ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
ቅዱስ ዮሴፍ | |
---|---|
የቅዱስ ዮሴፍ የሥራ መደብር | |
አረጋዊ ፃድቅ | |
የኖረው | በመጨረሻዎቹ ዓ.ዓ. ና በመጀመሪያዎቹ ዓ.ም. በቤተልሄም በገሊላ በናዝሬት በኢየሩሳሌም |
የሚከበረው | በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች |
በዓለ ንግሥ |
ሐምሌ ፳፮ ቀን ዕረፍቱ ና ግንቦት ፳፬ ቀን ስደቱ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን) ማርች ፲፱ (በምዕራባውያን ክርስትና) ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጀመሪያው እሁድ (በምሥራቃውያን ክርስትና) |
ቅዱስ ዮሴፍ በዕብራይስጥ: יוֹסֵף ፣ በሮማውያን ማለት በላቲን : Yosef ፣ በግሪክ : Ἰωσήφ)
በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ አካባቢ ስም አጠራራቸው ከከበረ ደጋግ እስራኤላውያን አንዱ የእመቤታችን ጠባቂ አረጋዊ ቅዱስ ነው ። ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ከንጉሥ ዳዊት ሲሆን አባቱ ያዕቆብ እናቱም ዮሐዳ ይባላሉ ።
ቅዱስ ዮሴፍ ድግር ጠራቢ ነበር፤ ይህም ማለት ለእርሻ አገልግሎት በበሬ ለማረስ የሚያስፈልጉ ሞፈርና ቀንበር የሚሠራ ነበር ፡፡
በጉብዝናው ወራት የእመቤታችንን አክስት ማርያምን አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ አርጅቷል ። ከልጆቹም ዮሳ ፣ ያዕቆብ ፣ ይሁዳ ፣ ስምዖንና ሰሎሜ በቅዱስ መጽሐፍ ተዘክረዋል። ቅዱስ ዮሴፍ እድሜው ሰባ አምስት ሲሆን ሚስቱ ማርያም ሞተችበት ።
ባለቤቱ ካረፈች ከጥቂት ወራት በኋላም አይሁድ በምቀኝነት ድንግል ማርያምን ከቤተክህነት አስወጡልን ብለው ግብግብ በፈጠሩ ጊዜ "ልማ በሥሉስ ጥፋ በሥሉስ" እንዲሉ በሦስት ነገር ተመስክሮለት በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ድንግል ማርያምን ሊያገለግል ተመረጠ ። በወንጌልም "እጮኛ" የሚለውም ለዚያ ነው (የታጨው ለአገልግሎት ስለሆነ) ።
እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ በሁለት ወገን ልጁ (ዘመዱ) ናት:
- የሚስቱ ማርያም የእኅት (የሐና) ልጅ ናት ።
- የቅድመ አያቱ የዓላዛር የልጅ ልጅ ናት ።
ደጉ ሽማግሌ ቅዱስ ዮሴፍ ምንም ቢያረጅ እመቤታችንን ለማገልገል አልደከመውም ። አብሩዋት ተሰዷል ፣ ረሐብ ጥማቷን ፣ ጭንቅና መከራዋን ፣ ሐዘንና ችግሩዋን ተካፍልዋል ። ከእመቤታችንና ከአምላክ ልጅዋ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለ፲፮ ዓመታት አብሩዋቸው ኖርዋል ።
ቅዱስ ዮሴፍ በክርስትና ሃይማኖትም ሆነ በዓለማዊ ሕይወት ኑሮ ውስጥ ላሉ ሰዎች የምርጥ አባቶችና የጎበዝ ሠራተኞች ምሳሌ ነው ።
ያረፈውም በ፲፮ኛው ዓ.ም. በተወለደ በዘጠና አንድ ዓመቱ ነው ። ክርስቶስ የገነዘው አንድ ቅዱስ ቢኖር ቅዱስ ዮሴፍ ነው ። በዚህም ዕለት እግዚአብሔር የፅድቅ አክሊል አቀዳጅቶታል ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር