ከእንግዲህ ወዲያም ለማንም እንደማይገብሩና ሀገራቸውንም ከጥቃት እንደሚከላከሉ በይፋ አወጁ። ለአዲሱ ሱልጣኔትም “አዳል” የሚል ስያሜ ሰጡ።

የኢማም ኣህመድ ኢብን ኢብራሂም ኣል ጋዚ ዘመን[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ታዋቂው ገዥ ኢማም አህመድ ኢብኑ ኢብራሂም አል ጋዚ በሱልጣኔቱ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ነበረው። ከ በለው ጎሳ የተወለደው አህመድ ግራኝ እንደ ማህፉዝ ባሉ ሌሎች የሙስሊም ገዥዎች ስር ብዙ ቦታዎችን ካገለገለ በኋላ በ1527 ወደ ስልጣን መጣ። ግራኝ በተለምዶ በኢትዮጵያ ታሪክ አብያተ ክርስቲያናትን በማፍረስ እና ለክርስቲያኖች የማይራራ ሰው ሆኖ ይገለጻል። ይህን ለመደገፍ አንዳንድ ማስረጃዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ አህመድ ግራኝ እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ ላይ ተጽእኖ ያላቸውን በርካታ ስኬቶችን ኣስመዝግብዋል። እንደ መሪ፣ በክርስቲያን ግዛት ላይ ብዙ ዘመቻዎችን መርቷል፣ እና ብዙ ጦርነቶች ላይ ልብነ ድንግልን እና ሌሎች ገዥዎችን አሸንፏል። በእርሳቸው አገዛዝ ወቅት ንግድ ለክልሎች ኢኮኖሚ ህልውና ቁልፍ ነገር ነበር እናም አዳል ከተለያዩ ሀገራት በተለይም ከኦቶማን ቱርክ ጋር ጠንካራ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ነበረው። የእስልምና ሀይማኖት እንዲስፋፋም የጊዜው ነጋዴዎች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በኣካባቢው ለሚኖሩ ሙስሊሞች መብዛት ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
          • ***** *****

የአዳል ሱልጣኔት የተወለደው ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ከታዩት ሱልጣኔታዊ መንግስታት ውስጥ እጅግ-ገናና ስም የነበረው ይኸው የአዳል ሱልጣኔት ነው። ይህ ሱልጣኔታዊ መንግስት የኢትዮጵያን ታሪክ ለመቀየር የቻሉትን እንደ አሚር ማሕፉዝ ሙሐመድ፣ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚ (አሕመድ ግራኝ) እና አሚር ኑር ሙጃሂድን የመሳሰሉ ታላላቅ መሪዎችን አፍርቷል። በርካታ ጸሀፍት ስለርሱ ከትበዋል። በልዩ ልዩ ህዝቦች ስነ-ቃል ውስጥ እስካሁን ድረስ ያልቀዘቀዙ ወጎች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል። አሁንም ስለርሱ ታሪክ የሚያወሱ በርካታ ድርሳናት እየተጻፉ ነው። ከዚህ እልፍ ሲል ደግሞ “አዳል” የሚለው የሱልጣኔቱ መጠሪያ የሰው ስም ሆኖ ይገኛል። በተለይ የሚያስደንቀው ደግሞ በዚህ ስያሜ የሚጠሩት ከሙስሊሞች ይልቅ ክርስቲያኖች መሆናቸው ነው። ለዚህም ብዙዎች የሚያስታውሷቸውን እንደ ጋሻው አዳል፣ ዘሪኹን አዳልና ራስ አዳል ተሰማ (በኋላ ንጉስ ተክለ ሀይማኖት ተብለው በጎጃም የተሾሙት) የመሳሰሉ ስሞችን መጥቀስ ይቻላል። በሌላ በኩል የሰለሞናዊው አጼ መንግስት ከአዳል ሱልጣኔት ጋር በጦር ሜዳ እየተላለቀ ከነበሩት ክፍለ ጦሮች መካከል አንዱን “አዳል መብረቅ” በሚል ስያሜ ይጠራው ነበር። እርሱም በበኩሉ አዳልን እየጠላው ያደንቀው ነበር ማለት ነው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የሱልጣኔቱ ስመ-ገናናት በሁሉም ወገኖችና ህዝቦች ዘንድ ተደናቂነት ነበረው።

          • ***** *****

“አዳል” የሚለው ስም ምንጭ በትክክል አይታወቅም። አንዳንዶች “አዳ አሊ” (በአፋርኛ የአሊ ቤት ለማለት ነው) ከሚል ሥርወ-ቃል እንደተገኘ ይገምታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጥንት የሀረር አሚር ከነበረው “አሚር ኢዳል” ስም የተገኘ እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም እርግጠኛው ነገር ላይ አልተደረሰም። የስያሜው ጥንታዊነት ግን በብዙ ምንጮች የተረጋገጠ ነው። ለምሳሌ አቡ ፈድሉላህ አል-ዑመሪ የሚባለው ግብጻዊ ምሁር በ1349 ዓ.ል. በጻፈውና “መሳሊከል አብሳር ፊ መማሊከል መሳር” በሚባለው ዝነኛ መጽሀፍ ውስጥ አዳል ተደጋግሞ የተጠቀሰ ስም ነው። ከ1415 ዓ.ል. በፊት “አዳል” በኢፋት ሱልጣኔት ስር የነበረ የአንድ አውራጃ ስም ነበር። የዐጼ ዐምደ ጽዮን (1314-1344 ዓ.ል) ዜና መዋዕል ዘጋቢ እንደጻፈው ከሆነ የዚህ አውራጃ ዋና ከተማ “ተላቅ” የሚል ስያሜ ነበረው። “ፉቱሕ አል- ሐበሽ” የተሰኘው መጽሀፍ ደራሲ ሱልጣኔቱን “አዳል” ከሚለው ስም በተጨማሪ “በሪ ሰዓደዲን” (የሰዓደዲን በር) እና “ዳር ሰዓደዲን” (የሰዓደዲን ሀገር) በሚሉ ስሞችም ይጠራዋል። ይህም ሱልጣኔቱን ያቋቋሙት የሱልጣን ሰዓደዲን ልጆች እንደ ሰማዕት በሚያዩት አባታቸው ስም ያወጡለት የክብር ስያሜ ነው። የግዕዝ ምንጮችም ስለኢትዮጵያ ኢስላማዊ ግዛቶች በሚጽፉበት ጊዜ “አዳል” የሚለውን ስም በእጅጉ ይደጋግሙታል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ስያሜው ከግዛት መጠሪያነት ያልፍና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በሙሉ በወል የሚጠሩበት ስም ሆኖ ይገኛል። በኢትዮጵያ ምድር ከታዩት ሱልጣኔቶች እምብዛም በማያደናግር ሁኔታ ታሪኩ የተጻፈለት “አዳል” ብቻ ነው (ከአንዳንድ አሻሚ ነጥቦች በስተቀር)። እጅግ ሰፊ ግዛት የሚያካልለውም “አዳል” ነው። ከሀረር ከተማ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘውም “አዳል” ነው።

          • ***** *****

አዳል በስፋቱም ሆነ በሕዝቦቹ ብዛት በኢትዮጵያ ምድር ከታዩት ሱልጣኔታዊ ግዛቶች በእጅጉ ይልቃል። በፕሮፌሰር ኡልሪች ብራውኬምፐር ጥናት እንደተገለጸው አዳል በስተምዕራብ በኩል ከባሊ፣ ደዋሮና ፈጠጋር(የአሁኗ ቢሾፍቱ) ጋር ይዋሰናል። በስተሰሜን በኩል ደግሞ እስከ አውሳ በረሃ መጨረሻ ድረስ ይደርሳል። በምስራቅ እስከ ኤደን ባህረ ሰላጤ የሚደርስ ሲሆን በደቡብ ደግሞ ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ይዋሰናል። በአዳል ግዛት ውስጥ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሀረላ (ሀረሪ) እና የአርጎባ ህዝቦች ይኖሩ የነበረ ሲሆን በዘመናችን በውል የማይታወቁ ሌሎች ህዝቦችም ነበሩበት። ዘይላ፡ አራ፣ በርበራ፣ ዳርዱራ፣ ሳሊራ፣ ሆበት፣ ጊዳያ፣ ሐርጋያ፣ ሀረር እና ኩሰም ከአዳል ከተሞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። “ደከር” የሱልጣኔቱ የመጀመሪያ መዲና ነበረች፤ ከዚያም በዜይላ ተተካች፤ በስተመጨረሻም ሀረር የግዛተ መንግስቱ ዋና ከተማ ሆነች። አዳል የአዋሽ ወንዝ በሚፈስበት ክፍሉ እጅግ ለምና ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት ነበረው። አብዛኛው የሱልጣኔቱ ነዋሪ በግብርና ይተዳደር የነበረ ሲሆን ይህም የሰብል ማምረትንና የከብት እርባታን ያካተተ ነበር። በሌላ በኩል ሱልጣኔቱ የህንድ ውቅያኖስና የኤደን ባህረ ሰላጤ ተጎራባች መሆኑ ንግድ በክልሉ እንዲስፋፋ በእጅጉ ረድቷል። ዘይላ ሱልጣኔቱ ከውጪው ዓለም ጋር የሚገናኝበት ዋነኛ ወደብ ነበረች። የታጁራ፡ በርበራና መርካ ወደቦችም የሱልጣኔቱ አካላት ነበሩ። ከደቡብ፣ ከምዕራብና ከደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡት የግብርና ውጤቶች፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ ዘወተ.. ወደ ውጪ የሚላኩት በነዚሁ ወደቦች በኩል ሲሆን ከውጪው ዓለም የሚገቡ ሸቀጦችም ወደ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገቡት በሱልጣኔቱ ምድር ነው። ሰፊው የአዳል ሱልጣኔት በስሩ ያሉትን ክልሎች ሁሉ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ አይደለም ያስተዳደረው። በስሩ ካሉት አካባቢዎች አንዳንዶቹ የራስ ገዝ አይነት አስተዳደር ነበራቸው። እነዚህ አስተዳደሮች “አሚር” የሚል ማዕረግ በነበራቸው ገዥዎች ይተዳደሩ ነበር። በአሚር ከሚተዳደሩት የአዳል ክፍለ ሀገራት በጣም ጎልተው የሚታዩት ዘይላ፣ ሁበትና ሀረር ናቸው።

