Jump to content

ታንግ

ከውክፔዲያ
ንጉሥ ታንግ፣ በ1250 ዓም ግድም እንደ ተሳለ

ታንግ (ቻይንኛ፦ 湯) በጥንታዊ ቻይና የሻንግ ሥርወ መንግሥት መሥራች ንጉሥ ነበር።

ቀዳሚው ስለ አገዛዙ በጣም ስለ ተጠላ አንዱ መኮንን የሻንግ ልዑል ሃይለኛ ሊሆን ቻለ። ብዙ ወገኖች ታማኝነት ከሥያ ንጉሥ ወደ ሻንግ ግዛት ይዛወሩ ነበር። በ1628 ዓክልበ. ታንግ የሻንግ ንጉሥ ሆነ።.ታንግ አማካሪ ሚኒስትሩን ዪ ዪንን እንደ ተልእኮ ለ፫ ዓመት ወደ ጄ ግቢ ላከው። የሻንግ ሃያላት በ1621 ዓክልበ ንና ቸንግ አሸነፉ፣ በ1620 ዓክልበ. ታንግ ለአንድ አመት ያህል በጄ እሥር ቤት ተያዘ። ታንግ ወጥቶ በ1616 ዓክልበ. ወንን አሸነፈ፣ በ1614 ዓክልበ. ዌይን ያዘና ጦርነት በና በኩንዉ ላይ ጀመረ። ያንጊዜ የጄ ዋና ዘጋቢ ዦንግ ጉ ወደ ሻንግ ወገን ሸሸ። በ1613 ዓክልበ. ጉ አውራጃ በሻንግ ተሸነፈ፣ «ሦስት ፀሓዮች አብረው ታዩ» ተዘገበ (ፍቹ ግልጽ አይደለም)፤ እና የፔ ልዑል ቻንግ ከጄ ግቢ ወደ ሻንግ ወገን ሸሸ። በ1612 ዓክልበ. ሻንግ ኩንዉን አሸነፈ።

በመጨረሻም በ1611 ዓክልበ. የሻንግ ሃያላት በሥያ ላይ በሚንግትያው ውግያ አሸነፉዋቸው። ታንግ ንጉስ ጄን ወደ ስደት አባረረውና ያንጊዜ የመላው ቻይና ንጉሥ ሆነ። በቀርቀሃ ዜና መዋዕል ውስጥ የታንግ ዘመን የሻንግ መስፍን ከሆነበት ከ1628 ዓክልበ. ጀምሮ ስለሚቆጥረው፣ ታንግ በ18ኛው ዓመት የቻይና ንጉሥ ሆነ ይላል።

ከ1610 እስከ 1605 ዓክልበ ድረስ በቻይና ዝናብ ቀርቶ ታላቅ ድርቆትና ረሃብ ይዘገባል። በ1609 ዓክልበ. ጭፍራ፣ ዘፈንና በክራር መጫወት ተከለከሉ። በ1608 ዓክልበ. ታንግ «መሐለቅ» ገንዘብ አሠራ። በመጨረሻ ንጉሡ በሾላ ደን ገብቶ ሲጸልይ ዘነበ፤ በ1604 ዓክልበ. «ታላቅ መድኅን» የተባለ ዘፈን ገጠመ። በ1602 ዓክልበ. «ዘጠኙ ድስቶች» የተባሉት የተቀደሡት ቅርሶች በታንግ ትዕዛዝ ወደ ሻንግ ዋና ከተማ ግቢ ተዛወሩ።

የቻይና መጽሐፈ ሰነዶችና የሢማ ጭየን ታሪካዊ ዘገባዎች የታንግን ዘመን በይበልጥ ተርከዋል። ለምሳሌ ሢማ ጭየን እንደ ጻፈ፣ ታንግ የአመት መባቻ ቀን ለወጠ፣ በሥነ ስርዓት ጊዜ ነጭ ወግ ልብስ መልበሱን መሠረተ። የታንግ በኲር ልዑል ዳ ዲንግ ሳይነግሥ አርፎ ሁለተኛ ልጁ ዋይ ቢንግ ተከተለው ይለናል። (ዳሩ ግን በሥነ ቅርስ ከ1200 ዓክልበ. የተገኙት «ንግርተኛ አጥንቶች» ጽሑፎች ላለፉት ነገሥታት መሥዋዕት ሲዘረዝር ዳ ዲንግም እንደ ንጉሥ ይቆጥራል በሌላ ቅደም-ተከተል ይለያያል።)

ቀዳሚው
የሥያ (ቻይና) ንጉሥ
1611-1600 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ዋይ ቢንግ