ሴሚራሚስ

ከውክፔዲያ

ሴሚራሚስ (ሻሚራም) በድሮ የግሪክ ታሪክ ጸሃፊዎች ዘንድ በጥንታዊው ዘመን የአሦር ንጉስ ኒኑስ ንግሥት ነበረች። በተለይ በዲዮዶሮስ ሲኩሉስ ጽሑፍ የእርሷ አፈ ታሪክ ይታወቃል። ዲዮዶሮስ እንደሚለው በአስቄሎንሶርያ ተወልዳ እናቷ ግማሽ ሰው ግማሽ አሣ የሆነች አድባር እንደ ነበረች ይባል ነበር። ሴሚራሚስ ከኒኑስ ጦር ሻለቆች አንዱን ዖኔስ የተባለውን አገባች። በባክትርያ ላይ ሲዘመት፣ ሴሚራሚስ በልብሷ ራሷን እንደ ወንድ አስመሰለችና በዘመቻው በጣም ጀግና ነበረች። ስለዚህ ኒኑስ ወደዳትና ከዖኔስ በግድ ለራሱ ወሰዳት። ዖነስም ራሱን ገደለ። ከዚህ በኋላ ለኒኑስ ልጁን ኒንያስ (ናንያስ)ን ወለደችለት።

ኒኑስ ከሞተ በኋላ ሴሚራሚስ መንግሥቱን ለ42 ዓመታት ያዘች። ትልቅ ከተማ በባቢሎን ሠራች። አንዳንድ ቤተ መንግሥት ደግሞ በፋርስ አሠራች። ዲዮዶሮስ እንደሚለን የቤኂስቱን ጽሑፍ በተራራ ገደል ላይ አስቀረጸች። አሁን እንደሚታወቀው ግን ይህን ጽሑፍ ያስቀረጸው የፋርስ ንጉሥ ፩ ዳርዮስ ነበረ። ከዚህ በላይ ወደ ሊብያና አይቲዮፒያ (አፍሪካ) እንደ ዘመተች ይለናል። በኋላ ወደ ሕንድ ንጉስ ስትራቶባቴስ ላይ ስትዘምት በሥራዊቷ ዝሆኖች እንደነበሯት ለማስመስል ብዙ ሀሣዊ ዝሆኖች እንዲፈጠሩ አደረገች ይባላል። ይህ ዘዴ መጀመርያ ቢከናወንም የስትራቶባቴስ ሥራዊት ግን በመጨረሻ ወደ ኢንዱስ ወንዝ ምዕራብ አስመለሳቸው።