          • ***** *****

“አዳል” ሱልጣኔቱ በታሪክ የሚታወቅበት ትክክለኛ ስም ነው። ይህም ከላይ እንደገለጽኩት በበርካታ የጥንት ሰነዶች ውስጥ የተመዘገበ ስያሜ ከመሆኑም በላይ የሱልጣኔቱ ገዥዎችና የሀገሬውም ህዝብ በመጠሪያነት ይጠቀሙበት ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንድ ጸሀፍት ስያሜውን ከታሪክ ሰነዶች የማውጣት አዝማሚያ እየታየባቸው ነው። ምክንያቱን ባይነግሩንም ከሁኔታዎች መገመት የሚቻል ይመስለኛል። ይኸውም የ“አፋር ህዝብ ስያሜውን እንደ ስድብ ያየዋል” በሚል ሰበብ ነው። በርግጥም የአፋር ህዝብ “አፋር” ተብሎ ነው መጠራት ያለበት። ይህንንም በ1969 ዓ.ል. በገዋኔ ከተማ በተደረገው ታላቅ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አስታውቋል። እኛም ውሳኔውን በሙሉ ልባችን እናከብረዋለን። ስለዚህ “አዳል” የሚለው ስም የ“አፋር” ህዝብ መጠሪያ ሆኖ መቅረብ የለበትም። ነገር ግን በታሪክ ድርሳናት የሰፈረው “አዳል” የመንግስት ስም ከመሆኑ ውጪ የአፋር ህዝብን በተናጠል የሚመለከት ስያሜ አይደለም። ደግሞም ስያሜውን ለመንግስታቸው ያወጡት የጥንቱ ወላስማዎችና የሱልጣኔቱ ህዝቦች በዚህ ስም መጠራቱን ይወዱት ነበር። ዛሬ እኛ ተነስተን ጥንት “አዳል” ሲባል የነበረውን የሱልጣኔታዊ መንግስቱን ስያሜ “አፋር” ወደሚለው ከቀየርነው ታሪክ በጣም ይፋለሳል። ሱልጣኔቱ የበርካታ ህዝቦች ግዛት ሆኖ ሳለ የአንድ ህዝብ ብቻ አድርጎ ማቅረቡም ከባድ ስህተት ነው። ስለሆነም የጥንቱን ሱልጣኔት “አዳል” በሚለው ትክክለኛ ስሙ መጥራት ይገባል።

