ሃሪ ፖተር ክፍል ስድስት (ፊልም)

ከውክፔዲያ

ሃሪ ፖተር ክፍል ስድስት (English: Harry Potter and the Half Blood Prince; ጥሬ ትርጉሙ: ሃሪ ፖተርና የግማሽ ደም ልዑሉ) እኤአ ፳፻፱ ዓም ለዕይታ የበቃ የብሪቲሽ ፊልም ነው። ፊልሙ በሃሪ ፖተር ተከታታይ ፊልሞች ውስጥ ስድስተኛው ክፍል ሲሆን በዴቪድ የትስ ዳይሬክት ተደርጎ በስቲቭ ክሎቭስ ተፅፎ እንዲሁም በዋርነር ብሮስ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።


ሃሪ ፖተር ክፍል ስድስት

ርዕስ በሌላ ቋንቋ Harry Potter and the Half-Blood Prince (እንግሊዘኛ)
ክፍል(ኦች) ስድስተኛ
የተለቀቀበት ዓመት 15 ጁላይ 2009 እ.አ.አ.
ያዘጋጀው ድርጅት ዋርነር ብሮስ (Warner Bros. Pictures)
ዳይሬክተር ዴቪድ የትስ (David Yates)
አዘጋጅ ዴቪድ ሀይማን (David Heyman)
ዴቪድ ባሮን (David Barron)
ምክትል ዳይሬክተር {{{ምክትል_ዳይሬክተር}}}
ደራሲ ሮውሊንግ (J. K. Rowling)
ሙዚቃ ኒኮላስ ሁፐር (Nicholas Hooper)
ኤዲተር ማርክ ደይ (Mark Day)
ተዋንያን ዳኒኤል ራዲክሊፍ (Daniel Radcliffe)
ሩፐርት ግሪንት (Rupert Grint)
ኢማ ዋትሰን (Emma Watson)
ራልፍ ፊነስ (Ralph Fiennes)
ሚካኤል ጋምቦን Michael Gambon)
ጂም ብሮድቤንት (Jim Broadbent)
አለን ሪክማን (Alan Rickman)
ቶም ፌልተን (Tom Felton)
ሄሊና ቦንሃም (Helena Bonham)
ካርተር (Carter) እና ሌሎችም
የፊልሙ ርዝመት 153 ደቂቃ
ሀገር እንግሊዝ
አሜሪካ
ወጭ 250 ሚሊዮን ዶላር
ገቢ 933,959,197 ዶላር
የፊልም ኢንዱስትሪ ሆሊውድ
የእንግሊዝ ፊልም ኢንዱስትሪ
ድረ ገጽ ይፋ ድረ ገጽ (እንግሊዝኛ)ይህ ፊልም "Harry Potter and the Half Blood Prince" በተሰኘው በፀሀፊ ጄ.ኬ ሮውሊንግ የተፃፈውና እ.ኤ.አ በ፳፻፭ ዓም ለህትመት በበቃው መፅሀፍ ተመስርቶ የተሰራ ሲሆን ፊልሙ የሚተርከውም ሃሪ ፖተር ስድስተኛ የትምህርት አመቱን በሆግዋርትስ የአስማተኛ ትምህርት ቤት የሚያሳልፈውን ጊዜንና የሎርድ ቮልድሞርትን የመርቻ ቁልፍ ስራ የሚሰራበትን ኩነት ነው። እ.ኤ.አ በ፲፭ ጁላይ ፳፻፱ ዓም ሲኒማ ቤትን የረገጠው ይህ ፊልም በተመልካቾችና በሐያስያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል። የዚህ ተከታይ ፊልም ሃሪ ፖተር ክፍል ሰባትኖቬምበር ፳፻፲ ዓም ለዕይታ በቅቷል።

