ምኒልክ ወስናቸው

ከውክፔዲያ

ምኒልክ ወስናቸው ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ድምፃዊ ሲሆኑ ጋሽ ጀምበሬ በመባልም ይጠራሉ።[1]

የህይወት ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ሐረርጌ ያደጉት ምኒልክ ወስናቸው የ፪ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጋምሰው ለ፭ ዓመታት ያህል በፈረንሣይ ትምህርት ቤት ካጠኑ በኋላ በ፲፰ ዓመት ዕድሜያቸው በቀ.ኃ.ሥ. ቲያትር ቤት በድምፃዊነት ተቀጠሩ።[1]

ምኒልክ የመድረክ ላይ ጧፏቸውን «አልማዝ እያሰብኩሽ» በሚል ምርጥ ዜማ ካበሩ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፋጣን የሆነ የኪነ ጥበብ ሰውነታቸውን በማስመስከር አንቱ ከሚያሰኝ ደረጃ ደርሰዋል።[1]

የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃ ስልት በሱዳን፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያ፣ በኬኒያ፣ በሶቭየት ሕብረትና በአሜሪካ በመሳሰሉት አገሮች በመዘዋወር ያስተዋወቁ የባህል አምባሳደር ነበሩ።[1]

ምኒልክ የሚደነቁት ቀደም ሲል ባቀረቡት የአማርኛ ሙዚቃቸው ብቻ ሳይሆን የተዋጣላቸው ዓለም አቀፍ ወይም በሙዚቃ ባለሙያዎች አጠራር የኦፔራ ዜማዎችን የሚጫወቱ ልዩ ተሰጥኦ የነበራቸው የኪነ ጥበብ ፈርጥ ሲሆኑ ቀደም ሲል በሸክላ፣ ካሴትና ሲዲ ያስቀረጿቸው ሙዚቃዎች ለትውልድ የሚተላለፉ ቅርሶች ሆነው ሲዘከሩ ይኖራሉ።[1]

ምኒልክ የብሔራዊ ቲያትር ቤት የድምፃውያን ቁንጮ የነበሩ ሲሆን ቆየት ሲሉ ካቀረቡዋቸው ዜማዎች «አፈር አትንፈጊኝ» የተሰኘው እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከዘፈኑዋቸው ውስጥ «እትት በረደኝ፣ ፍቅር ይበርዳል እንዴ» እና «ጋሽ ጀምበሬ» የተሰኙ ከፍተኛ ተደማጭነትን አግኝተዋል።[1]

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ "ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 31-32". Archived from the original on 2011-09-29. በ2010-12-18 የተወሰደ.