          • ***** *****

ከዚህ ጋር መጠቀስ ያለበት ሌላ ጉዳይ ደግሞ በ“አዳል” ታሪክ ላይ የሚደረገው የታሪክ ሽሚያ ነው። በዘመናችን የተለቀቁ በርካታ የኢንተርኔት ገጾች “አዳል” የሶማሊዎች ሱልጣኔት እንደነበረና ግዛቱም ሶማሊዎች የሰፈሩበትን አካባቢ (ሶማሊያ፣ ሶማሊላንድ፣ ኦጋዴን ወዘተ...) ብቻ እንደሚያጠቃልል አድርገው ነው የሚጽፉት። እነኝህ የኢንተርኔት ጽሁፎች አንድ የማያስተባብሉት ነገር ቢኖር “ሀረር የአዳል ዋና ከተማ ነበረች” የሚለው ብቻ ነው (ይህንንም ማስተባበል ያልቻሉት በፉቱሑል ሐበሽ ውስጥ የተጻፈ ሀቅ ስለሆነ ነው)። የሶማሊያው ጄኔራል ሙሐመድ ዚያድ በሬ በ1970 ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜም ይህንን የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ እንደ ባለቤትነት ማረጋገጫ (justification) በማቅረብ “ከአዋሽና ዋቤ ሸበሌ ወንዞች በስተምስራቅና ደቡብ ያለው ግዛት በሙሉ የሶማሊያ ህጋዊ መሬት ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ ነዝቶ ነበር። ይሁንና ይህ ሁሉ ዐይን ያወጣ የታሪክ ዘረፋ ነው። በአዳል ግዛት ውስጥ ሶማሊዎች መኖራቸው እርግጠኛ ነገር ቢሆንም አዳልና የዛሬዋ ሶማሊያ በአፈጣጠራቸው፣ በማህበረ ህዝብ ተዋጾኦዋቸውና በታሪካዊ ጉዞአቸው በጭራሽ አይመሳሰሉም። አዳል የጥንታዊው የኢፋት ሱልጣኔት ቀጥተኛ ወራሽ (historical extension) ሆኖ ነው የተቋቋመው። የሱልጣኔቱ መሪዎችም በኢፋት (የዛሬው ሰሜን ምስራቅ ሸዋ ) አካባቢ ማዕከላቸውን ከቆረቆሩት የጥንቱ የወላስማ ሱልጣኖች የዘር ሀረግ ነው የተገኙት። የሱልጣኔቱ ዋና መስራች የሚባሉት ህዝቦች የሚኖሩትም በአሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነው። በአንድ ዘመን “አዳል” ሲባል የነበረው ስፍራ የተጠቃለለው በአሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነው (“አዳል እና ኢሳ” እና “ጨርጨር፣ አዳልና ጋራ ጉራቻ” የሚባሉትን አውራጃዎች ታስታውሱ የለም?)። የዛሬዋ ሶማሊያ አብዛኛው ክፍል በአዳል ሱልጣኔት ስር የነበረ ግዛት ቢሆንም ሱልጣኔቱ ታሪክ ሲሰራ የነበረውም ሆነ ታሪኩ የተቀበረው አሁን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ባለው ዋነኛ መሬቱ ላይ ነው። በአጭር አነጋገር የ“አዳል” መነሻም ሆነ እምብርቱ የነበረው በአሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ነው። በሌላ በኩል አዳል በዘመኑ (ከ13ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን) የነበሩት የኢትዮጵያ ሱልጣኔታዊ ግዛቶች ሁሉ (ሀዲያ፣ባሌ፣ ደዋሮ፣ ሻርካ፣ ደራ፣ አራባባኒ ወዘተ..) የፖለቲካዊና መንፈሳዊ መሪ እንደነበረም የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ። ዛሬ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ 45 በመቶ ያህል የሚሸፍኑት ሙስሊም አማኞች መነሻም በነዚያ የጥንት ሱልጣኔታዊ ግዛቶች የሚኖሩት ሙስሊሞች ናቸው። በዚህ አንጻር ሲታይም የሱልጣኔቱ ታሪክ ህጋዊ ባለቤቶች መላው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንጂ በ1960 ዓ.ል የተወለደው የሶማሊያ መንግስትና የ“ታላቋ ሶማሊያ” መፈክር አቀንቃኞች አይደሉም።

(ምንጭ፡- አፈንዲ ሙተቂ፣ “ሀረር ጌይ-2”- የሀረርና የአዳል ታሪካዊ ወጎች፡ ገጽ 33-35)

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ Herausgegeben von Uhlig, Siegbert, Encyclopaedia Aethiopica. Wiesbaden:Harrassowitz Verlag, 2003, pp.71
  2. ^ I.M Lewis, "The Somali Conquest of Horn of Africa," The Journal of African History, Vol. 1, No. 2. Cambridge University Press, 1960, p. 223.

(ምንጭ፡- አፈንዲ ሙተቂ፣ “ሀረር ጌይ-2”- የሀረርና የአዳል ታሪካዊ ወጎች፡ ገጽ 33-35) አዳል የምለው ስም የጉሣ ስም ይምሰልናል አፋር ውስጥ አዳአል ይምባል ጐሣ አለ ና አዳል የሚለው ስም የጐሣ ስም የምሰልናል