ቀንደ መሬት

ከውክፔዲያ
በማልታ-ቡረት ሥልጣኔ ሳይቤሪያ የተገኘ የቀንደ መሬት ስዕል በዝሆን ጥርስ ላይ

ቀንደ መሬት (እንግሊዝኛ፦ Mammoth /ማሞጥ/) በአውርስያና በስሜን አሜሪካ የነበረ በጥንት የጠፋ የዝሆን አስተኔ አባል ነበረ። ከዛሬው የአፍሪካ ወይም የእስያ ዝሆን እጅግ ጸጉራም ዝርዮች ነበሩ።

ስሙ Mammoth እና ተመሳሳይ ስያሜዎች በሌሎች ልሳናት የደረሱ ከሩስኛ /ማማንት/ እንደ ነበር ይታመናል፤ ይህም ከአንድ ኡራሊክ ቋንቋ እንደ ማንሲኛ (ሳይቤሪያ) ቃል *መንግ-ኦንት እንደ ደረሰ ይታመናል፤ የዚህም ማለት ከ*መንግ («መሬት») እና ከ*ኦንት («ቀንድ») ደረሰ። የዚህም ምክንያት እንስሳው ብዙ ጊዜ ከጠፋ በኋላ በ1700ዎቹ ዓም በተለይ በሳይቤሪያ የነበሩ ብሔሮች በመሬት ወይም በበረዶ ካገኙት ታላላቅ ቀንዶች ብቻ መኖሩን ያወቁት ነበር። እነዚህ «ቀንዶች» በውነት የዝሆን ጥርስ ነበሩ፤ ስለዚያ ነው ስያሜው «ቀንደ መሬት» ሆነ።

አሁን እንደምናውቀው በቅድመ-ታሪክ ይህ እንስሳ በሰው ልጅ መካከል በአውሮፓና እስያ ይኖር ነበር፤ የጠፋበት ዋና ምክንያት ማደን ነበረ። የአውሮፓ ሊቃውንት እንደገመቱ ይህ የሆነ ከ10,000 እስከ 2,000 ዓክልበ. ድረስ ነበር፤ ለዚህ ያህል ረጅም ጊዜ ሁሉ ግን (8000 አመታት) ተከታታይ መዝገብ መሥራት ይከብዳል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወይም በጥቂት መቶ አመት ከማደን ለምን እንዳልጠፉ አይገልጹም። በጣም በራቁ በአንዳንድ የሳይቤሪያ ወይም አርክቲክ ደሴቶች ላይ እስከ 1650 ዓክልበ. ድረስ እንደ ቆየ ይታስባል።

ሥነ ቅርስ በእርግጥ የምናውቀው መጀመርያ በአውሮፓና በእስያ የሰፈሩት የሰው ዘሮች ቀንደ መሬቱን በማደን ከጥርሱ ብዙ እቃዎች፣ አሻንጉሊቶች፣ ጣኦቶች፣ አሸንክታቦች ወይም ጌጦች ይቀርጹ ነበር። በዚህ መካከል የ«ቀንደ መሬት»ና ሌሎች አራዊት ምስሎች ይቀርጹ ነበር።

በአንድ ሥፍራ በሳይቤሪያ በሥነ-ቅርሳዊው ማልታ-ቡረት ሥልጣኔ (ባይካል ሐይቅ አካባቢ) የዝሆን ጥርስ የድሪ-ተንጠልጣይ ጌጦች ተገኙ፣ ለወንዶች የበራሪ ይብራ፣ ለሴቶችም የሴት ቅርጽ ከድሪ እንደ ለበሱ ይመስላል።