ይዘት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሎርድ ቮልድሞርት በተራው አለም(Muggle World)ና በአስማተኛው አለም የሽብር እጆቹን አሁንም እየዘረጋ ነው። ፕሮፌሰር ዳምብልዶ ሃሪን ከፕሮፌሰር ስለጎርን አስተዋውቆት እንዲቀርበው ያዘዋል። በዚህም ጊዜ ዳምብልዶ ግራ እጁ እንደገረጣና እንደጠቆረ ሃሪ ያስተውላል። ምን እነደሆነ ሃሪ ቢጠይቀውም ዳምብልዶ ሊመልስለት አልፈለገም። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ሃሪ ድራኮ ማልፎይን ከእናቱ ጋር ወደ አንድ የእንጨት መደብር ሲያመራ ይመለከተዋል። እሱም ማልፎይ የአባቱ የሉሲየስ ማልፎይ መታሰርን ተከትሎ የሎርድ ቮልድሞርት ተከታይ ወይም ዴዝ ኢተር(Death Eater) እንደሆነ ጠረጠረ። ይህ ሀሳብ ቅዠት ነው ብለው ጓደኞቹ ሄርመኒና ሮን ቢነግሩትም ሊሰማቸው አልፈለገም። በድብቅም እሱን መከታተልም ጀመረ። በሆግዋርትስም ፕሮፌሰር ስለጎርን አስተማሪያቸው እንደሚሆን በዳምብልዶ ተበሰረ። ሃሪም በፕሮፌሰር ስለጎርን ትምህርቶች ላይ በግማሽ ደም ልዑሉ(The Half Blood Prince) መፅሐፍ አጋዥነት ጥሩ ተሳትፎ እያሳየ የፕሮፌሰሩን ቀልብ ሳበ። ይህን የተመለከተችው ጓደኛው ሄርሞኒም የባለመፅሐፉን ማንነት እንዲያጣራ ደጋግማ ለመነችው እሱ ግን አሻፈረኝ ብሎ ይበልጥኑ ከመፅሐፉ ጋር ያለውን ቁርኝት አጠበቀው።

አንድ ጊዜ ዳምብልዶ ሃሪን ቢሮው ጠርቶ ያለፉትን ትዝታዎችን እንደ መስታወት በሚያሳየው ፔንሲቭ(Pensieve) በሚባለው አስማተኛ እቃ በመጠቀም ከሎርድ ቮልድሞርት ወይም በዛን ጊዜ ቶም ሪድል ተብሎ የሚጠራበትና እሱን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀበት ወቅት አሳየው። ዳምብልዶም አክሎ ቶም በሆግዋርትስ ተማሪ ሳለ ከፕሮፌሰር ስለጎርን ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳላውና ለሱ ምስጢር እንደሚያካፍለው ገለፀለት። በመቀጠልም በአንድ ሰሞን ለእሱ የነገረውን ምስጢር የያዘ ትዝታ(Memory) እንዲቀበለው አዘዘው ለዚህም ቀድሞ እንዳስተዋወቀውና እንዲቀርበው እንደጠየቀው ነገረው። ሃሪም ይህን ተከትሎ ብዙ ጊዜ ሊያወጣጣው ሞከረ ግን አልቻለም።

የማልፎይ ነገር አሁንም አልዋጥለት ያለው ሃሪ ክትትሉን አላቆመም። በአንድ ወቅትም ለዳምብልዶ በተላከ እቃ ውስጥ የሚገል አስማተኛ ቃል(curse) ተያዘ። ሃሪም ቀጥታ ማልፎይን ጠረጠረ። በማልፎይና በፕሮፌሰር ስኔፕ ድብቅ ንግግርም ማልፎይ ዳምብልዶን እንዲገል በቮልድሞርት እንደተላከ ሰማ። ስኔፕም እሱን ሊረዳው ለእናቱ ቃል እንደገባ ነገረው። ይህንንም ለኦርደር ኦፍ ፎኒክስ(Order of Phoenix) አባል ለሆኑት ለሉፒንና ለሮን አባት አርተር ገለፀላቸው እነሱም ስኔፕ የኦርደር ኦፍ ፎኒክሱ አባል እንደሆነና ዳምብልዶም እንደሚያምነውም ነገሩት። በነገሩ ግራ የተጋባው ሃሪ አይኑን ከሁለቱ ማለትም ስኔፕና ማልፎይ ሊነቅል አልፈለገም። ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላም እውነቱን ለማወጣጣት ማልፎይን ተጋፈጠው። ማልፎይም በንዴት ሃሪ ላይ ጥቃት ማድረስ ሞከር። ሃሪ ከግማሽ ደም ልዑሉ የተማረውን አስማተኛ ቃል(Spell) ተጠቀመበት። ይህም አደገኛ ጉዳት ማልፎይ ላይ አደረሰ ስኔፕም በቦታው ተገኝቶ ማልፎይን ከአደጋው አተረፈው በዚህ የተደናገጠው ሃሪ መፅሐፉ መጥፎ ነገር እንዳስተማረው ተረድቶ ከጂኒ ጋር እቃዎች በሚደበቅበት ክፍል ውስጥ ደበቁት። በዛውም ጂኒ ለእሱ ያላትን ፍቅር ገለፀችለት።

ከብዙ ካልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ ሃሪ በስለጎርን ትምህረቶች ጥሩ አቋም በነበረበት ጊዜ ላይ የተሸለመውን ጥሩ እድል አምጪ ፈሳሽ(Liquid Luck) በመጠቀም ከስለጎርን ቮልድሞርት የነገረውን ትዝታ ሰጠው። ዳምብልዶና ሃሪም ተመለከቱት። ከሱም ቮልድሞርት ሆክሮክስ(Hocruxes) የተባለ አስማት የተጠቀመ እንደሆነና ነፍሱንም ሰባት ቦታ ከፍሎት በተለያዩ እቃዎች እንዳስቀመጠው ተረዱ። ዳምብልዱ የጠረጠረው ልክ እንደነበርና የመጀመሪያው ነፍሱ ያየዘው እቃ የእሱ ዲያሪ እንደነበርና ሃሪም ከአራት አመት በፊት እንዳጠፋው ሁለተኛው ደግሞ የእናቱ ቀለበት ሲሆን እሱን ለማጥፋት ሲል ግራ እጁ እንደጠቆረና እንደገረጣ ነገረው። በመጨመርም ሶስተኛውን እንዳገኘና አብረው ማጥፋት እንደሚሻ ገለፀለት። ሃሪም ተስማማ።

ሃሪና ዳምብልዶ የቮልድሞርት ሶስተኛ ነፍስ የተቀመጠበትን እቃ ለመፈለግ ወደ አንድ ዋሻ ያመራሉ በዚያም ዳምብልዶ አድካሚ ፈሳሽ የመጠጣት ክፍያ አስከፍሎት ሶስተኛውን ወይም የአንገት ሃብሉን አገኙት። ሀብሉን አግኝተውት እንደተመለሱም ዳምብልዶ በመድከሙ ስኔፕን እንዲጠራለት ሃሪን አዘዘው። ሃሪም ስኔፕን ለመጥራት ልክ ሲሄድ ማልፎይ ዳምብልዶን ሊገለው መጣ። ዳምብልዶም ማልፎይ ገዳይ እንዳልሆነና ሊገለው እንደሚፈልግ ከብዙ ጊዜ በፊት ያውቅ እንደ ነበር በእርጋታ ነገረው። ማልፎይን ተከትሎም ለሌሎች የቮልድሞርት ተከታዮች በቦታው ተገኙ። ዳምብልዶም ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት እንዴት ተከታዮቹ ወደ ውስጥ እንደዘለቁ ጠየቀው እሱም አንድ እንጨት መደብር ውስጥ ያለ ቁም ሳጥን ትምህርት ቤቱ ውስጥ ሌላ መንታ ቁምሳጥን እንዳለውና ሰውን አንዱ ቁምሳጥን ካለበት ቦታ ወደሌላኛው ቁምሳጥን እንደሚያዘዋውር ነገረው። ዳምብልዶም ደጋግሞ እንዳይገለው ቢጠይቀውም ማልፎይ እንደፈራና ካልገደለው ቮልድሞርት እንደሚገለው እንባ እየተናነቀው ነገረው። ይህንን ሁኔታ በድብቅ የሚከታተለው ሃሪ ስኔፕ ከቦታው እንዳይነቃነቅ ምልክት ሰጠው። ስኔፕም በቦታው በማምራት የዳምብልዶን አይን እየተመለከተ ዳምብልዶን ገድሎት ከቦታው ሸሸ።

