ሐረ ሼይጣን
ሐረ ሼይጣን | |
«ሐረ ሼይጣን» | |
ሐረ ሸይጣን ከአዲስ አበባ ወደ ደቡባዊው ኢትዮጵያ ክፍል ፻፵፫ ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ የሚያገኙት ሐይቅ ሐረ ሸይጣን ይባላል፡፡ የሚገኘውም በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ርእሰ ከተማ ወራቤ በስተሰሜን አቅጣጫ ፴ ኪሎ ሜትር ተጉዘውም ያገኙታል፡፡
ሐይቁ ከኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የሐይቁ ይዘት አስገራሚ ሁኔታዎች አሉበት፡- ሐይቁ የሚገኘው ከመሬት ንጣፍ በታች ሲሆን፣ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ሀብቶችና ገጽታዎች እንዲሁም ክስተቶችን የያዘ ሐይቅ ነው፡፡ በመሆኑም የገበቴ ቅርጽ ያለውን ሐይቅ ከጉድጓዱ አፋፍ አንስቶ ቁልቁል ውኃው እስካለበት ለመድረስ በአማካይ የ ፪፻፷ ሜትር ርቀት ጉዞ ይጠይቃል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአፋፉ እስከ ውኃው ያለው አምዳዊ (Vertical) ርቀት አማካይ ከፍታ ፻፱ ሜትር ነው፡፡ ከዳገቱ አፋፍ በመነሳት ድንጋይ ወርውሮ ለማስገባት ፪፻፴፯ ሜትር የጎንዮሽ (Horizontally) የመወርወር አቅምን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ድንጋይ ሲወረወር ወደ ውኃ የማይዘልቅበት ዋናው ምክንያት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡
የሐረ ሸይጣን ሐይቅ የውኃ ቀለም ወቅትን ጠብቆ የሚለያይ ሲሆን፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ (በተለይም የቀድሞው) የተለያዩ ትርጓሜዎችን ይሰጡት ነበር፡፡ ነገር ግን ከሰገላዊ እይታ፣ ከሐይቁ አፈጣጠርና ይዘት ጋር ሲታይ የውኃው መልክ የሚቀያየረው ከአካባቢው ነጸብራቅ (Reflection) ነው፡፡
ስለሐይቁ አፈጣጠር ኅብረተሰቡ የሚተርከው ነገር አለው፡፡ በአፈታሪክነትም ይጠቀሳል፡፡ አፈታሪኩም ከሰገላዊ ምልከታ ጋር የሚገናዘብበት አጋጣሚም አለው፡፡
የሐረ ሸይጣን ሐይቅ አፈጣጠር ከተፈጥሮ ውስጣዊ ኃይል አንዱ በሆነው የእሳተ ገሞራ ነው፡፡ እሳተ ገሞራ የመሬትን ውስጣዊ አካል በእሳት በማቅለጥ ወደ መሬት ውጫዊ አካል የቀለጡ አፈሮችንና አለቶችን ይዞ በመዝለቅ ቀዳዳ ይፈጥራል፡፡ ከከርሰ ምድር ውኃ የሚያገናኝ ሳህን/ገበቴ የመሰለ ጉድጓድ በመፍጠር በውኃ እንዲሞላ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሰዎች እንደሚናገሩት አልፎ አልፎ ውኃው የተቃጠለ ዘይት ዓይነት ሽታ እንዳለው የተገነዘቡትን ገልጸዋል፡፡ የሐረ ሸይጣን ሐይቅ ከመሬት ገጽታ በታች መገኘት፣ የገበቴ ቅርጽ ያለው መሆኑ፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መልክዓ ምድራዊ ገጽታዎች ወይም አነስተኛ ኮረብታዎች፣ ተፈጥሯዊ ዋሻዎቸው፣ ፍል ውኃዎች፣ ሌሎች ሐይቆች፣ እሳተ ገሞራዎች በስምጥ ሸለቆ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኝ መሆኑና በአካባቢው የሚገኙ ድንጋዮች እና አፈሮች ጋር በተያያዘ ስንመለከተው ሐይቁ የተፈጠረው በአንድ ወቅት በነበረ የእሳተ ገሞራ ውጤት መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በሰገላዊ አጠራሩ ክሬተር ሌክ (Crator Lake) ይባላል፡፡
ኅብረተሰቡ በአፈታሪክ እንደሚለው ሐይቁ የተፈጠረው ኑር ሁሴን ከሚባሉ የሃይማኖት አባት (ወለይ) ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው፡፡ ቦታው በሜዳ ላይ የሰፈረ ከተማ እንደነበረና በከተማው የነበሩ ሰዎች እንግድነታቸውን ስላልተቀበሏቸው በመራገማቸው ከተማው ሙሉ በሙሉ እንደሰመጠና በቦታው ትንሽ ውኃ በመፈጠሩ ይህ ውኃ ቀስ በቀስ እየሰፋ ሄዶ ያሁኑን ሐረ ሸይጣን እንደፈጠረ በአፈታሪክ ይነገራል፡፡
የሐይቁ ስያሜ አመጣጥም ከቦታው ምትሃታዊ ክስተቶች ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡
"ሐረ ሸይጣን" ቃሉ የኦሮምኛ እንደሆነና ትርጉሙም የሰይጣ ሐይቅ ማለት ነው ሲሉ በሌላ በኩልም "ሐር-አሽ-እጣን" ከሚለው የስልጥኛ ቃል የተወሰደ ሆኖ ትርጉሙም "እጣን አቀጣጥል/አጭስ" ማለት ነው ይላሉ፡፡
በሐይቁ ዙርያ ያሉ ባህላዊ አመለካከቶችም ከአፈጣጠሩና ይዘቱ እንዲሁም ካለው ምትሃታዊ ክስተቶች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹም፡- ምትሃታዊ ክስተቶች የተባሉትም ቀለሙን በመቀያየርና ከዳገቱ አፋፍ ላይ ድንጋይ ወርውሮ ለማስገባት አለመቻሉና በንጉሡ ዘመን የነበሩ የተወሰኑ ጎሳዎች ለምትሃታዊ ኃይሉ የተለያዩ አምልኮአዊ ክንውኖች በማድረጋቸው ነው፡፡
“ሐረ ሸይጣን” ፣ ሪፖርተር (በሔኖክ ያሬድ)፣ 01 September 2010 http://www.ethiopianreporter.com/pre-rep/index.php?option=com_content&view=article&id=3314:2010-09-01-07-09-34&catid=105:2009-11-13-13-47-17&Itemid=625