ሌቱም አይነጋልኝ
ሌቱም አይነጋልኝ በውቤ በረሃ በ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. ተጀምሮ በፈረንሳይ አገር ኤክስ አን ፕሮቫንስ የተፈጸመ መጽሐፍ ነው።
ደራሲው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር መጽሐፉ እንዲታተም እሱ ደንታ ባይኖረውም...በመጽሐፉ ውስጥ እንደጠቀሰው «እኔ 'ኮ ያደረብኝ ለዘብተኛ ልዝብ ዛር በበቂ ደሞዝና 'ትርፍ' ስኣት እያምበሻበሸ ስላበረታታኝ ፃፍኩ'ንጂ፤ ይታተም አይታተም ደንታ አልነበረኝም።»
ወዳጆቹ ቢሞክሩም በመንግስት ሳንሱር «ለአንባቢያን የማይገቡ ግልጽ የወሲብ ቃላቶች አሉበት» በሚል ምክንያት እየታገደ ለሃያ አምስት ዓመታት በአንባቢዎቹ እጆች በእጅ እየተገለበጠ ሲነበብ ኖሯል።
በአሁኑ ሰዓት በመጀመሪያ እነዚያ ወሲባዊ ቃላቶችን «ለስለስ» ባሉ ቃላቶች በመተካት ለአንባቢያን እንዲደርስ መጽሐፉ ታትሞ ለገብያ የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም በአገራችን አቆጣጠር በ1999 ያንኑ መጽሐፍ ደራሲው የተጠቀመባቸውን ቃላቶች ትክክለኛ ግልባጭ የያዘ «ሌቱም አይነጋልኝ...እንደ ወረደ» ለአንባቢያን ቀርቧል።
ስብሐትም እዚሁ ዕትም ላይ «እንግዲህ አንባብያን ሆይ፤ በገዛ ታሪኬ፤ በገዛ ሦስት ሺ ዘመን ያገሬ ክርስትና፤ በገዛ ውቤ በረሀዬ፤ የኖርኩትን፤ ያየሁትን፤ የሰማሁትን፤ በተቻለኝ አቅምና በታደልኩት የትረካ ተሰጥዎ ለአራዳዎችም ለፋራዎችም ያገሬ ልጆች (ያውም ከሊቅ እስከ ደቂቅ!) ለምን አላበረክትላቸውም? አራዳዎቹም አብረውኝ ደስ ይላቸዋል፤ ፋራዎቹም ድብርታቸው ይብስባቸውና አንጀቴ ቅቤ ይጠጣል፤ ቀኑ የፆም ቢሆንም፤ እና እኔ የቄስ ልጅ፤ የደብተራ የልጅ ልጅ በመሆኔ የምኮራ ብሆንም። ያውም መብቴ በህገ መንግስት እየተጠበቀልኝ! ለሁላችሁም እንሆ በረከት!» እያለ ይኼንን የሚይስቅ፤ የሚያዝናና እና የ'ውቤ በርህን' የ፲፱፻፶ዎች ታሪክ 'የሚያስተምረን' መጽሐፍ አቅርቦልናል።