ይህንን አይቶ የደረቀው ሃሪ ስኔፕን በሩጫ ተከተለው። ሊጎዳውም ስለፈለገ ከመፅሐፉ የወሰደውን ቃል ተጠቀመበት። ስኔፕም በቀላሉ ጥቃቱን ተከላከለ ቀርቦም ይህንን አስማተኛ ቃል እራሱ እንደፈጠረና የመፅሀፉ ባለቤት(ባለግማሽ ደም ልዑል) እሱ እንደሆነ ነገረው። በመጨረሻም ሃሪ ዳምብልዶ ሲገደል እያየ ምንም አለማድረጉ እንደቆጨውና እሱ የጀመረውን ስራ ማለትም ነፍሶቹን እንደሚፈልግ ለጓደኞቹ ነገራቸው እነሱም እንደሚረዱት ቃል ገቡ።

ተዋንያንና ገፀባህሪያት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • ዳንኤል ራድክሊፍ እንደ ሃሪ ፖተር

ሃሪ ፖተር ገና ልጅ ሳለ ጨካኑ አስማተኛ ቮልድሞርት እናትና አባቱን የገደለበትና በእሱም ላይ የግድያ ሙከራ ያመለጠ ሲሆን በዚህም ሰበብ ቮልድሞርትና ሃሪ ቀንደኛ ጠላት ናቸው። በዚህ ክፍል ውስጥ ባለ፲፭ቱ ታዳጊ ሃሪ ቮልድሞርትን ለመርታት ከዳምብልዶ ጋር ሆኖ ሲፋለም እናየዋለን። ዳንኤል ራድክሊፍም ከመጀመሪያው ክፍል ጀምሮ ሃሪን ሆኖ የተወነው አሁንም ለሰባተኛው ክፍል አንደሚተውነው ፈርሟል።

  • ኤማ ዋትሰን እንደ ሄርሞኒ ግሬንጀር

የሃሪ ፖተር ጓደኛና የበሰለ አስተሳሰብ ያላት ልጅ ናት። በዚህ ፊልም ላይም ከጓደኛዋ ሮን ጋር ፍቅር እንደያዛት እንመለከታለን።

  • ሩፔርት ግሪንት እንደ ሮን ዊዝሊ

የሃሪና የሄርሞኒ ጓደኛ። ሮን የአስማተኞች ጨዋታ ላይ ተካፋይ ሆኖ ድል ተቀዳጅቷል።

  • ሚካኤል ጋምበን እንደ ፕሮፌሰር ዳምብልዶ

በአስማተኛው አለም ውስጥ በጣም ብልጥና ብልህ አስማተኛ ነው። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ቮልድሞርትን ሲዋጋ እንደነበርና እሱን ለመዋጋትም ኦርደር ኦፍ ፊኒክስ የተባለ ቡድን አቋቁሟል። በዚህ ክፍልም በባልደረባው በስኔፕ ተክዶ ሞቷል።

  • አላን ሪክማን እንደ ፕሮፌሰር ስኔፕ

የሆግዋርትስ ትምህርት ቤት መምህርና በፊት ቮልድሞርት ተከታይ። ሃሪ አሁንም ቢሆን ለቮልድሞርት እንደሚሰራ ቢጠረጥርም ጥርጣሬው በጓደኞቹ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። በመጨረሻም ስኔፕ ዳምብልዶን ገድሎት ጥርጣሬው ልክ እንደነበር እንመለከታለን።

  • ቶም ፌልተን እንደ ድሬኮ ማልፎይ

ማልፎይ ከድሮ ጀምሮ ከሃሪ ጋር አይስማሙም ነበር። አሁንም ጠላትነታቸው ጣሪያ ነክቷል። በቮልድሞርት ዳምብልዶን እንዲገል ቢታዘዝም ሊያሳካ አልቻለም።

  • ጂም ብሮድቤንት እንደ ፕሮፌሰር ስለጎርን

የሆግዋርት ትምህርት ቤት መምህርና በአንድ ጊዜ የቮልድሞርት መምህር። ሃሪ ከስለጎርን ቮልድሞርት የነገረውን ምስጢር ለማወቅ ይሞክራል። ከብዙ ሙከራ በኋላም ተሳክቶለታል።

  • ራልፍ ፊንስ እንደ ሎርድ ቮልድሞርት

ስሙ በፊልሙ ቢጠቀስም በአካል አልታየም። ቮልድሞርት ከመቼውም በላይ ሀይሉ እየጨመረ መጥቷል። ሃሪም እሱን መውጊያ ምስጢር አውቋል።