ሚስቶች በኖህ መርከብ ላይ

ከውክፔዲያ

ማየ አይህ በፊት በነበሩ ዕለታት ስለ ኖሩ በኖህ መርከብ ላይ ስለ ተገኙ ስለ አራቱ ሴቶች ኦሪት ዘፍጥረት ምንም እንኳን ዝም ቢል፣ ከሌላ ምንጭ ስለነዚሁ ሴቶችና በተለይ ስለ ስሞቻቸው የተገኘው አፈ ታሪክ በርካታ ነው።

በጥንታውያን እምነት ዘንድ፣ የሴም፣ የካምና የያፌት ሚስቶች ዕጅግ የረዘማቸው ዕድሜ ሲኖራቸው ከመጠን ይልቅ ለብዙ መቶ ዓመታት ኑረው ለያንዳንዱ ትውልድ ትንቢት እየተናገሩ ኖሩ። እነኚህ ሲቢሎች ተብለው ለግሪኮችሮማውያንም እንደ ቅዱሳን መጻሕፍት የተቆጠሩት የሲቢሊን መጻሕፍት ደራሲዎች እንደ ነበሩ ታመነ። የሮማውያን ቅጂ በ397 ዓ.ም. አካባቢ በእሳት ተቃጥ ዛሬ የሚታወቁ የሲቢሊን ራዕዮች የተባሉት ሰነዶች ኦሪጂናል መሆናቸው ለምሁሮች አይመስላቸውም። ከመጀመርያ ሲቡሎች በኋላ ሌሎች ሲቢሎች እንደ ተከተሉ ለንግሮቹም እንደ ጨመሩ ይታስባል።

መጽሐፈ ኩፋሌ የሴም፣ የካምና የያፌት ሚስቶች እንዲሁ ተብለው ይሰየማሉ፤

  • የሴም ሚስት፣ ሰደቀተልባብ
  • የካም ሚስት፣ አኤልታማኡክ (ወይም በሌላ ትርጉም ናኤልታማኡክ)
  • የያፌት ሚስት፣ አዶታነሌስ (ወይም በሌላ ትርጉም አዳታነሥስ) ናቸው።

ከዚህ በላይ ሦስቱ የኖህ ልጆች ከጥቂት ዓመት በኋላ ከአራራት ሠፈር በየአቅጣጫው ሂደው ለሰው ልጆች ሁሉ እናቶቻቸው ለሆኑት ለሚስቶቻቸው ስሞች የተባሉ 3 መንደሮች እንደ መሠረቱ ይታረካል።

በኋላ ዘመን የክርስቲያን ጸሓፊ ቅዱስ አቡሊድስ (227 ዓ.ም. የሞቱ) በጽርዕ ታርጉም ዘንድ ለዚህ ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ መዘገቡ። ነገር ግን እዚህ የሴምና የካም ሚስቶች ስሞች እንዳለዋወጡ ይመስላል። እሱ እንዲሁ፦ «የኖህ ልጆች ሚስቶች ስሞች አንዲሁ ናቸው፤ የሴም ሚስት፣ ናሐላጥ ማሕኑቅ፤ የካምም ሚስት፣ ዘድቃጥ ናቡ፣ የያፈትም ሚስት አራጥቃ ይባላሉ» ብሎ ጻፈ።

ጆን ጊል (1697-1771 እ.ኤ.አ.) በመጽሓፍ ቅዱስ ነክ አስተያይቶቹ ስለ አንድ የዓረብ አፈ ታሪክ የጻፈው እንዲሁ ነው፤ «የሴም ሚስት ስም ዛልበጥ ወይም ዛሊጥ ወይም ሳሊት ሲሆን፣ የካምም ደግሞ ናሓላጥ ተባለች፣ የያፌትም ደግሞ አረሢሢያ ተባለች።

ኪታብ አል-ማጋል የተባለው ጥንታዊ አረብኛ መጽሐፍ (ከ'ቄሌምንጦስ መጻሕፍት' መሃል)፣ በጽርዕ የተጻፈው መጽሐፍ የመዝገቦች ዋሻ (350 ዓ.ም. ገዳማ) እና የእስክንድርያ ግሪክ ኦርቶዶክስ አቡነ ዩቲኪዮስ (920 ዓ.ም. ገደማ) ሁሉ ሲስማሙ የኖህን ሚስት ሃይኬል ይሏታል፤ እርስዋም የናሙስ ልጅ፣ ናሙስም የሄኖክ ሴት ልጅ፣ ይህም ሄኖክ የማቱሳላ ወንድም እንደ ነበሩ ይላሉ። ኪታብ አል-ማጋል ደግሞ የሴም ሚስት የናሲህ ልጅ ልያ ብሎ ይሰይማታል።

የሳላሚስ አጲፋንዮስ የጻፈው ፓናሪዮን ደግሞ የኖህ ሚስት ባርጤኖስ ይላታል። በ5ኛ ክፍለ ዘመን አካባቢ በግዕዝ የተሠራው መጽሐፈ አዳምና ሕይዋን ግን የኖህ ሚስት ሃይካል ሲጠራት ይቺ የአባራዝ ልጅ፣ አባራዝም የሄኖስ ልጆች ሴት ልጅ ናት ይላል። አንዳንድ ጸሐፊ ስለዚህ የአጲፋንዮስ 'ባርጤኖስ' ማለት ከእብራይስጥ 'ባጥ-ኤኖስ' መሆኑን አጠቁሟል።[1].

በ'ሲቢሊን ራዕዮች' ዘንድ፣ ከሲቢሎቹ የአንዲቱ ስም ለዛልበጥ ተመሳሳይ ነበረ፤ እሷም የ«ባቢሎን ሲቢል» ሳምበጥ ነበረች። ከጥፋት ውሃ 900 አመት በኋላ ወደ ግሪክ አገር ሄዳ የንግሮች ጽሑፍ እንደ ጀመረች ብላ ጻፈች። ከዚያ በላይ የጻፈችው ጽሁፍ ከማየ አይህ አስቀድሞ የነበሩ የቤተሠቧ ስሞች ይታርካል። እነሱም አባቷ ግኖስቲስ፣ እናቷ ኪርኬ፤ እህቷም ዒሲስ ናቸው። በሌሎች ጥንታዊ ምንጮች ደግሞ ሳባ የምትባል ሲቡል ኖረች።

15ኛ ክፍለ ዘመን አውሮፓዊ መነኩሴ አኒዮ ዳ ቪተርቦ ዘንድ፣ ከለዳዊቤሮሶስ (280 ዓክልበ ያህል የጻፈ) የልጆቹ ሚስቶች ፓንዶራ፣ ኖኤላ፣ ኖኤግላ የኖህም ሚስት ቲቴያ ተብለው እንደ ተሰየሙ ብለው ነበር። ነገር ግን ይህ አኒዮ ዛሬ አታላይ ጸሐፊ እንደ ነበር ይታመናል[1]

አይርላንድ አፈ ታሪክ ስለ ሦስቱ ልጆችና ስለ ሚስቶቻቸው የሚተረተው ብዙ አለ። በዚሁ ምንጭ ሚስቶቹ ኦላ፣ ኦሊቫ፣ ኦሊቫኒ ይባላሉ። እነኚህም ስሞች የተወሰዱ ኮዴክስ ጁኒየስ ከተባለው ጥንታዊ (700 ዓ.ም.) እንግሊዝ ብራና ጥቅል ይመስላል። ይኸው ጽሕፈት እንደ ረጅም ግጥም ሆኖ በገጣሚው በካድሞን እንደተጻፈ ይታሥባል። እዚህ ደግሞ የኖህ ሚስት ፔርኮባ ትባላለች።

ሀንጋሪ አፈ ታሪክ ደግሞ ስለ ያፌትና ኤነሕ ስለ ተባለችው ስለ ሚስቱ አንዳንድ ተረት አለበት። ይህ መረጃ የሚገኘው የአንጾኪያ ጳጳስ ሲጊልበርት ከተጻፉት ዜና መዋዕል እንደ ሆነ ይባላል።

በደቡብ ኢራቅ በሚኖሩት በጥንታዊ ማንዳያውያን ሐይማኖት ተከታዮች መጻሕፍት ዘንድ፤ የኖህ ሚስት ኑራይታ ወይም አኑራይጣ ተባለች።

ግብጽ 1-3 ክፍለ ዘመናት ዓ.ም. የተገኘው ግኖስቲክ ሃይማኖት መጻሕፍት ዘንድ የኖህ ሚስት ኖሬያ ስትሆን መጽሐፈ ኖሬያ የሚባል ጽሕፈት ነበራቸው።

አይሁዳዊ ሚድራሽ 'ራባ' እና በ11ኛ ክፍለ-ዘመን የኖረው አይሁድ ጸሐፊ ራሺ እንዳለው የኖህ ሚስት የላሜህ ሴት ልጅና የቱባልቃይን እኅት ናዕማህ ነበረች። እንዲሁም ከ1618 ዓ.ም. ብቻ በሚታወቀው ሚድራሽ «ያሻር መጽሐፍ»፣ የኖህ ሚስት ስም የሄኖክ ልጅ ናዕማህ ተባለች። ነገር ግን፤ ጥንታዊ መጽሀፈ ኩፋሌ ስምዋ አምዛራ ተብሎ ይሰጣል። «ናዕማህ» የሚለው የካም ሚስት ስም ለኖህ ሚስት ስም በአይሁድ ልማድ እንደ ተሳተ ጆን ጊል ሐሳቡን አቅርቧል።

ሮዚክሩስ («የጽጌ ረዳ መስቀል ወንድማማችነት»፤ ምስጢራዊ ማኅበር) ጽሕፈት ኮምት ደ ጋባሊስ (1672 ዓ.ም.) ዘንድ፣ የኖህ ሚስት ስም ቨስታ ትባላለች።

በመጨረሻም፣ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው በሞርሞን ሃይማኖት ('የየሱስ ክርስቶች መጨረሻ ዘመን ቅዱሳን') መጻሕፍት ዘንድ፣ የካም ሚስት ስም ኢጅፕተስ ነበረ።

  1. ^ A Dictionary of Christian Biography, Literature, Sects... p. 268